ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ማለቂያ የሌለውን ጥፋት ለማስቆም ሰብዓዊ ወንድማማችነት ማጠናከር ይገባል አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 2ኛውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የቪዲዮ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ሁሉም ሰዎች የሰው ልጅን የሚከፋፍሉ ጭፍን ጥላቻና ግጭቶችን ለማስወገድ አስቸጋሪውን የወንድማማችነት ጎዳና እንዲከተሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ ወንድማማችነት ቀን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የተቋቋመው ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለአለም ሰላም እና አብሮ ለመኖር አስፈላጊ ነው የተሰኘው ሰነድ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቅ ኢማም አህመድ አል ጣዬብ እ.አ.አ በየካቲት 4 ቀን 2019 ዓ.ም በአቡ ዳቢ የተፈራረሙትን ሰነድ ለማስታወስ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለተ አርብ ጥር 27/2014 ዓ.ም ዓለም ለዚህ ታሪካዊ ክስተት የተዘጋጀውን ሁለተኛ ቀን ሲያከብር በቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል። ርእሰ ሊቃነ ጳጳሱ እንዳሉት ወንድማማችነት እንደ “ጥላቻ፣ ዓመፅ እና ኢፍትሃዊነት ማሸነፊያ መሣርያ” ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብለዋል።

ብዙ ሰዎችን እና ድርጅቶችን በተለይም ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ፣ የአቡ ዳቢ አልጋ ወራሽ እና የሰብአዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ - የሰነዱን እሴቶች ተግባራዊ ለማድረግ ላደረጉት ብዙ ተነሳሽነት አመስግነዋል።

“ወንድማማችነት በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ከሚገባቸው መሰረታዊ እና አለም አቀፋዊ እሴቶች አንዱ ነው፣ ስለዚህም በመከራ ውስጥ ያሉ ሰዎች ወይም የተቸገሩ ሰዎች የተገለሉ እና የተረሱ እንዳይመስላቸው፣ ነገር ግን እንደ አንድ የሰው ቤተሰብ አካል ሆነው እንዲቀበሉ እና እንዲደገፉ የወንድማማችነትን መንፈስ ማጠናከር ይገባል” ብለዋል።

እግዚአብሔርን ማምለክ ፣ ባልንጀራን መውደድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት፣ ሁሉም ሰዎች፣ ሃይማኖትና እምነት ሳይለያዩ፣ ሁሉንም የሚቀበል “የሰላም ባህል” እንዲያራምዱ ተጠርተዋል፣ ልማትን እና አብሮነትን የሚያበረታታ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ተጠርተዋል ብለዋል።

በመልእክቱ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ሁላችንም የምንኖረው በአንድ ሰማይ ስር ነው" የሚለውን ማረጋገጫ እና የቆዳችንም ቀለም ሆነ የህብረተሰብ ክፍል ምንም ይሁን ምን ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ማሰብ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

ሌሎች “ዓይናቸውን ወደ ሰማይ እንዲያነሱ እና ጸሎታቸውን እንዲያደርሱ” በመርዳት እያንዳንዱ ሰው ዓለምን የተሻለች ቦታ በማድረግ ረገድ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

“እግዚአብሔርን በቅን ልብ የሚያመልክ ሁሉ ባልንጀራውን ይወዳልና ዓይኖቻችንን ወደ ሰማይ እናንሳ። ወንድማማችነት የሁሉም አባት ለሆነው ፈጣሪ ራሳችንን እንድንከፍት ያደርገናል እናም ሌሎችን እንደ ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን እንድንመለከት፣ ህይወታችንን እንድናካፍል፣ እንድንረዳዳ እና እንድንዋደድ እና ሌሎችን እንድንተዋወቅ ያስችለናል” ብለዋል።

"በብዝሃነት ውስጥ ያለ አንድነት"

ዓለም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተጋፈጠ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እኛ ብቻችንን እንዳልዳንን ማስታወስ አለብን ብለዋል። ይልቁንም “አንድነታችንን በልዩነት ለማክበር እጆቻችንን መዘርጋት አለብን - አንድነት ወጥነት ማለት አይደለም” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።

አክለውም “የወንድማማችነት ጊዜ ደርሷል” ስለሆነም “እርስ በርስ ተባብረን ለመኖር” መጣር አለብን ብለዋል።

በተጨማሪም “ሦስተኛው ዓለም ጦርነት በጥቂቱም ቢሆን እየተካሄደ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው ሕይወትን የሚያጠፉ፣ ልጆች በረሃብ እንዲያልቁ የሚያደርግ እና የሚያስገድድ እንዲሁም የትምህርት እድሎችን የሚገቱትን ብዙ ትናንሽ ጦርነቶች እንዳሉ አውስተው በዚህ ጉዳይ እጅጉን እንደ ሚያዝኑ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አክለው ገልጸዋል።

"አሁን የቸልተኝነት ጊዜ አይደለም፤ ወይም ወንድሞች እና እህቶች ነን፣ ወይም ሁሉም ነገር ይፈርሳል" ብለዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳሉት አንዳችን ለሌላው መከራ ግድየለሽ መሆን የለብንም ። እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው የተስፋ ቃል የክርስቲያኖች፣ የሙስሊሞች እና የአይሁዶች የጋራ ቅርስ ሆኖ ከእኛ ጋር ይተባበርና “እንደ ሰማይ ከዋክብት የሰፋና የደመቀ ወንድማማችነት” እንድንኖር ይረዳናል ብለዋል።

የመዳን መልሕቅ ለሰው ልጆች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በድጋሚ “ውድ ወንድማቸውን” ለታላቁን ኢማም ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ እና የወንድማማችነት መንገድ “ረጅም እና ፈታኝ” ቢሆንም “የሰው ልጅ የመዳን መልህቅ” መሆኑን አስምረውበታል።

"ብዙውን አስጊ ምልክቶች፣ የጨለማ ጊዜ እና የግጭት አስተሳሰቦች ሌሎችን በመቀበል እና ማንነታቸውን በማክበር ወደ የጋራ ጉዞ የሚጋብዛቸውን የወንድማማችነት ምልእክት እንልካለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ማንኛውም ሰው በማንነቱና በሰባዊነቱ ሊከበር ይገባል ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው ገልጸዋል።

ሁላችንም “የእግዚአብሔር ፍጥረታት፣ ወንድሞችና እህቶች” ስለሆንን ዓለም ተስማምቶ መኖር ይችላል ብለው ለሚያምኑ ሁሉ አመስግኗል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ "ሁሉም ለሰላም ዓላማ እንዲተጉ እና አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች፣ ድሆች እና ራሳቸውን መከላከል ለማይችሉ ሰዎች ሁሉ ችግሮች እና ፍላጎቶች ተጨባጭ ምላሽ እንዲሰጡ አበረታታለሁ" ብለዋል። "የእኛ ቁርጠኝነት "ከወንድሞች እና እህቶች ሁሉ ጋር" ጎን ለጎን መሄድ ነው፣ ውጤታማ ሰላም እና ፍትህ የምናመጣ ጠቢባን፣ ልዩነቶችን ተስማምተን የእያንዳንዱን ማንነት በማክበር መፍታት ይኖርብናል" ብለዋል።

04 February 2022, 12:20