ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን  

ቤተ ሰብ በሚኖሩበት እና በዓለም ሁሉ የሰብዓዊ ክብር ባለ አደራዎች ናቸው

አነሰም በዛ፣ ቤተ ሰብ ስለ ሰብዓዊ ክብር ምስክርነትን በመስጠት አስተዋጾን ሊያበረክቱ እንደሚችል፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ አስታወቁ።

ዮሐንስ መኰንን - ከቫቲካን

ቤተ ሰብ በሚኖሩበት እና በዓለምም ሁሉ የሰብዓዊ ክብር ባለ አደራዎች መሆናቸው ተነገረ።

አነሰም በዛ፣ ቤተ ሰብ ስለ ሰብዓዊ ክብር ምስክርነትን በመስጠት አስተዋጾን ሊያበረክቱ እንደሚችል፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ አስታወቁ።  ብጹዕ ካርዲናል ይህን የተናገሩት ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ. ም. በፈረንሳይ አገር ፋጢማ በተባለ ሥፍራ ተገኝተው፣ የኖተርዳም ኤኩፔስ በመባል በሚታወቀው የባለ ትዳሮች መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ከሌሎች በርካታ ርዕሶች መካከል፣ የስብዓዊ ክብር አስፈላጊነት፣ በቤተ ክርስቲያን ምስጢራት አማካይነት በተዋሄደው በቤተ ሰብ በኩል ዋስትናን ሊያገኝ ይችላል፣ መኖሪያ ቤቱን የመንከባከብ ሃላፊነት ያለው ሰው፣ የጋራ መኖሪያ የሆነውን ዓለማችንን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ሃላፊነት እና አደራን ጠንቅቆ ያውቀዋል በማለት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በማከልም፣ ቤተሰብ ክብራቸው ተጠብቆላቸው፣ በስነ ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ ተጠርተውል ብለዋል።

በቤተ ሰብ ውስጥ የሚኖር ሰው፣ በዚያ ቤተ ሰብ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ጤናማ ግንኙነት አስፈላጊነት በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ የሰው ልጅ ማሕበራዊ እንደመሆኑ አብረውት ከሚኖሩት ጋር የሚገናኝበት በርካታ መንገዶች አሉት ብለዋል። ይህን የአንድነት እና የሕብረት ጎዳናን በመከተል፣ ቤተ ሰብ ቀዳሚ ምሳሌ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ሰብዓዊ ክብርን ከአካባቢ ወይም ከተፈጥሮም ጋር ሊኖረውን ግንኙነት ያስታወሱት ካርዲናል ታርክሰን፣ የሰው ልጅ ማሕበራዊ እና ቤተ ሰብንም በመመስረት በሕብረት ለመኖር የሚችል እና የማሕበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆን በሕብረተ ሰብ መካከል ሊኖር እንደሚችል አስረድተዋል።

ቤተ ሰብ በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ተግዳሮቶችን ያስታወሱት ካርዲናል ታርክሰን፣ ቤተ ሰብ መጠነ ሰፊ ችግሮች እንደተደቀኑበት ተናግረው ከእነዚህም መካከል በጣም ዝቅተኛ የወር ገቢ፣ ሥራ ማጣት፣ በተለይም ራስን ማስተዳደር ካለመቻል የተነሳ ከቦታ ወደ ቦታ ወይም ከአገር ወደ አገር በሚያደርጉት አደገኛ የስደት ጉዞ ወቅት የጉልበት ብዝበዛ እና የባርነት ሕይወት እንደሚያጋጥማቸው አስታውሰዋል። በዓለም ዙሪያ በተከሰተው የአየር ለውጥ ምክንያት በርካታ ቤተ ሰብ በመጠጥ ውሃ እጥረት፣ በምግብ ማነስ፣ በመጠለያ እጦት የሚጎስቆሉ መኖራቸውን ካርዲናል ታርክሰን አስታውሰው የዉሃ እጥረት በሚታዩባቸው አካባቢዎች በእርሻ ሥራ እና በዓሣ እርባታ የሚተዳደሩ ቤተ ሰቦች ችግር እንደሚደርስባቸው አስረድተዋል።

ቤተ ሰብ ለተለያዩ ችግሮች ቢጋለጡም፣ ለችግር ከመጋለጣቸው አስቀድመው ጥንቃቄን ሊወስዱ፣ ችግሩ ከደረሰባቸውም በኋል የሚላቀቁበትን መንገድ ማግኘት እንደሚችሉ አስረድተዋል። ከእነዚህም መካከል ቤተ ሰብ አላስፈላጊ ብክነቶችን ወይም ወጪዎችን በመቀነስ እገዛ ለሚያስፈልገው ቤተ ሰብ የልግስና እጁን መዘርጋት ይችላል ብለዋል። በተጨማሪም ቤተ ሰብ ቀጥታ ተሳትፎን በማከል አንዳንድ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ማበርከት እንደሚችሉ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን አስገንዝበዋል።

24 July 2018, 09:11