“ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ይቁም” “ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ይቁም” 

ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀልን መግታት የሚቻለው ተባብሮ በመሥራት እንደሆነ ተገለጸ።

“ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ይቁም” በሚል ዓላማ፣ ቅድስት መንበር በምትመራው እንቅስቃሴ ወንጀሉን መግታት የሚቻለው ተባብሮ በመሥራት እና ለሕብረተ ሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን- ቫቲካን

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት ክፍል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ “ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ይቁም” በሚል ዓላማ፣ ቅድስት መንበር አንድ እንቅስቃሴን መጀመሯል ገልጸዋል። ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ እንደገለጹት ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወርን ወንጀል መግታት የሚቻለው ተባብሮ በመሥራት እና ለሕብረተ ሰቡ ግንዛቤን በማስጨበጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ የመጣውን አሳዛኝ ክስተት ዓለም እንዲያውቀው በማለት  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በየዓመቱ እንዲከበር መወሰኑን ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በግል የቲዊተር ማሕበራዊ መገናኛ በኩል እንደገለጹት ሕገ ወጥ ጉዞ እንዲያደርጉ ተገድደው በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እርዳታን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው የሚታውስ ነው። ሰዎችን እንደ ስብዕናቸው ሳይሆን እንደ ዕቃ በመቁጠር በየዕለቱ በሴቶች ላይ ከሚደርስባቸው ጾታዊ ጥቃት፣ የሕጻናትን ጉልበት መበዝበዝ መቆም እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሳሰባቸውን ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጀንቲና ቦይነስ አይረስ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ባገለገሉበት ጊዜም ሳይቀር በአርጀንቲና፣ በላቲን አሜሪካ እና በመላው ዓለም በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቀረት በነበራቸው ጽኑ ዓላማ፣ የጋራ ጸሎቶችን በማዘጋጀት፣ በዓላትን በማስተባበር፣ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በብርቱ ይጥሩ እንደነበር ክቡር አባ ፋቢዮ አስታውሰው፣ ቅዱስነታቸው ይህን ጥረታቸውን በማጠናከር ባሁኑ ጊዜ የስደተኞችን፣ የጥገኝነት ጠያቂዎችንና ባጠቃላይ አደገኛ በሆነ ሕገወጥ ጉዞ ላይ ሆነው የሚሰቃዩ ሴቶች፣ ወንዶች እና ሕጻናት ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መክፈታቸውን ክብር አባ ፋቢዮ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ የስደተኞችን ቀን አስፈላጊነት በማስታወስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳብ የገለጹት ክቡር አባ ፋቢዮ፣ ምንም እንኳን ዕለቱ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጸሎት ታስቦ የሚውል ባይሆንም ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ በጸሎት እንድናስታውሰው መልካም አጋጣሚ ሆኗል ማለታቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ባበረከቱባት በአርጀንቲና ዋና ከተማ፣ በቦይነስ አይረስውስጥ በሰፈራቸው እና በሮም ከተማም ሳይቀር መኖሩን እንዳስታወሱ ክብር አባ ፋቢዮ ገልጸው፣ ቅዱስነታቸው በሌላ መልዕክታቸው፣ ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ካለ፣ በዚህ ወንጀል የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች እንዳሉ መግለጻቸውን ክብር አባ ፋቢዮ ተናግረዋል። ይህ በመሆኑ ሕብረተ ሰቡ ችግሩን በተለያዩ አቅጣጫዎች መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት ክፍል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ እንደገለጹት፣ አንዳንድ ጊዜ ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል የሚመለከተው በወንጀሉ የተሰማሩትን ግለ ሰቦችን ብቻ እንደሚመለከት፣ ወይም ወንጀሉ እና የወንጀሉ ተጠቂዎች የሚበዙባቸውን አገሮች ብቻ እናስብ ይሆናል። ነገር ግን ሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀልን መከላከል የሚቻለው የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ሲታከልበት እና በዚህ ወንጀል ላይ ያለንን ግንዛቤ በማሳደግ ድርጊቱንም በመቃወም መሆኑን መዘንጋት የለብንም ብለዋል።

04 August 2018, 13:08