ከፊንላንድ የመጡ የክርስቲያኖች አንድነት ልኡካን ቡድን ከፊንላንድ የመጡ የክርስቲያኖች አንድነት ልኡካን ቡድን 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “የእግዚአብሔር ብርሃን የልዩነት ጨለማን ያስወግዳል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ጥር 9/2014 ዓ. ም. ከፊንላንድ የመጡ የክርስቲያኖች አንድነት ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለዋቸውል። በየዓመት ጥር 10 ቀን የሚጀምር የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ከጀመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት ወደ ሮም የመጡትን የፊንላንድ ክርስቲያኖች አንድነት ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለው ባስተላለፉት መልዕክት፣ እግዚአብሔርን ለማግኘት የምናደርገው ፍለጋ የሚጀምረው ሰብዓ ሰገል ካደረጉት የሕብረት ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰብአ ሰገልን በጉዞአቸው የመራው ኮከብ ዛሬም ክርስቲያኖችን ወደ እግዚአብሔር እንደሚመራቸው ገልጸው፣ ከፍተኛ ጥረቶች በመደረግ ላይ ባሉበት በሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች በኅብረት ለመሰብሰብ እና ለመተባበር በመቻላቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን ሀሳባቸውን የገለጹት የፊንላንድ ልዑካን ቡድንን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ወቅት መሆኑ ታውቋል። የፊንላንድ ልዑካን ቡድኑ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ከጀመጀመሩ ከአንድ ቀን በሮም የተገኙት የአገራቸው የመጀመሪያ ጳጳስ እና ሰማዕት፣ የቅዱስ ሄንሪክ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት መሆኑ ታውቋል። በየዓመቱ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት የዘንድሮ ጭብጥ “ኮከቡን በምስራቅ አይተን ልንሰግድለት መጣን” የሚል መሆኑ የር. ሊ. ጳጳሳት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በኅብረት የሚደረግ ጉዞ

ወደ ፊት መራመድ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋገመው በንግግራቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ሰብአ ሰገሉ ኮከቡን ተከትለው በመጓዝ ኢየሱስን ማግኘት እንደቻሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ “እግዚአብሔር ‘ምልክቱን’ ያሳያቸው እርሱን የፈለጉት የመጀመሪያዎቹ በመሆናቸው ነው” ብለዋል። “ሕይወትን በዚህ መንገድ መረዳት ምንኛ ያማረ ነው!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የምርምር ጉዞ የተጀመረው በእኛ ሳይሆን አስቀድሞ እኛን መፈለግ ከጀመረው እና በጸጋው ከሳበን ከእግዚአብሔር በኋላ መሆኑን አስረድተዋል። ሁሉም ነገር የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ገልጸው፣ “የእኛ ምላሽ እንደ ሰብአ ሰገል በአንድነት መጓዝ ነው” ብለዋል።

በወንድማማችነት መካከል የሚያበራ ብርሃን

የሰብዓ ሰግልን ትውፊት በመከተል የኅብረት ጉዞን በማድረግ ላይ የሚገኘውን የክርስቲያኖች ኅብረት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የአብያተ ክርስቲያናቱ የጋራ ጉዞ የተለያዩ ባህሎችን እና ህዝቦችን የሚወክል መሆኑን አረጋግጠዋል። በተለይ በዚህ ዘመን ጥረታችን ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን አብሮ መጓዝ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። “የመለያየት ጨለማን ገፍፎ ወደ አንድነት በሚወስደን በእግዚአብሔር ብርሃን እየተመራን እንገኛለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ “በወንድማማችነት መንፈስ በዚህ የጋራ መንገድ ላይ እንገኝለን” ብለዋል።

የእግዚአብሔር ፈላጊዎች ነን

በኅብረት ሲኮን “በፍጥነት እና በትጋት” መጓዝ ይቻላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በድሆች እና ዕርዳታ ፈላጊዎች ዘንድ የሚገኙ፣ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ እና አንድ እንድንሆን የሚያደርገን የበጎ አድራጎት መንገድ ብዙ መሆናቸውን አስረድተዋል። ድካም እና ተስፋ መቁረጥ ሊኖር እንደሚች የገለጹት ቅዱስነታቸው "ሩቅ እና ለመድረስ አስቸጋሪ የሚመስሉ ግቦች" ቢኖሩም የማያቋርጡ ጥረቶችን በማድረግ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ገልጸዋል።

ወደ ኢየሱስ መቅረብ

አንድ ላይ ለመራመድ ሁለት አስፈላጊ ደረጃዎች መከበር አለባቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እ. አ. አ በ2025 ዓ. ም. የሚከበረው 1700 ኛ ዓመት የኒቂያ ጉባኤ ክብረ በዓል እና "የዚህ ጉባኤ አካል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ መሆኑን የሚመሰክር፣ የከተጠመቁት ሁሉ ጋር አንድ የሚያደርግ የሥላሴ ምስጢር መሆኑን አስረድተዋል። ስለዚህም "በክርስቶስ መንገድ እና ራሱም ክርስቶስ በሆነው አብረን እንድንመላለስ ምኞታችንን እና ፍላጎታችን ማደስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሁለተኛው ደረጃ እ. አ. አ. በ2030 ዓ. ም. 500ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው የአውግስበርግ ጉባኤን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አንድነታቸውን ለማስጠበቅ ክርስትያኖች የተለያዩ መንገዶችን ሲከተሉ እንደ ነበር አስታውሰዋል። በወቅቱ መከፋፈልን ማስቀረት እንዳልተቻለ እናውቃለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እ. አ. አ. በ2030 ዓ. ም. የሚከበረው 500ኛ ዓመት ክብረ በዓል፣ በኅብረት መንገድ ላይ መራመዳችንን ለማረጋገጥ እና ለማጠናከር፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ የበለጠ ታዛዦች እንድንሆን እና በሰዎች አመክንዮ ላይ ቆመን መንገዱን ወደፊት ለማስቀጠል የበለጠ ፈቃደኛ ለመሆን የሚያስችል ፍሬያማ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ህልም ያለው ጠንካራ ሐዋርያዊ እረኛ

ወደ አንድነት የሚደረገው ጉዞ በነገረ መለኮት ምሁራን ጥናት የታጀበ ቢሆንም "በጸሎት፣ በበጎ አድራጎት ሥራ እና በጋራ ጥረት" ጭምር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ በተጨማሪም ከአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎችን ጋር የተደረጉ ሥራዎችን እና ሕልሞች ፈጽሞ መርሳት እንደማይገባ አስታውሰዋል። ሐዋርያዊ እረኛ ከምዕመናኑ ጋር ተጨባጭ የሆነ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል ብለው፣ ከዚህም በላይ ሕልሙን ማቆም እንደሌለበት ይታየኛል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከፊንላንድ ለመጡት የክርስቲያኖች አንድነት ልኡካን ያደረጉትን ንግግር ከማጠቃለላቸው በፊት እያንዳንዱ ልኡክ በራሱ ቋንቋ “አባታችን ሆይ!” ጸሎት እንዲያቀርብ ከጋበዙ በኋላ ከልኡካን ቡድኑ ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል።

17 January 2022, 16:34