በሕንድ የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልድ ግራሲያስ፣ በሕንድ የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልድ ግራሲያስ፣ 

ካርዲናል ግራሲያስ፥ የአማዞን አካባቢ ሕዝቦች ችግር በሕንድም የሚገኝ መሆኑን አስታወቁ።

በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. በምካሄድ ላይ የሚገኘውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እንዲከታተሉ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተመረጡት፣ በሕንድ የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልድ ግራሲያስ፣ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ የአማዞን አካባቢ አገሮች አካባቢያዊ እና ማሕበራዊ ኑሮ ከሕንድ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ተነገሩ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በመከታተል ላይ የሚገኙት ካርዲናል ግራሲያስ፣ የአካባቢው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በድህነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙት እና መከራ ለደረሰባቸው የአማዞን ደናማው አካባቢ ሕዝቦች ልባዊ ፍቅር እንዳላቸው መመልከታቸውን ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን እንዲከታተሉ በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የተጋበዙት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ ባሁኑ ጊዜ የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳስት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸው ታውቋል። የሕንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሁለት የአምልኮ ስርዓቶችን የምትከተል ቤተክርስቲያን ስትሆን እነርሱም የላቲን ስርዓተ አምልኮን እና በምስራቅ ቤተክርስቲያናት መካከል የሶርያን ስርዓተ አምልኮን የሚከተሉ የማላባር እና የማላንካራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ ከዚህ የቤተክርስቲያን አገልግሎት በተጨማሪ የመላው እስያ አህጉር ብጹዓን ጳጳሳት ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል። በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤውን በሚያገባድድበት በመጨረሻው ሳምንት የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳትን ጉባኤ ከመጀመሪያው አንስቶ ሲከታተሉ የቆዩት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አንድ መሆኗን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ ከአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውይይቶች የተገነዘቡት ነገር ቢኖር በእስያ አህጉር ውስጥ በሕንድ የሚታይ ተግዳሮት የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦችን ካገጠማቸው ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል። ካርዲናል ግራሲያስ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በመሳተፍ ብዙ ነገሮችን ለመማር፣ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦችን ያጋጠማቸውን ችግሮች በቅርበት ለመገንዘብ ዕድል የሰጡትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አመስግነዋል። ካርዲናል ግራሲያስ በማከልም በሕንድ እና በአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች መካከል የሚታይ የጎላ ልዩነት አለመኖሩን ገልጸው በሁለቱም አካባቢዎች ለሚገኙ ሕዝቦች የወንጌልን መልካም ዜና ለማዳረስ የሚደረጉ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ለሕዝቦች የሚገልጽ ፍቅር፣               

ካርዲናል ግራሲያስ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ወቅት ከተገነዘቧቸው ስሜቶች መካከል አንዱ በአማዞን አካባቢ አገሮች በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ ለሚገኝ የአካባቢው ሕዝቦች ያላቸው ልባዊ ፍቅር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። የአካባቢ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በእርግጥም ድምጻቸው እንዳይሰማ ለተደረጉት እና በከፍተኛ ማሕበራዊ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሕዝቦቻቸው ድምጽ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረው፣ አመጽን፣ ጭቆናን፣ የፍትህ መጓደልን በመቃወም ድምጻቸውን የሚያሰሙ ሕዝቦችን የሚያያዳምጡ መሆናቸውን እና ለሕዝቦቻቸው የወደ ፊት ተስፋም የሚጨነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህን ሁሉ ከቅርብ ሆኖ ለመመልከት የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን መካፈላቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት አስረድተዋል።

በአማዞን ነባር ሕዝቦች ላይ የሚደርስ ጭቆና፣

በብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ መካከል በተደጋጋሚ የሚቀርብ አቤቱታ፣ በአማዞን አካባቢ አገሮች ነባር ሕዝቦች ላይ የሚደርስ ጭቆና እንደሆነ የገለጹት ካርዲናል ግራሲያስ ተመሳሳይ ችግር በአገራቸው ሕንድም የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል። መሬታቸውን በመቀማታቸው፣ የባለቤትነት መብታቸውን በመከልከላቸው የተነሳ በሕንድ ውስጥ የሚገኙ ነባር ሕዝቦች በየጊዜው ቅሬታቸውን የሚያሰሙ መሆናቸውን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ ከእነዚህ ቀደምት ነዋሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ የግል መታወቂያ ሰነድ እንኳ የላቸውም ብለው በዚህ ምክንያት መሬታቸውን በድንገት በመቀማት ለቀው እንዲሄዱ ይገደዳሉ ብለዋል።

የደን መጨፍጨፍ፣

የደን መጨፍጨፍን አስመልክተው እንደተናገሩት ምንም እንኳን የአማዞን አካባቢ አገሮችን ያህል ባይሆንም በሕንድ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ በሕንድ የኮርፖሬት ኩባንያዎች መሬቱን እየተረከቡ ስለሆነ የሀገሪቱ አረንጓዴ ሽፋን ቀስ በቀስ እየቀነሰ መምጣቱን በምሬት ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥ በአገራቸው ከፍተኛ አደጋን እያስከተለ መሆኑን የገለጹት ካርዲናል ግራሲያስ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሕዝቡ ማሳሰቢያን በመስጠት አስፈላጊው ጥንቃቄ እና እንክብካቤ እንዲደረግ ማድረጉን አስረድተዋል።

የወንጌል አገልጋዮች እጥረት፣

በቫቲካን በመካሄድ ላይ በሚገኝ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መካከል የተነሳው ሦስተኛው የመወያያ ርዕስ በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የካህናት እጥረት የሚታይ መሆኑ ተገልጿል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ምዕመናን ለስድስት ወር ወይም ደግሞ ለአንድ ዓመት ያህል ቅዱስ ቁርባንን ሳይቆርቡ የሚቆዩበት አጋጣሚ መኖሩ ተገልጿል። በሕንድ ይህ ችግር የለብንም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ በሕንድ የሚታየው ከፍተኛ ችግር በቀደምት ነዋሪዎች ላይ የሚደርስ ብዝበዛ እና የመሬት ቅሚያ ነው ብለዋል።       

23 October 2019, 15:23