የቫቲካን ሬዲዮ የቤርሊን ግንብ መፍረስን ያበሰረበት ዕለት ተዘከረ።

የቫቲካን ሬዲዮ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 9/1989 ዓ. ም. ባስተላለፈው ግንባር ቀደም ዜናው የቤርሊን ግንብ መፍረስን የዘገበበት ቀን ታስቦ መዋሉን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዘጋቢ አሌሳንድሮ ደ ካሮሊስ የላከልን ዘገባ አመክቷል። ዘገባው የሬዲዮ ጣቢያው የዝግጅት ክፍል ሠራተኞች የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን እምነት ለመላው ዓለም ምዕመናን በየዕለቱ በማዳረስ ከፍተኛ አገልግሎት ማበርከታቸውን አክሎ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቤርሊን ግንብ የፈረሰበት 30ኛ ዓመት ያለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 29/2012 ዓ. ም በመላው የአውሮጳ አገሮች ታስቦ መዋሉ ታውቋል። የአውሮጳ አገሮች አንድ ላይ በመሆን ለነጻነታቸው እንዲቆሙ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከፍተኛ አስተቃጽዖ ማበርከታቸው የሚዘነጋ አይደለም። የጀርመን ሕዝብ፣ የምዕራብ እና የምሥራቅ በመባል ከጎርጎሮሳዊው 1961 – 1989 ዓ. ም. ድረስ በርዕዮተ ዓለምም ሆነ፣ በአካል ተለያይቶ እንዲቆይ ያደረገው ወታደራዊ መንግሥት ገንኖ የቆየበት ዘመን መሆኑ ይታውሳል። በቤርሊን ከተማ ተገንብቶ የነበረው ግድግዳ ለያይቶ የኖረው የከተማውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በቀዝቃዛው ጦርነት ዓመታት የምዕራብ እና የምሥራቅ የአውሮጳ አገሮች በማለት በአውሮጳ ውስጥም ክፍፍልን ፈጥሮ የቆየ መሆኑ ይታወሳል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በሰኔ ወር 1979 ዓ. ም. የትውልድ አገራቸው ወደ ሆነችው ፖላንድ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያካሄዱት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ኮሚኒስት አገር ወደ ሆነችው ፖላንድ ያደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ተለያይተው ለኖሩት የአውሮጳ አገሮች ትልቅ ለውጥ ያመጣ መሆኑ ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ይዘውት የሄዱት ሐዋርያዊ መልዕክት በአውሮጳ አገሮች መካከል እንዲሁም በጀርመን ውስጥ የነበረውን ልዩነት እና አምባ ገነናዊውን ስርዓት በመጣል ለውህደት ያበቃቸው መሆኑ በስፋት ይነገራል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ፖላንድ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ያስተላለፉትን መልዕክት በማስመልከት በወቅቱ የቫቲካን ሬዲዮ ጋዜጠኛ የነበረች ቪክቶሪያ ስካሪስብሪክ ያጠናቀረችው ዝግጅት በቫቲካን ሬዲዮ ማሕደር ውስጥ ተጠብቆ መቆየቱ እና ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ይፋ መውጣቱ ታውቋል።

በወቅቱ የቫቲካን ሬዲዮ ጋዜጠኛ የነበረች ቬሮኒካ አዘጋጅታ ካስቀመጠቻቸው ዝግጅቶች መካከል ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ መገኘቱ ታውቋል። ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ከዚህም በተጨማሪ በወቅቱ የምዕራብ ቤርሊን ከተማ ከንቲባ ከነበሩት ዎልተር ሞምፐር ጋር እና በምዕራብ ቤርሊን በኩል የብሪታኒያው ክፍል አዛዥ ከነበሩት ሮቤርት ኮርበርት እና ጉብቴር ሻቦስኪ መካከል የሁለቱን ቤርሊኖች ውህደት በማስመልከት የተደረገው ቃለ ምልልስ በጀርመን ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ስሜትን የቀሰቀሰ እንደነበር ከቃለ ምልልሳቸው ለማወቅ ተችሏል።

በጀርመን ውስጥ የቤርሊን ከተማ በሃያኛው ክፍለ ዘመን የናዚዎች እና የቀዝቃዛው ጦርነት ማዕከል ሆኖ በመቆየቱ ከፍተኛ ግምት ይሰጥ የነበረው የጀርመን ከተማ መሆኑ ይታወሳል። በጀርመን ውህደቱ እስከተካሄደበት፣ እስከ መስከረም 23/1983 ዓ. ም. ድረስ ቤርሊን የምዕራብ እና የምስራቅ ክፍለ ከተማ በመባል በሁለት ተከፍሎ የቆየ መሆኑ ይታወሳል። 162 ኪ. ሜ. ርዝመት ያለው የቤርሊን ግድግዳ ከ28 ዓመታት በኋላ የሚፈርስ መሆኑ ለጀርመን ሕዝቦች ሲነገር ለውሕደትም መልካም አጋጣሚን የከፈተ መሆኑ ታውቋል።        

 የቫቲካን ሬዲዮ ጋዜጠኛ የነበረች ቪክቶሪያ ከምዕራብ ቤርሊን ከተማ ከንቲባ ከነበሩት ዎልተር ሞምፐር ጋር እና በምዕራብ ቤርሊን በኩል የብሪታኒያው ክፍል አዛዥ ከነበሩት ሮቤርት ኮርበርት እና ጉብቴር ሻቦስኪ መካከል የሁለቱን ቤርሊኖች ውህደት በማስመልከት ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በመጽሐፍ መልክ ባሳተመችበት ወቅት፣ ለመጽሐፉ የሰጠችው “ምንም ልዩ ነገር አልተከሰተም” የሚል መሆኑ ሲታወስ ይህም በሕዝቡ መካከል የተቀሰቀሰውን ስሜት ለማርገብ እና ከምስራቅ ቤርሊን ከተማ ባለስልጣናትም አስቀድሞ የተነገረ ዜና መሆኑን መግለጿ ይታወሳል። የቫቲካን ሬዲዮ ጋዜጠኛ ከነበረች ከቪክቶሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ ለመረዳት እንደተቻለው ጋዜጠኛዋ የሁለቱ ጀርመኖች ውሕደትን ተከትሎ በነዋሪዎች መካከል ሊቀሰቀስ የሚችለው የሃሳብ መግለጫ ትዕይምት በሰው ሕይወት ላይ አደጋን ሊያስከትል ይችል ይሆናል የሚል ስጋት ስለነበራት መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 November 2019, 15:18