'Click To Pray' የተባለ አዲስ የጸሎት መተግበሪያ የሲኖዶሱን ሂደት የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በጸሎት ለመተባበር እና ሲኖዶሳዊ ጉዞን በጸሎት ለመጓዝ የሚረዳ አዲስ ስሪት የጸሎት መተግበሪያ ጥቅምት 9/2014 ዓ. ም. ይፋ መሆኑ ታውቋል። መተግበሪያውን ያስተዋወቀው የቅዱስነታቸው ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"Click To Pray" 2.0 በሚል መጠሪያ የሚታወቅ በመተግበሪያን በስልኮቻን በነጻ በመጫን መጠቀም የሚቻል ሲሆን፣ መተግበሪያው በየቀኑ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር አብረው ለመጸለይ እና የሲኖዶሱን ሂደት የሚደግፉ ልዩ ልዩ ሃሳቦችን ለማግኘት የሚያግዝ መሆኑ ታውቋል። መተግበሪያውን ማክሰኞ ጥቅምት 9/2014 ዓ. ም. በጋራ ይፋ ያደረጉት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና

ዓለም አቀፍ የገዳማት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት መሆናቸው ታውቋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ፣ “የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ዋና መሠረት ጸሎት ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማስገንዘባቸውን ገልጸው፣ “Click to Pray” የሚለው አዲስ መተግበሪያ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በጸሎት እንዲገንኙ ከማገዝ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ዲጂታል የጸሎት ማህበረሰብን ለመገንባት ዕቅድ ያለው መሆኑ ታውቋል።

በቅድስት መንበር የማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሞንሲኞር ሉቾ ሩዊዝ በመልዕክታቸው፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስተማረን ትምህርቶች መካከል አንዱ “ዲጂታል ባሕል ብዙ የሚያበረክትልን ጥቅም” መሆኑን ገልጸው፣ ዲጂታል መገናኛዎች በመልክዓ-ምድራዊ አቀማመጣቸው እጅግ ርቀው በሚገኙ አከባቢዎች የሚኖርትን በሚገኙበት የትኛውም ቦታ ለመድረስ አቅም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ተከታይ ብዛት በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል። “Click to Pray” የሚል አዲስ የጸሎት መተግበሪያ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ የሆኑት ቤቲና ራይድ በበኩላቸው፣ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ካሁን ጀምሮ የራሳቸውን የጸሎት ጊዜ በመመደብ፣ ለእያንዳንዱ ቀን የጸሎት ዕቅድ ማውጣት የሚችሉ መሆኑን አብራርተዋል። መተግበሪያውን ላልተላመዱት ሁሉ በቀኑ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ማሳወቂያዎችን በመላክ ሰፊ የይዘት ምርጫን የመቀበል አማራጭን በማሳየት፣ ሰዎች በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓላማዎች ሙሉ ተነሳሽነትን በመግለጽ፣ ሰብአዊ ቤተሰብን ለሚጋፈጡ ተግዳሮቶች እና ለቤተክርስቲያን ተልዕኮ ፍሬያማነት እንዲጸልዩ የሚያስታውስ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰባት ቋንቋዎችን መጠቀም የሚያስችል "Click To Pray" መተግበሪያው፣ እያንዳንዱ ተጠቃሚ የጸሎት ሃሳቦችን በአውታረ-መረብ ላይ በመግለጽ ከሌሎች ጋር መጋራት የሚችልበትን የጋራ መድረክ ለመስጠት እና በተጠቃሚዎች መካከል መስተጋብርን በማስተዋወቅ ትውልዶች መገናኘት የሚችሉበትን ድልድይ ለማቅረብ ያለመ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም ጸሎትን በጥልቅ ደረጃ ለመለማመድ የሚያግዝ የመማሪያ መሣሪያንም ያካተተ ሲሆን፣ "Click To Pray" የተሰኘ የጸሎት መተግበሪያን እስከ ዛሬ ከ 2.5 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች በሁሉም አህጉራት የሚጠቀሙት ሲሆን፣ ይህም ከ 400,000 በላይ ተጠቃሚዎች ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር እንዲጸልዩ አስችሎአቸዋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በበኩላቸው፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በማቅረብ ላይ ባለው መንፈሳዊ አገልግሎት እርስ በእርስ እንድንገናኝ፣ አንዳችን ሌላውን ከልብ እንድናዳምጥ እና መንፈስ ቅዱስ የሚናገረንን በማስተዋል እንድናስተነትንበት የሚጋብዘን መሆኑን ገልጸዋል። የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት በጸሎት የታገዘ፣ ዘላቂነት ያለውን የግል እና የማህበረሰባዊ መለወጥን ይጠይቃል ብለው፣ ከጸጥታ እና ከማሰላሰል የሚመነጨው ጸሎታችን ለመላው ቤተክርስቲያን ትልቅ እገዛ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

20 October 2021, 16:57