የቻይና ወጣቶች በሥራ ላይ ሆነው የቻይና ወጣቶች በሥራ ላይ ሆነው 

ካርዲናል ታርክሰን ወጣቶች ሥራ ከማጣት የተነሳ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው አሳሰቡ።

ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ወጣቶች ሥራ በማጣት ምክንያት ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው አሳስበው ባለማቋረጥ ሥራን መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶች ሥራ ከማጣት የተነሳ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ተገለጸ።

ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ወጣቶች ሥራ በማጣት ምክንያት ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው አሳስበው ባለማቋረጥ ሥራን መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል። ካርዲናል ታርክሰን፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወቅቱ ዋና መነጋገሪያ ርዕስ በሆነው በሥራ አጥነት ዙሪያ “Civiltà Cattolica” ወይም ካቶሊካዊ ስልጣኔ ከተባለ መጽሔት አዘጋጅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል። 

“ካቶሊካዊ ስልጣኔ” የተሰኘ አንጋፋው የጣሊያን መጽሔት በመጨረሻ እትሙ ከብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ይፋ አድርጓል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በቃለ ምልልሳቸው ወቅት አስምረው እንደተናገሩት፣ በሥራው ዓለም የሰው ልጅ ስብዕና ሊከበር የሚችለው ሥራው መልካም እና ሰብዓዊ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል። ሁሉ ሥራ መልካም አይደለም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ መልካም ካልሆኑ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹን ሲጠቅሱ፦ ጦርነት እንዲስፋፋ የሚያደርግ የጦር መሣሪያ አምራችነት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወቅት የሚፈጸም ሴተኛ አዳሪነት እና የሕጻናትን ጉልበት መበዝበዝ ጥቂቶቹ ናቸው ብለው ያለ ሕጋዊ ቅጥር የሚከናወኑ፣ ሴቶችን የሚለዩ እና ለአካል ጉዳተኞችን የሚሰጠውን አገልግሎት እንደ ሥራ የማይቆጥር አመለካከት በሙሉ የሥራን ክብር ይቀንሳል ብለዋል።

በዓለማችን የተከሰተውን ከፍተኛ የኤኮኖሚ ቀውስ እና የገንዘብ ድጋፍ መቀንስን የጠቀሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በሥራው ዓለም ዙሪያ የተመለከትን እንደሆነ በኢጣሊያ ብቻ የወጣት ስራ አጥ ቁጥር መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል። የአንድ መንግሥት የፖለቲካ ሥርዓት ለሰብዓዊ ክብር ቅድሚያን በመስጠት፣ በተለይም ለወጣቶች የፈጠራ ችሎታ መዳበር፣ ለሞያ ስልጠና እና ለሥራ እድል መክፈት፣ ገንዘብን ለግል ጥቅም እና ለማይገባ ተግባር ከማፍሰስ ይልቅ ተቋማትን በገንዘብ ማገዝ ወይም መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን የሰውን ክብር የሚያስጠብቁ የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላት የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ያለ ሥራ መኖር እንደማይቻል ገልጸው ሰብዓዊ ክብርን በሚገባ ማስጠበቅ የሚቻለው ሥራ ሲኖር ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም በቤተክርስትያን ማህበራዊ አስተምህሮአቸው ሥራ ከሰው ልጅ ክብር ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚናገሩ ስለዚህ ነው ብለዋል። ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስፈላጊነትን በሚገባ የተገነዘበች በመሆኑ ሕገ ወጥ የሆኑ ሥራዎችን ወይም ሰብዓዊ ክብርን የሚያጎድፉ ሥራዎች እንዳይኖሩ የማድረግ፣ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በመክፈት የበኩሏን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ትገኛለች ብለዋል። ይህን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን በኢጣሊያ እና በሌሎችም አገሮች፣ ለምሳሌ አውስትራሊያን በመሳሰሉ አገሮች የሥራ ዕድልን በመፍጠር ከመንግሥት ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች ብለው፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ በተለያዩት ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎችና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸቷን ገልጸዋል።

በሥራ እና በሠራተኛ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ፍትሃዊነ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ለሠራተኛ የሚከፈል ደመወዝ ፍትሃዊ፣ ቤተ ሰብን ከመመገብ አልፎ ልጆችን ለማስተማር እና ለማሰልጠን የሚያስችል መሆን አለበት ብለዋል። ምክንያቱም ልጆች በተለያዩ ሞያዎች የሰለጠኑ እንደሆነ ሥራን የማግኘት ዕድል ስለሚሰፋ፣ ይህ ደግሞ ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በማከልም ሙስና የሰዎችን ሁለ ገብ እድገት የሚያደናቅፍ እንቅፋት እንደሆነ ገልጸው ባሁኑ ጊዜ በበርካታ አገሮች ያለው የሥራ ዕድል የተቀጣሪዎችን ችሎታን ያገናዘበነ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በሥራው ዓለም በርካታ ለውጦች መከሰታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ዘመኑ ያፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሥራ ዕድልን እየቀሙ መሆናቸውን ይህም አስቀድሞ የነበረው የሥራ ክፍፍል ባሕል እንዲጠብ ማድረጉን አስታውሰዋል። ቢሆንም ሰዎች ከዚህ ለውጥ ጋር ራሳቸውን ማለማመድ እንደሚያስፈልግ ተናግረው የተክኖሎጂ ውጤቶችም ቢሆኑ በሥራው ዓለም ተጨማሪ እገዛን የሚያበረክቱ  እንጂ የሰውን የሥራ አቅም ለመተካት አለመሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በተጨማሪም ለስደተኞች የሚከፈለው የጉልበት ዋጋ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸው ይህም ባጠቃላይ ለሥራ የሚሰጠውን ተገቢ እና ትክክለኛ ክፍያን አሳንሶታል ብለዋል። ስደት በብዛት ከሚታይበት ከመጨረሻዎቹ ዓመታትም አስቀድሞ የሥራ ተቋማት ትርፎቻቸውን ለማሳደግ ብለው የምርት ተቋሞቻቸውን ዝቅተኛ የጉልበት ክፍያ ወደ ሚገኝበት ወደ ሦስተኛው ዓለም ማዛወራቸውን አስታውሰዋል። ይህንን ለመዋጋት ትክክለኛው መንገድ በማደግ ላይ ያሉ የሦስተኛው ዓለም ሰዎች የኑሮ ደረጃ መሻሻል እንዳለበት በተለይም ስደትን መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በመጨረሻም፣ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፣ ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ሥራን በማጣት ምክንያት ተስፋቢስ  እንዳይሆኑ፣ ባለማቋረጥም ሥራን መፈለግ እንዳለባቸው እና ሥራን ለመፍጠር የሚያስችሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።  

03 August 2018, 17:07