ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የልብ ፈውስ የሚጀምረው ከማዳመጥ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማቅረባቸው ተመልክቷል። በላቲን የአምልኮ ሥርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት ከማር. ምዕ. 7: 31-37 ተወስዶ በተነበበው በዕለቱ ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው፣ የልብ ፈውስ የሚጀምረው ከማዳመጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻችን፣ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነሐሴ 30/2013 ዓ. ም በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተነተን ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ትርጉም  እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ ደንቆሮ እና ዲዳ የነበረው ሰው በኢየሱስ መፈወሱን ይተርክልናል። በዚህ ታሪክ ውስጥ በጣም የሚያስደንቀው ኢየሱስ ይህን አስገራሚ ምልክት እንዴት እንደሚያከናውን ነው። አንድ መስማት የተሳነውን ሰው ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደ እና ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አገባ፤ ምራቁንም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና ሰውየውን “ኤፋታህ” አለው፤ ፍቺውም “ተከፈት” ማለት ነው (ማር. 7:33-34)። በሌሎች የፈውስ አገልግሎቱ፣ እንደ ሽባ ወይም ለምጽ የመሰሉ ከባድ የአካል ጉዳቶችን እንደዚህ ብዙ ነገሮችን አላደረገም ነበር። እጁን ብቻ በሰውየው ላይ እንዲጭን በተጠየቀ ጊዜ፣ ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ ማስገባት፤ ምራቁንም እንትፍ ማለት፣ ወደ ሰማይም አሻቅቦ ማየት እና ማቃተት፣ ይህን ሁሉ ለምን አደረገ? (ቁ. 32) ምናልባት የዚያ ሰው ሁኔታ የተለየ ምሳሌያዊ እሴት ስላለው ሊሆን ይችላል። መስማት ያለመቻል ወይም ደንቆሮ የመሆን ሁኔታ ለሁላችንም አንድ ምልክት ሊነግረን ይችላል። ለመሆኑ ደንቆሮነት ምንድነው? ያ ሰው መናገር ያልቻለው መስማት ስላልቻለ ነው። ኢየሱስ ሰውየውን ከሕመሙ ለመፈወስ ፣ በመጀመሪያ ጣቶቹን በሰውየው ጆሮ ፣ ከዚያም በኋላ በአፉ ላይ አደረገ። መጀመሪያ ግን በጆሮዎቹ ላይ አደረገ።

እኛ ሁላችንም ጆሮ አለን። ነገር ግን ብዙን ጊዜ ለማዳመጥ ዝግጁዎች አይደለንም። ይህ ለምን ይመስላችኋል? ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ኢየሱስ በእጆቹ ዳስሶ እንዲፈውሰን መጠየቅ ያለብ የውስጥ ደንቆሮነት አለብን። ደግሞ ከሁሉም የሚብሰው የውስጥ ደንቆሮነት ነው። ምክንያቱም የልብ ደንቆሮነት ነውና። ብዙ ነገሮችን ለመናገር እና ለማድረግ እንቸኩላለን እንጂ ቆም ብለን ሌሎች የሚናገሩትን ለማዳመጥ ጊዜ አናገኝም። በችግሮች ላለመበገር ጥረት በምናደርግበት ጊዜ አንዳንድ እኛ እንድናዳምጣቸው ለሚፈልጉ ሰዎች ቦታን ያለመስጠት አደጋ ውስጥ እንወድቃለን። ይህን በምልበት ጊዜ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን እና አረጋዊያንን አስባለሁ። ከእኛ የሚወጣውን ቃል ሳይሆን እነርሱ የሚናገሩትን እንድናዳምጣቸው የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ሌሎችን የማድመጥ ችሎታዬ ምን ያህል ነው? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። የሌሎች ሕይወት ግድ ይለኛል ወይ? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ጊዜዬን ከሚቀርቡኝ ሰዎች ጋር እንዴት ማሳለፍ እንደሚቻል አውቃለሁ? ይህ ጥያቄ ሁላችንን የሚመለከት ቢሆንም በተለይ ካኅናትን ይበልጥ ይመለከታል። ካኅን ለሕዝቡ ወይም ለምዕመናኑ ጊዜን በመስጠት እንዴት መርዳት እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋን። ነገር ግን መጀመሪያ ማዳመጥ ይኖርበታል። ሁላችንም ብንሆን፣ መጀመሪያ ማዳመጥ፣ ከዚያ በኋላ መልስ መስጠት ይኖርብናል። የቤተሰብን ሕይወት ለምሳሌ እንውሰድ፤ ሳናዳምጥ ደጋግመን የምንናገራችው ስንት ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ? ይህ ሊከሰት የሚችለው በቅድሚያ ማድመጥ ካለመቻላችን እና ሌላው ተናግሮ እንዲጨርስ፣ ሃሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ካለመስጠታችን የተነሳ ነው። ውይይት የሚጀመረው ጸጥታ ሲሰፍን እንጂ በጫጫታ ወይም በጭቅጭቅ መካከል አይደለም። ሊነግሩን በልባቸው ውስጥ ያለውን ጉዳይ በትዕግስት ማዳመጥ ስንጀምር ነው።

