2018.11.29 Conferenza Internazionale “Droghe e Dipendenze", apertasi oggi in Vaticano 2018.11.29 Conferenza Internazionale “Droghe e Dipendenze", apertasi oggi in Vaticano 

ቫቲካን በጎጂ ሱሶች ላይ የሚወያይ ስብሰባን በማስተናገድ ላይ መሆኗን አስታወቀች።

በስብሰባው ወቅት በርካታ ርዕሶች ውይይት እንደሚደረግባቸው፣ ጥናታዊ ጽሑፎችም እንደሚቀርቡ ይጠበቃል ያሉት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አባልት በማከልም የስብሰባው ተካፋዮች ባሁኑ ጊዜ አንዳንድ አገሮች የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በገበያ ላይ ሕጋዊ እያደረጉ ስለመሆናቸው፣ በቅርቡም በርካታ አገሮች ካኒቢስ የተባለ ንጥረ ነገር አጠቃቀምን ሕጋዊ ማድረጋቸው እንደ መፍትሄ ቢመለከቱትም የበለጠ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት የስብሰባው አዘጋጆች ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአደንዛዥ ዕጾችን የተለያዩ ገጽታዎች፣ የመፈወሻ መንገዶችንና የመከላከያ ዘዴዎችን የሚፈልግ የሁለት ቀን ስብሰባ ለማከሄድ ማቀዷን ቫቲካን አስታውቃለች። ስብሰባውን በበላይነት ያዘጋጀው፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት እንደሆነ ታውቋል። “አደንዛዥ ዕጾችና የአደንዛዥ ዕጾች ሱሰኝነት በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት መካከል ሊያስከትሉ የሚችሉት እንቅፋቶች” በሚል ርዕስ ከዛሬ ህዳር 20 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን በሚገኘው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ስብሰባ እንደሚካሄድ ታውቋል።

ለበርካታ ሰዎች የእድገት እንቅፋት ከሆኑት ልማዶች መካከል በስብሰባው ላይ ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ርዕሠ ጉዳዮች ዕፅ፣ ቁማር፣ ወሲብ እና ወሲባዊ ፊልሞች የሚሉ የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህ ልማዶች የሚፈወስበትንና የመከላከያ መንገዶችን ለማፈላለግ ነው ተብሏል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የስብሰባውን ጠቅላላ ዓላማ ባስታወቀበት ጊዜ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2007 ዓ. ም. ለአደንዛዥ ዕጽ አምራች ወይም አስፋፊ ግለሰቦች ያስተላለፉትን መልዕክት ጠቅሶ፣ አደንዛዥ እጾችን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ማሰራጨት ሕገወጥና አሳፋሪ ግብይት እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውን አስታውሷል። ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ ሕዝብ ቁጥር በሚያስደነድጥ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ገልጾ፣ ከዓለም ሕዝብ መካከል 5 ከመቶ የሚሆነው የተለያዩ ዕጾች ተጠቃሚ እንደሆነ ገልጿል። ከእነዚህም መካከል 29.6 ሚሊዮን የሚሆኑ አደንዛዥ እጽን በመውሰድ ለሚመጡ የጤና መቃወስ እንደሚሰቃዩ ገልጾ አደንዛዥ ዕጾችን መውሰድ ለጤና ጠንቅ እንደሆነና ፈውስም የሚያስፈልገ የጤና መቃወስ እንደሆነ ጳጳስዊ ምክር ቤቱ አስረድቷል።

በተመሳሳይ መልኩ ለአደንዛዥ ዕጾች ዝውውር መስፋፋት ምክንያቱ፣ አደንዛዥ እጾችን መውሰድ እንደ ደስታ ምንጭ፣ ተመራጭ የመዝናኛ መንገድና አልፎ ተርፎ በማሕበረሰቡ ዘንድ ራስን እንደ ሃብታም አድርጎ ስለሚያስቆጥር እንደሆነ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ አስረድቷል። በስብሰባው ወቅት በርካታ ርዕሶች ውይይት እንደሚደረግባቸው፣ ጥናታዊ ጽሑፎችም እንደሚቀርቡ ይጠበቃል ያሉት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አባልት በማከልም የስብሰባው ተካፋዮች ባሁኑ ጊዜ አንዳንድ አገሮች የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በገበያ ላይ ሕጋዊ እያደረጉ ስለመሆናቸው፣  በቅርቡም በርካታ አገሮች ካኒቢስ የተባለ ንጥረ ነገር አጠቃቀምን ሕጋዊ ማድረጋቸው እንደ መፍትሄ ቢመለከቱትም የበለጠ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት የስብሰባው አዘጋጆች ገልጸዋል። በሱስ መጠመድ ሲባል ሌሎች በርካታ የሱስ ዓይነቶ መኖራቸውን የጠቀሱት የስብሰባው አዘጋጆች፣ በኢነተርኔት ላይ በቀን በርካታ ሰዓታትን ማባከን፣ ወሲብ እና ወሲባዊ ፊልሞችን መመልከት፣ የቁማር ጨዋታዎች እንደሆኑ ጠቁመው እነዚህ ሱሶች በሱሰኞች ላይ ከፍተኛ መቅሰፍት ሆነው ቆይተዋል ብለዋል። የቁማር ጨዋታን ሕጋዊ ማድረግ ወንጀለኞችን ለማጋለጥ የሚያግዝ መንገድ ነው ተብሎ ቢታሰብም በሌላ ወገን በቁማር ሱስ የሚያዙትን ሰዎች ቁጥር እጅግ እንዲጨምር ማድረጉ ተስተውሏል ተብሏል።

በስብሰባው ንግግር የሚያደርጉት፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት እና ከእርሳቸውም ጋር ክብርት ወይዘሮ ጁሊያ ግሪሎ፣ በኢጣሊያ መንግሥት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መሆናቸውን የስብሰባው አጸጋጆች ገልጸዋል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ፌደሬሽን የጸረ አደንዛዥ ዕጽ ድርጅት ተወካዮች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕጽና ወንጀል ተቆጣጣሪ ጽሕፈት ቤት ተወካዮችና ከኢጣሊያ መንግሥት ፖሊስ ሃይሎች መካከል አንዱ እንደሚገኙበት ታውቋል።

ተሳታፊዎቹ ስብሰባው በሚዘጋበት ዕለት ማለትም አርብ ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት እንደሚካፈሉና ቀጥሎም በነጋታው ቅዳሜ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በሚያቀርቡት መልዕክት እንደሚጠናቀቅ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስታውቋል።             

 

29 November 2018, 16:17