ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ቤተክርስቲያን ከአፍሪቃ ወጣቶች ጋር መሆኗን አስታወቁ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ፕሬዚደንትና የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች የበላይ ጠባቂ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱ ሱራፌል፣ ትልቁ የአፍሪቃ ወቅታዊ ፈተና ሥራ አጥነትና ስደት እንደሆነ ለቫቲካን የዜና ምንጭ አስረድተው፣ ይህን ችግር ለመቀነስ መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የአገር ውስጥ ስደት፣

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ አፍሪቃ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለበት አህጉር እንደሆነ፣ ከእነዚህም መካከል አብዛኛው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ እንደሆነ አስረድተዋል። ስለ ወጣቶች መሰደድ ሲነሳ ወደ አውሮፓ ወይም ወደ አረብ አገሮች ስለሚሰደዱት ብቻ ይወራል። ነገር ግን 80 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የሚፈናቀሉት ወይም የሚሰደዱት በትውልድ አገራቸው ውስጥ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም ብለው ለዚህ ዋናው ምክንያት የመልካም አስተዳደር እጦትና፣ ግጭቶችን ለማስፋፋት አስተዋጽዖን የሚያደርግ፣ በውጭ አገሮች የሚታገዝ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ነው ብለዋል። በግጭቶቹም የሚሳተፉት ወጣቶች እንደሆኑ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ገልጸው ትላልቅ የውጭ አገር ኩባንያዎች ለአፍሪቃ ልማት በመጨነቅ፣ በተለይም ለገጠራማው አካባቢ ልማት አስበው ቢመጡ መልካም ይሆን ነበር ብለዋል።

የሥራ ማጣት ችግር፣

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የአፍሪቃ ወጣቶች ሐይማኖተኞች ናቸው፣ ቤተክርስቲያንም ከጎናቸው ሆና ታዳምጣቸዋለች። ነገር ግን ወጣቶች ቤተክርስቲያን ከምታቀርብላቸው አገልግሎት ራሳቸውን በሚያገሉበት ጊዜ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ይወድቃሉ ብለዋል። የኤች አይ ቪ ኤይድስ እና የሥራ እጦት ከፍተኛ የወጣቶች ችግር እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱ ሱርፌል፣ የውጭ አገር እርዳታ ሰጭ ድረጅቶች የቤተክርስቲያንን ፈለግ በመከተል፣ ከቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር፣ በትላልቅ ከተሞች ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በገጠራማው አካባቢ ላሉት ወጣቶችም እርዳታን ማዳረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

11 October 2018, 08:55