የልብ መፈወስ የሚጀምረው፣ የሚታደሰውም ከማዳመጥ ነው። ተመሳሳይ ነገሮችን በመደጋገም የሚያሰለቹን ሰዎች ይኖራሉ። ቢሆንም የሚናገሩትን ነገር በሙሉ ማድመጥ፣ ተናግረው ሲጨረሱ መናገር መልካም ነው። ከኢየሱስ ጋርም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ለእርሱ ብዙ ጥያቄዎችን ማቅረብ ጥሩ ነው። ነገር ግን አስቀድመን እርሱ በቅዱስ ቃሉ የሚነግረንን ማድመጥ ያስፈልጋል። ኢየሱስም የሚፈልገው ይህን ነው። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የሙሴ ሕግ መምህር ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ከሁሉ የሚበልጠው ትዕዛዝ የቱ ነው?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ፣ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት። “ከሁሉ የሚበልጠው ትዕዛዝ ‘እሥራኤል ሆይ ስማኝ!’ ብሎ ይጀምርና፥ ‘እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም አሳብህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደድ’ የሚል ነው። ይህንንም የሚመስል ሁለተኛው ትዕዛዝ ‘ሰውን ሁሉ እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ’ የሚል ነው” በማለት መለሰለት። እኛስ እግዚአብሔርን ማዳመጥ እንዳለብን እናስታውሳለን? ክርስቲያኖች ነን፤ በየቀኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቃላትን እንሰማለን። ነገር ግን ጥቂት የወንጌል ቃላት በልባችን ውስጥ ገብተው የሚገለጹበትን ጊዜ አናገኝም። ኢየሱስ እራሱ እውነተኛ ቃል ነው። ልናዳምጠው ጊዜን የማንሰጥ ከሆነ፣ እርሱ አልፎን ይሄዳል። ቅዱስ አጎስጢኖስም “ኢየሱስ ሳያስተውለኝ አልፎኝ እንዳይሄድ እሰጋለሁ” ይል ነበር። ፍርሃቱም ኢየሱስን ሳይሰማው እንዳይሄድበት ነበር። ቅዱስ ወንጌል ለመስማት ጊዜን የምንሰጥ ከሆነ መንፈሳዊ ጤንነታችን ለመንከባከብ ዕድል እናገኛለን። በየቀኑ ጥቂት የጸጥታ ጊዜን በማግኘት፣ የማይጠቅሙ ንግግሮችን ከመስማት ይልቅ ከእግዚአብሔር ቃል በብዛት ብንሰማ መድኃኒት ይሆነናል። ቅዱስ ወንጌልን ሁል ጊዜ በኪስ መያዝ ብዙ ሊጠቅማችሁ ይችላል። እንደ ጥምቀት ቀናችን፣ “ኤፋታህ” ወይም “ተከፈት” የሚለውን የኢየሱስ ቃል ዛሬም እንሰማለን። ጆሮአችሁን ክፈቱ። ኢየሱስ ሆይ! እራሴን ለቃሎችህ ክፍት አደርጋለሁ፤ ልቤን ከመዘጋት አድን፣ ልቤን ከችኮላ ፈውስ፣ ትዕግሥትንም ስጠው። 

በውስጧ ሥጋ ሆኖ የተገለጠውን ቃል ለመስማት እራሷን ክፍት አድርጋ የተገኘች ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ልጇን ኢየሱስን በቅዱስ ወንጌሉ በኩል በየቀኑ መስማት እንድንችል፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በቅን ልብ፣ በታጋሽ ልብ፣ በትዕግሥት ማድመጥ የምንችልነት ጸጋ በመስጠት እንድታግዘን እንለምናታለን።”     

06 September 2021, 15:38