“ፍራንችስኮስ” የሚል ዘጋቢ ፊልም በታየበት ዕለት “ፍራንችስኮስ” የሚል ዘጋቢ ፊልም በታየበት ዕለት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለተፈናቃዮች እና ለስደተኞች ያላቸውን ርኅራሄ በተግባር ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጳጉሜ 1/2013 ዓ. ም በጳውሎስ 6ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተገኝተው፣ ወደ መቶ ከሚጠጉ ተጋባዥ እንግዶች ጋር በመሆን፣ “ፍራንችስኮስ” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ አንድ ዘጋቢ ፊልም ተመልክተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአዳራሹ ውስጥ የተገኙት ተጋባዥ እንግዶቹ መጠለያ የሌላቸው ጥገኛ ቤተሰቦች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል በቅርቡ ከአፍጋኒስታን ካቡል ከተማ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች መገኘታቸው ታውቋል። ዝግጅቱን ያስተባበረው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ፋውንዴሽን ሲሆን፣ የዘጋቢ ፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ኤቨጀኒ አፊኒቪስኪ ለእንግዶች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበዋል። ቀጥለውም የግል ሕይወታቸውን በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፣ ከሩሲያዊ ወላጆቻቸው ጋር ወደ እስራኤል ከተሰደዱ በኋላ ወደ አሜሪካ በመሄድ ኑሮአቸውን እዛው መጀመራቸውን አብራርተዋል።

የተመልካቾችን ልብ በጥልቅ ስሜት ውስጥ ያስገባው “ፍራንችስኮስ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልሙ፣ ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ የጦርነት ሰለባ በሆኑ ሰዎች ላይ የደረሰውን መከራ እና ስቃይ የሚተርክ መሆኑ ታውቋል። ዘጋቢ ፊልሙ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት መኖሪያ ቤታቸውን እና ትውልድ አካባቢያቸው ለቅቀው ለመከራ ሕይወት የሚዳረጉትን ለመደገፍ የሚያደርጉት የግል ጥረት የሚያስገነዝብ በፊልሙ ፍጻሜ በአዳራሹ ውስጥ የተገኙት ስደተኛ ቤተሰቦች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በስደት እና በአመጽ ለመከራ ሕይወት የተዳረጉ በርካታ ቤተሰቦች በዘጋቢ ፊልሙ አማካይነት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቀረበውን የማበረታቻ ተግባራትን ተመልክተው ብርታትን ማግኘታቸው ተመልክቷ።

ልብ የሚሰብር ስሜት የታየበት ዘጋቢ ፊልም ለመመልከት በቅርቡ በአፍጋኒስታን ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት እና የእርስ በእርስ አመጽ ምክንያት የተፈናቀሉ ሃያ ስደተኞች መገኘታቸው ታውቋል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ በመግለጫቸው፣ በአፍጋኒስታን በተቀሰቀሰው ጦርነት እና አመጽ ምክንያት ለተፈናቀሉት ቤተሰቦች ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የፍቅር እና የማፅናኛ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል። የአፍጋኒስታን ስደተኞች ወደ ጣልያን እንዲገቡ መንገድ ያመቻቸው፣ ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሮም ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ መሆኑ ታውቋል።

በቅርቡ ወደ ጣልያን ለመድረስ ከቻሉት የአፍጋኒስታን ከስደተኞች መካከል አንዱ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጠው የምስክርነት ቃል፣ የአፍጋኒስታን ተፈናቃዮች ድምጽ ተደማጭነትን ማግኘቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጾ፣ በተለይም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተሰሚነትን ማግኘቱ አስፈላጊ እንደሆነ እና በአዳራሹ ውስጥ ከተፈናቃይ ቤተሰብ ጋር መሆናቸው፣ ወደፊት የሚደርስባቸውን ችግሮችን ለመጋፈጥ ብርታትን የሰጠ መሆኑን አስረድቷል።

በጳውሎስ 6ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ከተከናወነው እና ታላቅ ርህራሄ ከታየበት የበዓል ድባብ ቀጥሎ በአዳራሹ የተገኙ ተፈናቃዮች፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንቸስኮን በማጀብ ወደ ቅድስት ማርታ መኖሪያ ቤታቸው የሸኟቸው መሆኑ ተመልክቷል።

07 September 2021, 16:46