ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ኢየሱስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” በማለት ይጠይቀናል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ከነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. እስከ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ድረስ ሲካሄድ የቆየው 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን አሳርገዋል። በቡዳፔስት ከተማ የተካሄደው ዓለም አቀፉ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓቱ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖችን አንድነት የሚገልጽ እና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዕድ ዙሪያ የሚያቀርብ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መሆኑ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በላቲን የምልኮ ሥርዓት መሠረት እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም በተነበበው የማር. 8.27-35 በተጻፈው ላይ በማስተንተን ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በ52ኛው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባቀረቡት ስብከት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” በማለት ያቀረበላቸውን ጥያቄ አስታውሰው፣ በእርግጥ ጥያቄው ፈጣን መልስ የሚጠይቅ ሳይሆን “ወሳኝ የግል ምላሽን የሚፈልግ” ነው ብለዋል። ለኢየሱስ ክርስቶስ የምንሰጠው ምላሽ እንደ ደቀ መዛሙርቱ ለአገልግሎት የሚያዘጋጀን እና ሦስት ደረጃዎች ያሉት መሆኑን ገልጸው፣ እነርሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማስተዋል መጓዝ እና ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት

የመጀመሪያው ደረጃ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት፣ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ አዳኝ አድርጎ ከመቀበል በላይ፣ የትንሳኤውን ክብር ብቻ ሳይሆን የመስቀል ላይ ስቃዩንም መመስከር ወይም ማወጅን ያካትታል ብለዋል። “እንደ ደቀ መዛሙርት እኛ የምንመርጠው በመስቀል ላይ ከተሰቀለው አገልጋይ ይልቅ ኃያል መሲሕን ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ደህንነት ሲል ሞትን መምረጡን       ቅዱስ ቁርባን ያስታውሰናል ብለው፣ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበውን ጥያቄ ማስታወስ መልካም ነው” ብለዋል።

ከኢየሱስ ጋር በመሆን በማስተዋል መጓዝ

ለኢየሱስ ክርስቶስ የምንሰጠው ሁለተኛው ምላሽ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማስተዋል መጓዝ እንደሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ወቅት እራሱን እንዳገለለው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ እኛም ኢየሱስን ከልባችን ውስጥ ወደ ጎን በማድረግ፣ የራሳችንን መንገድ ብቻ መጓዝ እንመርጥ ይሆናል” ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም ከምናዘነብል ይልቅ የእርሱን መንገድ እንድንከተል ይፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም፣ በቅዱስ ቁርባን ፊት የምንበረከክበት የጸሎት እና የውዳሴ ጊዜ ሊኖረን እንደሚገባ አሳስበው፣ በራሳችን ከምንመካ ይልቅ በእግዚአብሔር እንድንመካ፣ ልባችንን ከፍተን ራሳችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ያስፈልጋል በማለት ብርታትን ተመኝተዋል።

ኢየሱስን መከተል

በማር. 8:33 ላይ ኢየሱስ ጴጥሮስን “አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ!” በማለት ጴጥሮስ ወደ እርሱ ተመልሶ እንዲከተለው ማድረጉን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ከኢየሱስ ኋላ መሄድ ማለት፣ የእግዚአብሔር ተወዳጅ ልጆች በመሆናችን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በመተማመን ሕይወትን መጓዝ እንደሆነ፣ ሊገለገል ሳይሆን ሊያገለግል የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል መሆኑን አስረድተዋ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ዘወትር በማገልገል ደስታን ለራሳችን እና ለሌሎች ለማምጣት ተጠርተናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ ላይ ያቀረቡትን ስብከት ሲያጠቃልሉ “ይህ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ አንድ ጉዞን ፈጽመን፣ ሌላውን ጉዞ መጀመር እንዳለብን ያሳስበናል” ብለው፣ ከኢየሱስ ኋላ መሄድ ማለት፣ ሁል ጊዜ ወደ ፊት መጓዝን እንደሚያሳስብ፣ ጸጋን መቀበል እንዳለብን የሚያሳስብ እና ኢየሱስ “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበላቸውን ጥያቄ እኛም ወደ ራሳችን ተመልሰን በጥያቄው ላይ እንድናስተነትን የሚጋብዘን መሆኑን አስርድተዋል።            

13 September 2021, 12:00