ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ልባችንን ወደ ቅዱስ መስቀል መመለስ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በስሎቫኪያ ፕሪሶቭ ከተማ ተገኝተው በምስራቅ ቤተክርስቲያ አምልኮ ሥርዓት የተፈጸመውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተካፍለዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ለተገኙት የስሎቫኪያ ምዕመናን ባቀረቡት ስብከት፣ ልባቸውን በመስቀላ ላይ ወደ ተሰቀለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመልሱ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት መስከረም 4/2014 ዓ. ም በፕሬሶቭ ከተማ የሕይወት ሰጪ ቅዱስ መስቀል ዓመታዊ በዓል የተከበረ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥፍራው በመገኘት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎቱ መርተዋል። በምስራቅ ቤተክርስቲያ የአምልኮ ሥርዓት የተፈጸመውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የከተማዋ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃን ባባክ ከሌሎች የግሪክ እና የላቲን የአምልኮ ሥርዓቶችን ከሚከተሉ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ሆነው ማቅረባቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ስብከት፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ፣ በምዕ. 1:23 ላይ “እኛ ግን ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ መሰቀሉን እንመሰክራለን፤ ይህም ምስክርነት ለአይሁዳዊያን መሰናከያ ነው፤ ለግሪካዊያንም ሞኝነት ነው” የሚለውን ጥቅስ በመድገም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የእግዚአብሔር ታላቅ ኃይል እና ጥበብ የተገለጠበት መሆኑን አስረድተዋል። መስቀል የሰዎች ውርደት እና ስንፍና የሚገለጥበት መስሎ ቢታየንም ለእኛ ለምናምን ግን የእግዚአብሔር እውነተኛ ፍቅር የተገለጠበት መሆኑን ገልጸዋል። “መስቀል የሞት መሣሪያ ቢሆንም ዘለዓለማዊ ሕይወት የተገኘበት ነው” ብለውዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት የቀረበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ከጻፈው የተወሰደ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር የነበረ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ በቅርብ ሆኖ የተመለከተ እና የመሰከረ ሐዋርያ መሆኑን ተናግረዋል።

መመልከት

ሐዋርያው ዮሐንስ በመስቀል ሥር ሆኖ ለሞት ተላልፎ የተሰጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልክቶታል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በዓለማዊ ዓይን ስንመለከተው መስቀል ውድቀትን እና ሽንፈትን የሚያመላክት ነው ብለዋል። የመስቀልን ትርጉም እና መልዕክት ሳንረዳ በዓይን ብቻ ልንመለከተው እንችላለን፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስን የርኅራሄ ፍቅር ምስጢር ልንዘነጋ እንችላለን ብለው፣ መስቀል የሌለው ክርስትና የቃል ብቻ እንጂ ፍሬን የሚያስገኝ አይደለም” ብለዋል። እግዚአብሔር አምላክ በሰዎች የስቃይ ታሪክ ውስጥ ለመግባት በመስቀል ላይ መሰቀሉን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በትክክል መመልከቱን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ መስቀል የሚያሳየን ማንም ሰው ተስፋ አስቆራጭ በሆነ መከራ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ የሚያመለክት ነው ብለው፣ በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስ በመመልከት ፣ ልባችንን ለእርሱ በመክፈት ከመስቀል የሚገኘውን ጸጋ ማየት መማር አለብን ብለዋል።

ምስክርነት መስጠት

በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማሰብ ማስተንተን፣ ምስክሮቹ እንድሆን ያደርገናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህን ካደረግን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት እንችላለን ብለዋል። የእርሱ ገጽታዎች የእኛ በመሆን በፍቅሩ አሸንፎን እንድንለወጥ ያደርገናል ብለዋል። የቅርብ ዘመን ሰማዕታትን በተለይም የስሎቫኪያ ሰማዕታትን አስታውሰው ስብከታቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሰሎቫኪያ ሰማዕታት ሰማዕትነታቸውን የገለጹት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው ፍቅር ላይ ለረጅም ጊዜ በማስተንተን እንደሆነ እና ይህን በተግባር ለመግለጽ በሞታቸው እርሱን መስለው መገኘታቸውን አስታውሰዋል። ምስክርነታችንም በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚገልጽ ሊሆን ይገባል ብለዋል። መስቀሉን በልቡ ውስጥ የሚሸከም ማንም፣ ሰውን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም እና እንደ እህት የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል። ለመስቀል የሚቀርብ ምስክርነት የሚገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየው ትሁት ፍቅር አማካይነት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስሎቫኪያ ምእመናን ባቀረቡት ስብከት፣ በሕይወት ዘመናቸው ያዩዋቸውን ምስክርነቶች እንዲያስታውሱ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ቢሆን በመስቀል ላይ ሆኖ ምስክሮቹ እንድንሆን ይጠይቀናል” ብለዋል።                       

15 September 2021, 17:20