ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ድጋፍ ተማጽነዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ድጋፍ ተማጽነዋል  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን ለሚያደርጉት ጉብኝት የቅድስት ማርያምን ድጋፍ ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሁለቱ የአፍሪካ አገራት ማለትም በኮንጎ ዴሞክርሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድጋፍን በጸሎት ተማጽነዋል። ጥር 22/2015 ዓ. ም. ሮም በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ደርሰው ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በኮንጎ ዴሞክርሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት 40ኛው ዓለም አቀፍ ጉብኝት ሲሆን፣ በዋዜማ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ደርሰው አጭር ጸሎት አቅርበው መመለሳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል። በሁለቱ አገራት የሚያደርጉትን የስድስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በይፋ የጀመሩት ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።    

በኮንጎ ዴሞክርሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ መዳረሻ አገር ኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፓብሊክ ስትሆን፣ የሚጎበኟትም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ታውቋል። ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ በ1985 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዚያች አገር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አካሂደው መመለሳቸው እና በጊዜው አገሪቱ ዛዬር ተብላ ትጠራ እንደነበር ይታወሳል።  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ጉብኝት ቀጥለው ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚሄዱ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ደቡብ ሱዳንን ሲጎበኙ ይህ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ መግለጫው ገልጾ፣ ቅዱስነታቸው በሁለቱ የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ንግደት የዕርቅ፣ የተስፋ እና የሰላም መልዕክተኛ በመሆን መሆኑን መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጉዞአቸው ቀን አስቀድመው፣ እሑድ ጥር 21/2015 ዓ. ም. ለሁለቱም አገራት ሕዝቦች ባስተላለፉት ልባዊ ሰላምታ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በተለይ ምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍሎች መሣሪያ የታጠቁ አማጺያን በሚቀሰቅሱት ግጭቶች እና በብዝበዛ መሰቃየታቸውን አስታውሰው፣ ደቡብ ሱዳንም ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት በርካታ ዜጎቿ ከቀያቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግር የዳረጋቸው የማያቋርጥ ብጥብጥ እንዲያቆም መፈለጓን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመጀመሪያ መዳረሻ አገር በሆነችው ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ከማክሰኞ ጥር 23-26/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆዩ፣ ከዚያም ዓርብ ጥር 26/2015 ዓ. ም. ወደ ደቡብ ሱዳን በመጓዝ እስከ ጥር 28/2015 ዓ. ም. ድረስ በሚያደርጉት ቆይታ በግጭት ለቆሰለው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ የሰላም ተስፋን የሚሰጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያካሂዱ ታውቋል።

31 January 2023, 09:37