ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ ምዕመናንን ሲጨብጡ    ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ ምዕመናንን ሲጨብጡ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ሃላፊነትን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ውስጥ ሪሚኒ ከተማ “በሕዝቦች መካከል ወዳጅነትን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 14-19/2013 ዓ. ም. ድረስ ስብሰባቸውን ለሚያካሂዱት አባላት በላኩት መልዕክት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተገታ በኋላ መልካም ለውጥን ለማምጣት እያንዳንዱ ግለሰብ ሃላፊነት መውሰዱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ከወረርሽኙ በኋላ ሕዝቦች ሕይወትን በአዲስ መልክ ለመጀመር በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመሩ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን መልዕክት ለስብሰባው ተካፋዮች የላኩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መሆናቸው ታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ያለፈው ዓመት በበይነ መረብ ያካሄዱትን ስብሰባ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኝተው ለማካሄድ በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደሰታ ገልጸዋል።

“እኔ” ለማለት ድፍረት ማግኘት የሚለውን የዴንማርክ ፈላስፋ፣ ሶሬን ኪርከጋርድ አባባል በማስታወስ ዘንድሮ ለ42ኛ ጊዜ ለሚካሄድ ስብሰባ ቅዱስነታቸው በላኩት መልዕክት፣ የፈላስፋው ንግግር ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው፣ ኮቪድ-19 የሰጠንን ዕድል በመጠቀም በዲስ መልክ ጉዞን በትክክለኛው መንገድ መጀመር ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም እያንዳንዱ ግለሰብ በነጻነት የሚጀምረው ጉዞ ሃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። ወረርሽኙ ማኅበራዊ ርቀትን እንድንጠብቅ ከማስገደዱ በተጨማሪ “እኔ” ለሚለው አስተሳሰብ ቅድሚያን በመስጠት መሠረታዊ የሆነውን እና ለረጅም ዘመናት ሳናውቀው የቆየነውን የመኖር ትርጉም እንድንረዳ አድርጎናል ብለዋል።

ሰው የኅብረተሰብ መሠረት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሃላፊነትን እንድናውቅ አግዞናል ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ለዚህም በርካታ ሰዎች ምስክርነታቸውን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስታውሰዋል። ወረርሽኙ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት በበሽታ፣ በሕመም፣ በአስቸኳይ ዕርዳታ ጥያቄ ብዙ ሰዎች ድምጻቸውን ማሰማት መቻላቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። አክለውም የሰው ልጅ የማኅበረሰብ መሠረት መሆኑን ገልጸው፣ ለሰዎች ቅድሚያን የማይሰጥ ማኅበረሰብ፣ ሕይወት ያለው የራስ ወዳዶች ስብስብ ብቻ ነው ብለዋል።

ሃላፊነት እንጂ ራስ ወዳድነት አያስፈልግም

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲያከትም ሁሉም ሰው ሃላፊነትን በመውሰድ ሌሎችን ማገልገል በተለይም ከመንግሥት መሪዎች እና ባለሥልጣናት ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ ግለሰብ ከራስ ወዳድነት ወጥቶ ተስፋን የሚሰጥ ሃላፊነት እንዲወስድ አደራ ብለዋል።

በክርስቶስ ድፍረትን ማግኘት

“እኔ” በማለት ሃላፊነትን ለመውሰድ ድፍረት ሊኖር ይግባል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ማለት የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታገዝ እውነተኛ የሕይወት አቅጣጫን ስናገኝ ነው ብለዋል። አክለውም በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር አባታዊነት ማግኘት የሚቻለው ፍርሃትን አስወግደን በአዎንታዊ አመለካከት ራሳችንን ለዓለም ክፍት ስናደርግ ነው ብለዋል። ድፍረት የሚገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ መመኪያችን እና ደህንነታችን፣ በመከራ እና ስቃይ ጊዜ ሰላምን የሚሰጥ፣ ሞትን ድል ያደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለዋል።

ከወንጌል የሚገኝ ደስታ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “በሕዝቦች መካከል ወዳጅነትን ማሳደግ”  በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 14-19/2013 ዓ. ም. ድረስ ስብሰባቸውን ለሚያካሂዱት አባላት የላኩትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ ስብሰባቸው ከወንጌል በሚገኝ ደስታ የተሞላ እንዲሆን፣ እምነትን ከሌሎች ጋር በኅብረት ለመኖር የሚያበቃ አዲስ ድፍረት እንዲያገኙ ተመኝተው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ላለ እምነት እንደ አድማስ የሚገለጠው መላው ዓለም ነው በማለት አስረድተዋል።         

19 August 2021, 16:21