ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ካናዳ ያደረጉት ጉዞ ከሌሎች የተለየ የንስሐ ንግደት እንደነበር ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐምሌ 27/2014 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን፣ በሉቃ. 24:13-15 ድረስ በተጻፈው ላይ በማስተንተን ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ጣሊያንን ጨምሮ ከተለያዩት አገራት ለመጡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች ባቀረቡት አስተምህሮ፣ ወደ ካናዳ ያደረጉት ጉዞ ከሌሎች ሐዋርያዊ ጉብኝቶች የተለየ የንስሐ ንግደት እንደነበር አስረድተዋል። የዝግጅታችን ተከታታዮች ቅዱስነታቸው በካናዳ ከሐምሌ 17 - 24/2014 ዓ. ም ድረስ ያደረጉትን 37ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ ያደረጉትን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እናቀርብላችኋለን። በቅድሚያ በዕለቱ የተነበበውን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እንመልከታለን።

“በዚያኑ ቀን ከኢየሱስ ደቀ መዝቃሙርት ሁለቱ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ነበር። ኤማሁስ ከኢየሩሳሌም አሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝ መንደር ናት። እነርሱም ይህን የሆነውን ነገር አንስተው እርስ በእርሳቸው ይወያዩ ነበር። ይህንንም በሚያወርሩበትና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ እብሯቸው ይጓዝ ነበር።”

(ሉቃ፣ 24:13-15)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት በቅርቡ ወደ ካናዳ ያደረግሁትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አብሬአችሁ ማስታወስ እፈልጋለሁ። ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ከሌሎች ሐዋርያዊ ጉብኝቶች የተለየ ነው። በእርግጥም የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ዋና ዓላማ ከአገሩ ቀደምት ሕዝቦች ጋር ለመገናኘት፣ ለእነርሱ የነበረኝን ቅርበት እና የተሰማኝን ህመም ለመግለፅ እና በአንዳንድ ክርስቲያኖች በኩል ለደረሰባቸው ጉዳት ይቅርታን ለመጠየቅ ነበር። ከእነዚህ መካከል በርካታ ካቶሊካዊ ምዕመናን በግዳጅ የባሕል ውህደት ፖሊሲዎች ውስጥ በጊዜው ከነበሩ መንግሥታት ጋር ይተባበሩ ነበር።

ከዚህ አንፃር፣ በካናዳ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ለተወሰነ ጊዜ ከአካባቢው ተወላጆች ጋር በመሆን እያደረገች ያለውን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ፣ ጠቃሚ ታሪኮችን ለመጻፍ ሂደት ተካሂዷል። በእውነቱ የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃልም "አብረን እንራመድ" የሚል ነበር። የዕርቅ እና የፈውስ ጉዞ፣ ለታሪካዊ ክስተቶች እውቅናን የሚሰጥ፣ ከአደጋ በመትረፍ በሕይወት ያሉትን ማዳመጥ፣ ግንዛቤ እንዲኖር እና ከሁሉም በላይ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚደረግበት ነበር። ከዚህ እውነታ እንደምንረዳው፣ በአንድ በኩል፣ አንዳንድ ምዕመናን ቆራጥ እና ደፋር ከሆኑ የአገሬው ቀደምት ተወላጆች ሰብዓዊ ክብር በመደገፍ፣ ተከላካይ ባይኖራቸውም ቋንቋቸውና ባሕላቸው እውቅናን እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋፅዖን አበርክተዋል። ነገር ግን በአንጻሩ የሚያሳዝነው ዛሬ ላይ ተቀባይነት የሌላቸው እና ቅዱስ ወንጌልን በሚቃረኑ እቅዶች ላይ የተሳተፉም አልጠፉም።

በመሆኑም ይህ የካናዳ ሐዋርያዊ ጉዞዬ “የንስሐ ጉዞ” ነበር። በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ወቅት ብዙ አስደሳች ጊዜያት ቢኖሩም ነገር ግን ጠቅላላ ስሜቱ የንስሃ እና የእርቅ ነበር። ከአራት ወራት በፊት ከካናዳ የመጡ ልዩ ልዩ የቀደምት ነዋሪዎች ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብያቸው ነበር።  ነገር ግን የእኔ ፍላጎት፣ ልክ እንደ እነርሱ፣ ቀደምት አያቶቻቸው በኖሩበት በካናዳ መገናኘት መቻል ነበር። ይህም እንዲሳካ እግዚአብሔር ፈቃዱ ስለሆነ  በቅድሚያ ምስጋናችንን ለእርሱ እናቀርብለታለን።

