የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፤  

የጳጳሳት ሲኖዶስ ትናንት ያካሄደውን ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሃሳብ አስታወቀ።

በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 26/2012 ዓ. ም. መሰብሰብ የጀመረው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ትናንት ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ጉባኤ የተወያየባቸውን ርዕሠ ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል። ጠቅላላ የጉባኤው ተካፋዮች በጋራ ሆነው የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ በሚጠናቀቅበት አካባቢ ማለትም ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ. ም. ይፋ የሚደረገውን የሲኖዶሱን የመጨረሻ ሰነድ የሚያዘጋጅ ምክር ቤትን እና የመረጃ አገልግሎት ክፍልን ማቋቋሙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለምክር ቤቱ ከሚፈለጉት አባላት መካከል አራቱ በጉባኤው ተመርጠው የቀረቡ ሲሆን የተቀሩት ሦስቱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ ቀናት መካከል የሚያቀርቧቸው መሆኑ ታውቋል።  ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላላ ጉባኤው በሌሎች ልዩ ልዩ ርዕሦች ላይ መወያየቱ ታውቋል።        

በአየር ንብረትን በተመለከተ፣

የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ወጣቶች ሊጫወቱት የሚችሉት ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል የተገነዘበው ሲኖዶስ፣ የስዊድን የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ወጣት ግረታ ታንበርግን ምሳሌ በማድረግ አቅርቧል። የአየር ንብረት የጋራ ጥቅም ማግኛ መንገድ በመሆኑ ለመጭው ትውልድ በመጨነቅ በሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል ጥበቃ እና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚያስፈልገው መሆኑን የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

የስኖዶሱ አባቶች በማከልም ዋና የአየር ብክለትን ያስከትላል ያሉትን የቅሪተ አካል ነዳጅ ጠቅሰው ነዳጁን የሚጠቀሙ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገራት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይጠቀሙ ሀሳብ አቅርበዋል።

ውሃ፣

የሲኖዶሱ አባቶች ከተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ ውሃን የተመለከተ ሲሆን በዚህ ወይይታቸው የከርሰ ምድር ውሃ በኬሚካሎች መበረዝ የለበትም ብለው እንዳይበረዝ ጥንቃቄ ሊደረግለት ያስፈልጋል ብለው ባሁኑ ወቅት በበርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶች እየደረሰ ያለው ብክለት መገታት አለበት ብለዋል።

መብት እና የአምልኮ ስርዓት፣

በአማዞን አካባቢ አገሮች ደኖች ውስጥ የሚኖሩት የተለያዩ ሕዝቦች በውሃ ሃብት ላይ ያላቸውን እምነት ቤተክርስቲያን በጥንቆላ መልክ ማየት የለባትም ብለው በአካባቢ ደህንነት ላይ አደጋን ወይም ስጋትን የሚያስከትል እስካልሆነ፣ ለማሕበራዊ ኑሮአቸው ተሚስማሚ እና ከእውነተኛው የአምልኮ ሥነ-ስርዓት ጋር ሊስማማ የሚችል ከሆነ ቤተክርስቲያን ልትቃወም አይገባትም ብለዋል።

የቤተክርስቲያን ምስጢራት፣

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ትናንትና ከሰዓት በኋላ ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባኤያቸው፣ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ሳይረሱ የቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራትን ማግኘት እንዲችሉ እና የአገልጋይ ካህናት ቁጥር ቀንሶ በሚታይባቸው አካባቢዎች በቂ ካህናት እንዲመደቡ የሚል ሃሳብ በቅድመ ዝግጅቱ ሰነድ ውስጥ እንዲካተት ሃሳባቸውን አቅርበዋል።  

08 October 2019, 16:52