2018.10.11 IX Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 2018.10.11 IX Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 

ቤተክርስቲያን ወጣቶችን በክርስትና ጉዟቸው ሁል ጊዜ እንደምታግዛቸው ተገለጸ።

ቤተክርስቲያን ራሷን የምትገልጸው በእያንዳንዱ ወጣት በኩል ነው ያሉት የሲኖዶሱ አባቶች በወጣቶችና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለው ኢየሱስ ክርስቶስ በወጣቶች መካከል ወጣት በመሆን የአስተዳደጋቸውን ሂደት ይከታተላል ብለዋል። ወጣቶች ኢየሱስን መቀበል ማለት ለማንኛውም የሕይወት ምርጫ መሠረታዊ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ፣ ወጣቶች፣ እምነትና ጥሪያቸውን በጥበብና በማስተዋል እንዲገነዘቡ ለማድረግ በሚል የመወያያ ርዕስ 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኝው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ትናንት ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው፣ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን በክርስትና ጉዞ እንደምታግዛቸው ገለጸ። 259 የሲኖዶሱን አባቶች የተሳተፉበት የትናንትናው ጉባኤ፣ ወጣቶች ለክርስትና ሕይወት የተጠሩበትን ዓላማ በሚገባ እንዲያውቁና ቤተክርስቲያን ከጎናቸው በመሆን እንደምትረዳቸው ገልጸዋል። ትናንት የተጀመረው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሰንድ በሁለተኛው የመወያያ ክፍል “እምነትንና ጥሪን በሚገባ ተገንዝበው በተግባር መግለጽ” የሚል ርዕስ ይዞ መውጣቱ ተገልጿል። የሲኖዶሱ አባቶች በዚህ ርዕስ ላይ ሲወያዩ እንደገለጹት እያንዳንዱ ምዕመን ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ፍቅር እንዳለው፣ በዚህ ፍቅር በመነሳስት ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ ዓለምንና የሰውን ልጆች በሙሉ የመንከባከብ አደራና ጥሪ አለበት ብለዋል።  በሰዎች መካከል በርካታ ልዩነቶች ቢኖሩም እርስ በርስ መፈቃቀር፣ የምንኖርባትን ዓለም በጋራ መንከባከብ ለሁሉ የቀረበ ጥሪና አደራ መሆኑ በጥበብ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።  የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም ይህ አደራ፣ ራስን ለፍቅር በማስገዛት፣ መልካም ተግባርን በማከናወን ለቅድስናም የሚያበቃ ሁለንተናዊ ጥሪ እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በወጣቶች መካከል ወጣት ነው፣

ቤተክርስቲያን ራሷን የምትገልጸው በእያንዳንዱ ወጣት በኩል ነው ያሉት የሲኖዶሱ አባቶች በወጣቶችና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለው ኢየሱስ ክርስቶስ በወጣቶች መካከል ወጣት በመሆን የአስተዳደጋቸውን ሂደት ይከታተላል ብለዋል። ወጣቶች ኢየሱስን መቀበል ማለት ለማንኛውም የሕይወት ምርጫ መሠረታዊ ነው ብለዋል። ወደ ክርስትና ሕይወት የተጠሩትን ያህል የሕይወት ጥሪን ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት ሁኔታ ለመረዳት መሞከር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት የሲኖዶሱ አባቶች፣ ወጣትን የሚመክር፣ ወጣቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ልቡ እንዲያስገባ የሚያግዝ ረዳት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የተጠሩበትን የሕይወት አቅጣጫን በሚገባ እንዲያውቁ በማለት የሚደረግ ጥረት፣ ጥረት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ለኢየሱስ ክርስቶስ በነጻነት መልስ የሚሰጡበትና እውነተኛ የሕይወት ምስክርነትን የሚሰጡበት መንገድ እንደሆነ የሲኖዶሱ አባቶች አስገንዝበዋል።