የሐዋርያዊ ጉብኝቴ ታላላቅ ደረጃዎች ሦስት ነበሩ፡- የመጀመሪያው በምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍል በሚገኝ በኤድመንተን ያደረግሁት ጉብኝት ነበር። ሁለተኛው ወደ ክቤክ ያደረግሁት ሲሆን፣ ሦስተኛው ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ወደ ሆነው ወደ ኢካሊት ያደረግሁት ጉብኝት ነበር። ከእነዚህ ሥፍራዎች መካከል ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ከመጡት ታዋቂ የቀደምት ነዋሪዎች መሪዎች ጋር በመጀመሪያው የተገናኘሁት በማስኳቺስ ነበር። ይህ ቦታ በካናዳ ውስጥ ሜቲስ እና ኢንዊት የተባሉ የመጀመሪያዎቹ ብሔረሰቦች የኖሩበት ሥፍራ ነው። በዚህ ሥፍራ ከልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የሺህ ዓመታት ታሪክ ጥሩ ትውስታዎችን፣ ከመሬታቸው ከባሕላቸው ጋር ተዋህደው በደስታ የኖሩበትን ጊዜ እና በተሳሳቱ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ምክንያት በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር የሚደርስባቸውን በደል እና ግፍ በጋራ ያስታወስንበት ሥፍራ ነው። በከበሮ የታጅብንበት፣ ገዥ እና ተገዥ የሌለበት፣ በወንድማማችነት እና እህትማማችነት ስሜት ሁላችንም ለጋራ ጸሎት ጊዜን እና ቦታን የሰጠንበት አጋጣሚ ነበር።

ከዚህ የትዝታ ጊዜ በኋላ የጉዟችን ሁለተኛ እርምጃ የእርቅ ሂደት የተከናወነበት ጊዜ ነበር። በመካከላችን አንዳች አለመስማማት አልነበረም፤ ሰላማችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ራሳችንን ለእርቅ ያቀረብንበት ጊዜ ነበር። “ለያይቶን የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰ እና አይሁዳዊያንን እና አሕዛብን አንድ ያደረገን ሰላማችን ክርስቶስ ነው።” (ኤፌ. 2:14) ይህን ሥነ ሥርዓት ያከናወንነው የዛፍን ምስል እንደ ምልክት በመውሰድ ነበር። ዛፍ በአገሬው ተወላጆች መካከል አዲስና ሙሉ ትርጉሙ የተገለጠበት የሕይወት ተምሳሌትነት ማዕከል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙም ሰላምን አደረገ (ቆላ. 1:20) በመስቀሉ ዛፍ ላይ ስቃይ ወደ ፍቅር፣ ሞት ወደ ሕይወት፣ ጥርጣሬ ወደ ሙሉ ተስፋ፣ ብቸኝነት ወደ ኅብረት፣ መራራቅ ወደ አንድነት ይለወጣል። ወንጌልን የተቀበሉ እና ሕይወታቸውን ከወንጌል ጋር ያዋሄዱት ቀደምት የአገሬው ማህበረሰቦች ክርስቲያናዊ ምሥጢርን በተለይም የመስቀል እና የቅዱስ ቁርባንን ገጽታ እንድናድስ ረድተውናል። በዚህ ማዕከል ዙሪያ ማኅበረሰብ ይመሠረታል፣ ክፍት እና ሰፊ እንግዳ ተቀባይ፣ የዕርቅና የሰላም ድንኳን የሆነው ቤተ ክርስቲያን ይገነባል።

በሦስተኛው የጉዞ ደረጃ ያለፈውን ታሪክ በማስታወስ እርቅን ማድረግ እና ከዚያም ፈውስ ማግኘት ነበር። ይህን ያከናወንነው የቅዱስ ኢያቄም እና የቅድስት ሐና ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት ዕለት፣ በቅድስት ሐና ሐይቅ ዳርቻ ነበር። ለኢየሱስ ክርስቶስ ሐይቅ በአደባባይ ሕይወቱ ውስጥ ጥሩ ክፍል ያለው የታወቀ አካባቢ ነበርና፤ በማር. 3: 7-12 ላይ እንደምናገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ሐይቅ ላይ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር አብሯቸው ነበር፤ ሁሉም ዓሣ አጥማጆች ነበሩ፤ በዚያም እያስተማረ ብዙ ድውያንን ፈወሰ። እኛ ሁላችንም የሕይወት ውሃ ምንጭ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ቁስላችን የሚፈውስበትን ጸጋ ማግኘት እንችላለን። አንድነትን ወደሚሰጥ፣ የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎች ጉዳት እና መከራ ፣ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ ወደሚገልጥ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይዘን መጥተናል። በመላው ዓለም የሚገኙ ድሆች እና የተገለሉ ሰዎች ቁስልን፣ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁስሎችንም ጭምር ይዘን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ቀርበናል።

