የቤተክርስቲያንን ሕገ ቀኖና የቤተክርስቲያንን ሕገ ቀኖና  

ቤተክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የሚከለክሉ ሕጎች አሏት።

በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራት በቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የቤተክርስቲያን ደንቦች ውስጥ ተቀባይነት የለውም።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሕጻናት ላይ በሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች፣ ድርጊቱን በፈጸሙ ሰዎች ላይ የሚጣልባቸው ቅጣቶች እና የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዳሏት ቤተ ክስቲያን አስታወቀች። ከየካቲት 14 ቀን እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ የሚካሄደውን ስብሰባ በማስመልከት አቶ ቤርናድ ካሌባት፣ የሕገ ቀኖና አዋቂ፣ በፈረንሳይ ቱሉስ ካቶሊካዊ የሕገ ቀኖና ኢንስቲትዩት ውስጥ የሕገ ቀኖና መምህር እና ተመራማሪ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት ቤተ-ክርስቲያን በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን የሚከለክሉ ሕጎች እንዳሏት አስታወቁ።

አቶ ቤርናርድ የቤተክርስቲያንን ሕገ ቀኖና አንቀጾችን እየጠቀሱ በጻፉት 6ኛ መጽሐፋቸው ውስጥ እንደገለጹት በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራት በቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የቤተክርስቲያን ደንቦች ውስጥ ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል። በአይርላንድ እና በሰሜን አሜርካ ባሉት ካቶሊካው ሀገረ ስብከቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለከቱ እስከ 1993 ዓ. ም. ድረስ በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ወደ ቅድስት መንበር ሐዋርያዊ የካርዲናሎች መማክርት እንደማያቀርቡ ገልጸው ይህም በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጉዳትን እንዳስከተለ አስረድተዋል። ይህ ሲሆን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ የግል ውሳኔን መጠበቅ ነበረብን ያሉት አቶ ቤርናርድ የቅዱስነታቸውን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርገውም በቅድስት መንበር የእምነተ አንቀጽ ጉዳይ የሚመለከት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደሆነ ገልጸው በግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ የግል ውሳኔ፣ በታዳጊ ሕጻናት ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጸም የገዳማት አለቆች የሚያሳዩትን ቸልተኝነት ለማስወገድ ባሁኑ ጊዜ የታዳጊ ሕጻናት ደህንነት የሚከታተል እና የሚያስጠብቅ ጳጳሳዊ ምክር ቤት መቋቋሙን ገልጸዋል።

አቶ ቤርናርድ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስረዱት በታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ክስ ቢመሠረት የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ እንዲሁም የገዳማዊ ማሕበራት አለቆች ከሁሉ አስቀድመው በእርግጥም ወንጀሉ ከቤተ ክሕነት በኩል ተፈጽሞ እንደሆነ ለማጣራት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ የቀረበው ክስ የሐሰት ክስ እንዳይሆን ከከሳሾች በኩል ግልጽነት እና የሚታመን ማስረጃ ቀርቦ እንደሆነ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። አቶ ቤርናርድ በማለልም ክሱ የተመሠረተው አግባብነት ባለው መንገድ ከሆነ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ወይም የገዳማት አለቆች ጉዳዩን በቅድስት መንበር የእምነተ አንቀጽ ጉዳይን ወደሚመለከት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ

አሳስበው ከዚህም በተጨማሪ የቤተክርስቲያን አባቶች ጉዳዩን በአካባቢያቸው የዳኝነት ሥልጣን ወዳለው የመንግሥት ፍርድ ቤት ዘንድ የማቅረብ ወይም የማመልከት ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

አቶ ቤርናርድ ገለጻቸውን በመቀጠል ወንጀሉ የተረጋገጠ ከሆነ በወንጀሉ ፈጻሚ ላይ የሚጣል ቅጣት የወንጀል ፍርድ ቤት በሚከተለው እና በወንጀል መቅጫ ሕግ ላይ የተቀመጠው የቅጣት ዓይነት ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቤተክርስቲያን በኩል የተመልከትን እንደሆነ በሕጻናት ላይ ህገ ወጥ ተግባርን የፈጸመ የቤተ ክህነት ወገን ከማንኛውም የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደሚታገድ እና በሚኖርበት ገዳም ውስጥ ሊታሰር እንደሚችል አስረድተዋል። ከቤተክርስቲያን የክህነት አገልግሎት ይታገዳል ሲባል የቤተክርስቲያንንም ምስጢራት ያገናዘበ መሆን አለበት ያሉት አቶ ቤርናርድ ጥፋቱ የተረጋገጠበት የቤተ ክህነት ወገን፣ ክህነታዊ አገልግሎቱትን እንዳያበረክት ቢደረግም የክህነት ስልጣኑ በቤተክርስቲያን ምስጢራት አማካይነት፣ በአንዳንድ ልዩ ውሳኔ ካልሆነ በቀር  ቋሚ እና ዘለዓለማዊ እንደሆነ አስረድተው፣ ከጵጵስና፣ ከክህነት እና ከዲቁና የቤተክርስቲያን አገልግሎት መታቀብ ማለት የቤተክርስቲያን ክህነታዊ ምስጢራት ሙሉ በሙሉ መወገድን ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል። 

በቅድስት መንበር የእምነተ አንቀጽ ጉዳይን ወደሚመለከት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ይግባኝ ማለትን በተመለከተ፣

አቶ ቤርናርድ ክስ የተመሠረተበት የቤተክህነት ወገን በቅድስት መንበር የእምነተ አንቀጽ ጉዳይን ወደሚመለከት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ይግባኝ ማለት እንደማይችል ቢገልጹም በቅድስት መንበር ልዩ ሐዋርያዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መኖሩን አስታውሰው ይህ ልዩ ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት ትክክለኛ ማረጋገጫ የማሰባሰብ ተልዕኮ ስላለበት የተከሳሹን ይግባኝ መመልከት ይችላል ብለዋል።   

ሕገ ቀኖናው ለጥቃቱ ሰለባዎች ፍርድ መስጠትን በተመለከተ ምን መንገድ ይከተላል?

ሕገ ወጥ ድርጊት የተፈጸመባቸው ተጠቂዎች ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ ሙሉ መብታቸውን ተጠቅመው፣ ክሳቸውን ካቀረቡበት ዕለት አንስቶ ሊያገኙ የሚገባቸውን የሕግ ከለላን እና ፍርድን የማግኘት መብታቸው የተጠበቀላቸው መሆኑን አቶ ቤርናርድ አስታውቀው ሕገ ቀኖናም የጥቃቱ ሰለባዎች ፍርድን የሚያገኙበት ሂደቶች እንዳሉት አስረድተዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያን አባቶች እና ሐዋርያዊ ፍርድ ቤቱም ለጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት፣ የክስ ሂደቱን የሚከታተል ወገን እንደሚመድብ እና ሕጋዊ ጠበቃን የማቆም አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።     

21 February 2019, 17:41