ለወጣቶች የግልና የጋራ ድጋፍ መስጠት፣

የሕይወት ጥሪያቸውን በትክክል እንዲያውቁ ቤተክርስቲያን የምትረዳቸው ወጣቶች ከግል ሕይወት አልፎ ስለ ሌሎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ሕይወት የሚያስቡና የሚጨነቁ መሆን አለባቸው። ከቤተክርስቲያን በኩል ለወጣቶች የክርስትና ሕይወት መጎልበት ተብሎ የሚሰጥ ድጋፍ የግልም የጋራም በመሆኑ፣ ቤተክርስቲያን ለዓለም ብርሃን ሆና እንደምትገኝ ሁሉ እያንዳንዱ ወጣት በልቡ የአንድነትን መንፈስ በማሳደግ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመጓዝ የተዘጋጀ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። እውነተኛ ጥሪ የሚያስገድድ ሳይሆን በፍላጎት እንዲከናወን የሚጋብዝ እንደሆነ የሲኖዶሱ አባቶች ገልጸዋል። የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ለሕዝበ እግዚአብሔር በሚያቀርቡት ሐዋርያዊ አግልግሎት መካከል፣ እምነትን እንዴት መመስከር እንዳለባቸው፣ ከአንድነት የሚገኘውን ደስታ እንዴት መጋራት እንዳለባቸው፣ የጸሎትን ጥቅምና የወንጌል ምስክርነት አስፈላጊ በሆኑን በተግባር መግለጽ አለባቸው። ለምዕመናን ይህ አገልግሎት በሚቀርብበት ጊዜ ሁሉ  ከማንኛውም ዓይነት ጥቃቶች እንዲርቁ በማድረግ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን ያስጠበቀ መሆን አለበት።

የቤተክርስቲያን ምስጢራት ትርጉም ይገለጽ፣   

በቤተክርስቲያን ውስጥ ወጣቶችን ማገዝ ቅዱስት ምስጢራትንም በሕብረት ለመካፈል ይጠቅማል ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት በተለይም በምስጢረ ሜሮን ላይ ትኩረትን በማድረግ ወጣቶች ምስጢረ ሜሮንን ከተቀበሉ በኋላ ቤተክርስቲያንን የሚሰናበቱ ሳይሆን በተቃራኒው እምነታቸውን የሚያሳድጉበት ምስጢር እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል ብለዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም ለወጣቶች የሚሰጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮዎች ጊዜን ሰጥተው በዝግታ የሚከናወን እንጂ በችኮላ መሆን እንደሌለበት አሳስበው እግዚአብሔር የሚሰጠው ትዕግስት ትክክለኛና ግልጽ የሆነ የሕይወት ምርጫን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ለተቸገሩ ወጣቶች ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣

ከቤተክርስቲያን ተልዕኮዎች መካከል አንዱ የወጣቶችን እውቀትና አቅም በመመልክት፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለምሳሌ በአካል ጉዳትና በአእምሮ ጤና መጓደል ምክንያት ራሳቸውን መርዳት ያልቻሉ ወጣቶችን በመለየት ልዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚያስፈልግ የሲኖዶሱ አባቶች ገልጸዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም እነዚህ ወጣቶች አቅመ ደካማ ሆነው ይገኙ እንጂ በማሕበራዊ ኑሮ ውስጥ መልካም ማድረግን እንድንማር በማድረግ ለውጥን እንድናሳይ የሚያደርጉን የእግዚአብሔር ስጦታ መሆናቸውን አስረድተዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በተጨማሪ፣ እድሜአቸው እየፈቀስደ ነገር ግን በተለያዩ ማሕበራዊ፣ ስነ ልቦናዊና ተፈጥሮአዊ ችግሮች የተነሳ፣ የጋብቻ ሕይወት ያልጀመሩ ብቸኛ ወጣቶች፣ ለሕይወታቸው ትርጉም በመስጠት፣ የእግዚአብሔርን እቅድ እንዲረዱ በማድረግ ቤተክርስቲያን ማገዝ እንዳለባት አሳስበው፣ እውነተኛ ቤተክርስቲያንን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥም እያንዳንዱ ሰው መሳተፍ እንዲችል ማደረግ አለባት ብለዋል።

ወጣቶች የጊዜውን ሁኔታ የመረዳት ችሎታ፣

ዓለማችን ፈጣንና ውስብስብ በሆኑ የለውጥ ሽግግር ውስጥ ትገኛለች ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት፣ ወጣቶች ለዚህ ፈጣን ለውጥ ትክክለኛ መልስ እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን ጥበብ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊያገኙ ይችላሉ ብለዋል። ወጣቶች የጊዜውን ሁኔታ ቶሎ የመረዳት ችሎታ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ያሉት የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ወጣቱ ትውልድ ለሕይወታቸው ምን እንደሚያስፈልግ፣ ልባቸውን የሚማርክ፣ ሕይወታቸውን የሚለውጥ፣ መልካምን በማሰብ ተስፋን የሚሰጥ ማን እንደሆነ ሊያውቁ ግገባል ብለዋል።

የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች ትናንት ባደረጉት ጉባኤያቸው፣ ቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በወጣቶች ላይ የነበራቸውን እምነት አስታውሰው፣ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት በቤተክርስቲያን በመታገዝ ከራሱና ከሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር ያለውን ግንኙነት ለማዳበር የተጠራበት እንደሆነ አስረድተዋል።

16 October 2018, 18:00