ከዚህ የትዝታ፣ የዕርቅ እና የፈውስ ጉዞ፣ በካናዳ እና በሁሉም ቦታ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ይገኛል። የኤማሁስ ደቀ መዛሙርት ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ጋር ከተጓዙ በኋላ፡- ምስጋና ለእርሱ ይድረሰው እና እነዚያ ደቀ መዛሙርት ከውድቀት ወደ ተስፋ ተሸጋግረዋል።(ሉቃ. 24:13-35) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በታሪክ ውስጥ ስንት ጊዜ በኤማሁስ መንገድ ተመላልሰዋል? ክርስቲያኖች በኃጢአታቸው ምክንያት ስንት ጊዜ ውርደት ካጋጠማቸው በኋላ፣ በእግዚአብሔር ታማኝነት የተነሳ ተስፋን አግኝተዋል! እግዚአብሔር ብቻችንን አይተወንም፤ በድካማችን እና በሐዘናችን ጊዜ ሁሉ አብሮን ይጓዛል፤ በቃሉ ያፅናናናል፤ የአዲስ እና ዘለዓለም ሕይወት እንጀራ ይመግበናል።

አስቀድሜ እንደተናገርኩት ከአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ጋር በኅብረት የተደረገው ጉዞ የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ክፍል ሆኖ ተገኝቷል። በአገሪቱ ከሚገኙ አቢያተ ክርስትያናት እና ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ሁለት ስብሰባዎች ተካሂደኖ አኝቼዋ። ስለዚህ ለእኔ እና ለተባባሪዎቼ በሙሉ ስለተደረገልን ደማቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን ለማደስ እፈልጋለሁ። በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት፣ በአገሬው ቀደምት ነዋሪዎች ተወካዮች እና በዲፕሎማሲያዊ አካላት ፊት ቅድስት መንበር እና የአገሪቱ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ፣ ቀደምት ባሕሎችን በተገቢው መንፈሳዊ መንገዶች፣ ለሕዝቦች ልማዶች እና ቋንቋዎች ትኩረትን ለመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጫለሁ።ከዚሁ ጎን ለጎን የቅኝ ገዥነት አስተሳሰብ ዛሬ በተለያዩ የርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛት ስር እንደሚገኝ፣ የህዝቦችን ወግ፣ ታሪክ እና ሃይማኖታዊ ትስስር አደጋ ላይ እንደሚጥል፣ ልዩነቶችን እንደሚያበላሽ፣ በጊዜያዊ ነገሮች ብቻ የሚያተኩር እና አብዛኛውን ጊዜ ለአቅመ ደካሞች የሚያስፈልጉ ግዴታዎችን እንዴት ወደ ጎን  እንደሚተው ተመልክቻለሁ። 

ጤናማ እና ሚዛናዊነት ያለውን ግንኙነት መልሶ የመገንባት ጥያቄ ነው። በዘመናዊው እና በአያቶች ባሕል መካከል፣ ዓለማዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን ለማስማማት መሞከር በዓለም ዙሪያ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለመመስከር እና "ለመዝራት" ከተነሳው ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት እሴቶች ጋር በቀጥታ ይጋጫል። (“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ቁ. 142-153) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጤናማ ግልጽነት ከማንነት ጋር ፈጽሞ አይጋጭም። ከየትኛውም የባሕል ጫና ውጪ በሆኑ ባሕሎች መካከል ለሚፈጠር ተከታታይ ውህደት ምስጋና ይግባውና፣ ዓለም አድጋ በአዲስ  ውበት ተሞልታለች። (“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ቁ. 148) ከዚህ አንጻር፣ በካናዳ ውስጥ ያሉ ሐዋርያዊ አገልጋዮች፣ ገዳማውያን፣ ገዳማውያት እና ምእመናን፣ የኪቤክ የመጀመሪያ ጳጳስ የሆነው የቅዱስ ፍራንሷ ደ ላቫልን ፈለግ እንዲከተሉ፤ ወንጌልንና ድሆችን እንዲያገለግሉ፣ ​​የተስፋ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ብርታትን ተመኝቼላቸዋለሁ።

የተስፋ ምልክት በሆነው እና የመጨረሻው የጉብኝት አካባቢ በሆነው በኢንዊት ምድር ከወጣቶች እና ከአዛውንት ጋር ተገናኝተን ነበር። በካናዳም ቢሆን ይህ የወጣቶች እና የአዛውንት ጥምረት ወጣቶች እና አዛውንት በታሪክ፣ በትዝታ እና በትንቢት መካከል እየተወያዩ አብረው መራመድ እንደሚያስፈልግ ያስረዳል። የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎች የነበራቸው ጽናትና ሰላማዊ ተግባር፣ ፍጥረትንና ፈጣሪን እንዴት መውደድ እንደሚገባ፣ ለወንድማማችነት ሕይወት ጠቃሚ አስተዋጾ ለማበርከት መልካም አርአያ ሊሆን ይገባል።”

03 August 2022, 16:57