የአማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የአማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ፤ 

በአማዞን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የሴቶች የወንጌል አገልግሎት ተሳትፎ እንዲያድግ ሃሳብ ቀረበ።

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በመስከረም 28/2012 ዓ. ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው የሴቶችን የወንጌል አገልግሎት ተሳትፎ ለማሳደግ ሃሳብ አቅርቧል። 174 የሲኖዶስ አባቶች የተካፈሉበት ጠቅላላ ጉባኤ በተጨማሪም በአማዞን አካባቢ አገሮች ስለተዋቀረው የካፒታሊስት ሥርዓት የልማት አርአያ፣ በአካባቢ አገሮች ላይ የተነሳው የሰደድ እሳት ከፍተኛ ጥፋትን እያስከተለ ስለመሆኑ፣ ሙስናን በተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች፣ ስለ ደን መጨፍጨፍ እና ሕገ ወጥ እርሻ፣ እነዚህ በሙሉ ተዳምረው በአካባቢው ሕዝቦች ጤና ላይ፣ በድንበሮች እና በመላው ዓለማችን ጉዳት እያስከተሉ መሆናቸውን ገለጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በየመንደሮቻቸው ተነጥለው የሚኖሩ ሕዝቦችን ከጥቃት መከላከል፣

7.8 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአማዞን ደን በላቲን አሜሪካ የሚገኝ ሲሆን የብራዚልን፣ የቦሊቪያን፣ የፔሩን፣ የኤኳዶርን፣ የኮሎምቢያን፣ የቬነዙዌላን፣ የጉያናን እና የሱሪናም ግዛቶችን የሚያቅፍ መሆኑ ታውቋል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ በደናማው አካባቢዎች በየመንደሮቻቸው ተነጥለው የሚኖሩ ሕዝቦች ለጥቃት እና ለእርስ በእርስ አመጽ የተጋለጡ በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የቤተክርስቲያን ተቋማት ሰብዓዊ መብታቸውን በማስጠበቅ እና ለደህንነታቸው ዋስትናን በማስገኘት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪን አቅርበዋል።

ቤተክርስቲያን የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦችን ለጋራ ውይይት ታዘጋጅ፣

አንዳንድ ጊዜ ቤተክርስቲያን የነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት እና ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ አትፈጥንም ያለው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በእርግጥም ቤተክርስቲያን ከምዕመናኖቿ ርቃ በመገኘቷ ምክንያት ለአዳዲስ እምነቶች የተጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል። በመሆኑም የአብያተ ክርስቲያናት እና የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ሲኖዶሱ አምኖበታል። የባሕል ብዝሃነትን ያገናዘበ፣ በመከባበር ላይ የተመሠረተ እና ፍሬያማ የሆነ የፓን-አማዞን አካባቢ አገሮች ሕብረት ለቤተክርስቲያን እድገት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጸው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተለያዩ ባሕሎችን ማቀራረብ ቀላል እንዳልሆነ ምክንያቱም አንዱ ባሕል በሌላው ላይ የበላይነትን እንዳያሳይ ስጋት ስላለ ነው ተብሏል። ቢሆንም ባሕሎች በመካከላቸው መልካም መንገድን የተከተለ የጋራ ውይይት ካለ፣ በዚህ ውይይትም መግባባት ከተፈጠረ በሰላም አብሮ መኖር የሚቻል መሆኑን የሲኖዶሱ አባቶች አስረድተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ቤተክርስቲያን ችግሮችን ይፋ በማድረግ፣ ከምዕመናኖቿ ጋር በግልጽ በመወያየት ፍሬያማ የወንጌን ተልዕኮ አገልግሎቷን ማበርከት የምትችል መሆኑን ገልጸዋል።

የአማዞን ሕዝቦች ፍላጎትን የሚያሟላ የወንጌል አገልግሎት፣

ከአማዞን አካባቢ አገሮች ምዕመናን በኩል ከረጅም ዓመታት ወዲህ ሲቀርብ የቆየው ጥያቄ የአማዞን ሕዝቦች ፍላጎትን የሚያሟላ የወንጌል አገልግሎት ይቅረብ የሚል ሲሆን ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከምዕመናን ወገን የተመረጡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን በብቃት ማሳተፍ የሚል መሆኑ በጉባኤው መካከል ተደምጧል። የጉባኤው ብጹዓን ጳጳሳት ይህ ሃሳብ የሲኖዶሱም ሃሳብ እንደሆነ ገልጸው ቤተክርስቲያን በአካባቢው የሚገኙ የነባር ሕዝቦች ባሕልን እና የማሕበራዊ ኑሮ ወጎችን ያገናዘቡ ልዩ ልዩ የሐዋርያዊ አገልግሎት ዘርፎችን በመዘርጋት በአካባቢው ተወላጆች እንዲመሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወዲህ ምዕመናን ስርዓተ አምልኮአቸውን ከባሕላቸው ጋር ቢያዛምዱ የሚል ሃሳብ መኖሩን ያስታወሰው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በእርግጥም የአምልኮ ስርዓት እና የቅዱስ ወንጌል ብስራት የምዕመናንን ባሕል እና ቋንቋ የተከተለ መሆን እንዳለበት እና ለምዕመናን መንፈሳዊ እድገት መልካም አስተዋጽዖን ሊያበረክቱ ይችላሉ የሚባሉት ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓይነቶች ወደ ጎን መባል እንደሌለባቸው ሲኖዶሱ ገልጾ ባለ ትዳር ወንድ እና ሴት ምዕመናንን በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ ማሰማራት የሚለውን ሃሳብ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በጽሞና እንዲያስብበት ሲኖዶሱ አሳስቧል።

በቤተክርስቲያን አገልግሎት የሴቶች ሚና፣

በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት የሴቶችን ተሳትፎ አስፈላጊነት የተመለከተው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሴቶች በሐዋርያዊ አገልግሎት በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ ከወንጌል ምስክርነት በተጨማሪ በአማዞን አካባቢ አገሮች ሴቶች ላይ በስፋት የሚፈጸመውን ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ሲኖዶሱ አምኖበታል።

በብዝሃነት መካከል የሚታይ አንድነት፣

በአማዞን አካባቢ አገሮች በሚታየው የባሕል ብዝሃነት መካከል አንድነትን መመልከት በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን መልዕክት ያስታወስው የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በአካባቢው አገሮች አልፎ አልፎ ከሚደረጉ ሐዋርያዊ የጉብኝት መርሃ ግብር ወደ ቋሚ የመገናኘት እና የመደማመጥ ሐዋርያዊ መርሃ ግብር መሸጋገር፥ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ፍቅርን እና ጥበቃን የምንመሠክረው በጋራ ቤታችን ውስጥ በቅርብ ለምናውቃቸው ብቻ ሳይሆን ርቀው ለሚገኙትም ጭምር መመስከር ያስፈልጋል ብሏል። ሲኖዶሱ በማከልም በወንድማማችነት ፍቅር አብሮ የመኖር አለም አቀፋዊ እሴት፣ በመልካም አኗኗር የተገነባ ሥነ-ምህዳራዊ እሴቶች በሙሉ በዘመናችን የምናየው የስግብግብነት ሕይወት ተለውጦ መሠረቱን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲያደርግ ያግዛሉ ብሏል። ጉዳቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነገረለት የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስም ቤተክርስቲያን ስነ ምሕዳራዊ ለውጦች እንዲደረጉ ሰፊ ትምህርቶችን ለማዳረስ የሚያስችላት አጋጣሚ እንደሚሆንላት የሲኖዶሱ አባቶች ተገንዝበዋል።    

10 October 2019, 17:18