በየመን የሚካሄደው ጦርነት ሰለባ ሕጻን፣ በየመን የሚካሄደው ጦርነት ሰለባ ሕጻን፣ 

ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ሴቶች የሕፃናት ሰላማዊ ሕይወት አስተማሪዎች መሆናቸውን አስታወቁ።

በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ የጸጥታው ምክር ቤት በኒው ዮርክ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተገኝተው “ሕጻናት እና በጦር መሣሪያ የታገዘ አመጽ” በሚል ርዕስ በተካሄደው ውይይት ላይ፣ ሕጻናትን ከጥቃት ለማዳን በሚደረጉ ጥረቶች ላይ በማሕበረሰቡ መካከል የሰላም ባሕል እንዲያድግ ማስተማር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጦር መሣሪያ የታገዙ አመጾች በሚሊዮኖች ለሚቆጥሩት ሕጻናት ሞት ምክንያት በመሆን ለአሁኑ እና ለወደፊቱ አጠቃላይ ማሕበራዊ ሕይወት ተጽዕኖን በማስከተል አስከፊ ጉዳቶችን እያደረሱ መሆኑ ታውቋል። በማሕበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ አመጾች፣ የሕጻናቱን ሕይወት ለማሻሻል ተስፋ ለተጣሉባቸው ጥረቶች፣ ከእነዚህም መካከል የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ማመቻቸት፣ የወላጅን ፍቅር እየተመለከቱ እንዲያድጉ ማድረግ እና በደህንነታቸው ዋስትና ላይ አደጋን ማስከተሉ ታውቋል። ድህነት፣ አስገዳጅ ለሆኑ የጉልበት ሥራ እና የውትድርና አገልግሎት መመልመል፣ ሕጻናት የሕጻንነት ዕድሜአቸውን በአግባቡ እንዳይኖሩበት የሚያደርግ እንቅፋት መሆኑ ታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ የጸጥታው ምክር ቤት በጠራው ጉባኤ ላይ፣ የምክር ቤቱን ዓመታዊ ሪፖርት በመጥቀስ እንደተናገሩት፣ በመላው ዓለም በሚቀሰቀሱት አመጾች ላይ የሚሳተፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ከእነዚህም መካከል በርካታ ሕጻናት መገኘታቸውን አስታውሰው፣ እነዚህ የአመጽ እና የጦርነት ቀጥተኛ ተሳታፊዎች የሕይወት ዋስትናን እና ጥበቃን መከልከላቸውን አስረድተዋል። 

ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ አፍሪቃን እንደ ምሳሌ ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ በአፍሪቃ ውስጥ ሕጻናት ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ በማድረግ ለግዳጅ የጉልበት ሥራ እና ለውትድርና አገልግሎት የሚመለመሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣቶችም የአክራሪነት ርዕዮተ ዓለምን እንዲከተሉ ይገደዳሉ ብለዋል።

በአፍሪቃ ውስጥ የሚካሄዱትን የውድ ማዕድናት ቅርምቶችን መመልከት በቂ ምሳሌ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶች ትምህርታቸውን በማቋረጥ በማዕድናት ማውጫ ሥራ ላይ የሚሰማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህም የባሰው በጦር መሣሪያ ትጥቅ በሚታገዙ አመጾች እና ጦርነቶች ለመሳተፍ ይገደዳሉ ብለው፣ ወጣቶችን እና ሕጻናትን በእንዲህ ዓይነት ተግባር እንዲሰማሩ ማስገደድ በቀጣዩ ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ አደጋን ሊያስከትል የሚችለው መሆኑን አስረድተው፣ የአመጾች እና የጦርነቶች መነሻ ምክንያቶችን መለየት ያስፈልጋል ብለው፣ በማሕበረሰቡ ኤኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ በማከልም በወጣቶች መካከል እየታየ የመጣው የአክራሪነት ርዕዮተ ዓለም መስፋፋት በማሕበረሰቡ እና በወጣቶች ሕይወት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከወጣቶች በኩል የሚፈጸም የአመጽ ተግባር በማሕበረሰቡ መካከል ከፍተኛ ጉዳትን ሊያከትል እንደሚችል ያስገነዘቡት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ በቤተሰብም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ ሴቶች ስለ ሰላም በማስተማር እና በመስበክ ለውጥን ማምጣት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ በማከልም በአመጽ እና በጦርነት ምክንያት የሚወድሙ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ገብተው የሚማሩባቸው የትምህርት መስጫ ተቋማት በአመጽ እና በጦርነት እየወደሙ መሆናቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረው፣ የሶርያ ሕዝቡ ከሞት እና ከመቁሰል አደጋ እንዲተርፍ፣ ጦርነቱ የበረታበት የኢድሊብ ከተማ ነዋሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከቤታቸው እንዳይፈናቀል፣ የተፈናቀሉትም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ በማለት ለፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ መልዕክት መላካቸውን አስታውሰዋል። ቅድስት መንበር፣ የተባበሩት መንግሥታት በየአገራቱ መካከል የሰላም ግንባታ ተግባራትን በማከናወን፣ የሕጻናትንም ሆነ የመላውን ማሕበረሰብ የሕይወት ዋስትናን የሚያረጋግጥ፣ ሰላምን የማሳደግ ባሕል እንዲኖር ማሳሰቧን ተናግረዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናትን መብት የሚያስከብሩ ደንቦች መኖራቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት እነዚህን ደንቦች ለማስከበር አዲስ መርሃ ግብሮችን በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አንድ ላይ በመሆን፣ ሕጻናት እና ወጣቶች በአመጽ እና በጦርነት ምክንያት ለሞት እንዳይዳረጉ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽዖን እንዲያደርጉ፣ በጦርነት ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕጻናት እና ወጣቶች በማገገም፣ ከማሕበረሰብ ጋር የሚቀላቀሉበትን መንገድ እንዲያመቻቹ በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል። የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ እርዳታም በማደግ ላይ ባሉት አገሮች የሚገኙ ደሃ እና ሰብዓዊ መብታቸውን ለተነፈጉ፣ ጭቆና እና ግፍ ለሚፈጸምባቸው ወጣቶች እና ሕጻናት እንዲደርሳቸው ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

   

05 August 2019, 16:00