ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ "ቤተክርስቲያንን የሚያድሳት የወንጌል ብርሃን ነው!"

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኩላዊት ቤተክርስቲያን የሌላውን እምነት ተከታይ ወደራሷ ለመጎትተ ሳትሞክር በወንጌል ብርሃን ብቻ በመታደስ ጉዞዋን ሳታቋርጥ መቀጠሏ ከወንጌል በምታገኘው ኃይል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ለነሐሴ ወር እንዲሆን ብለው ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፣ በጥሪ ላይ በማትኮር ቤተክርስቲያን በየጊዜው የምትሻገራቸው የፈተና እና የቀውስ ወቅቶች የሕያውነት ምልክት መሆናቸውን አስታውሰዋል። 

"የቤተክርስቲያን ጥሪ ወንጌልን መስበክ ነው፤ ይህ ማለት የሌላውን እምነት ተከታይ ወደራስ መሳብ ማለት አይደለም። ለቤተክርስቲያን የተሰጣት ጥሪ ወንጌልን መስበክ ነው። ማንነቷም የሚታወቀው ወንጌልን በመስበክ ነው።"

በመንፈስ ዕርዳታ መለወጥ

በቤተክርስቲያን ውስጥ ለውጥ የሚመጣው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለይተን በማወቅ እና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለውጥ ማሳየት ስንጀምር እንደሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ “በልባችን ውስጥ በሚገኝ የእግዚአብሔር ስጦታ አማካይነት ነው” ብለዋል። አክለውም “ይህ ለውጥ ከእኛ አልፎ ሁሉንም ነገር የሚቀይር ነው” ብለዋል።  

"የእኛ መለወጥ አስቀድሞ በተዘጋጁ ሀሳቦች ሳይሆን፣ በርዕዮተ ዓለማዊ ጭፍን አስተሳሰብ ሳይሆን፣ ነገር ግን ያለ ግትርነት ከመንፈሳዊ ተሞክሮ መጨመር ፣ ከመስጠት ተሞክሮ ፣ ከበጎ ሥራ ተሞክሮ እና ከአገልግሎት ተሞክሮ የሚገኝ መሆን አለበት።"

የሚታይ የሚጨበጥ ምስክርነት

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለነሐሴ ወር እንዲሆን ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ በግልጽ እንደተናገሩት፣ ቤተክርስቲያን የተልዕኮ ጥሪዋን በማሳደግ፣ በዛሬው ዓለም ወንጌልን መመስከር እንዲያስችላት ሁሉንም መዋቅሮቿን ማደስ መቀየር እንዳለባት ተመኝተዋል።

"ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ችግሮች ውስጥ እንደምትገኝ እናስታውስ ፤  እነዚህን ችግሮች ሁል ጊዜ ልትሻገር የቻለችው ህያው ስለሆነች ነው። ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ችግር ውስጥ መግባት የግድ ነው። ወደ ቀውስ ውስጥ የማይገቡት ሙታን ብቻ ናቸው፤ ቤተክርስቲያን በወንጌል ብርሃን እንድትታደስ የሚያደርጋት ጸጋና ኃይል ከመንፈስ ቅዱስ እንድታገኝ  እንጸልይ።"

ምቹ ጊዜን መፈለግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም ባስተላለፉት የጸሎት ሃሳብ መልዕክት በግጭት እና በቀውስ መካከል ያለውን ልዩነት መግለጻቸውን ያስታወሱት የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ የቅዱስነታቸውን መልዕክት በመጥቀስ እንደተናገሩት፣ “ለወንጌል ምስክርነት እና ለቤተክርስቲያን ተሃድሶ ምቹ ጊዜ የችግር እና የመከራ ጊዜ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በነሐሴ ወር የጸሎት ሃሳብ መልዕክታቸው፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ተሃድሶን ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት “ባረጀ ጨርቅ ላይ እንደሚለጠፍ አዲስ ጨርቅ” መታየት እንደሌለበት አሳስበው፣ “ነግር ግን አጋጣሚው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈለግ እና ለማወቅ የተገኘ ምቹ ጊዜ ነው” ብለዋል።

ከ 2016 ጀምሮ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሁሉም የቫቲካን ማኅበራዊ አውታረ መረቦች በኩል የሚያስተላልፉት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ ከ 158 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን፣ ወደ 23 ቋንቋዎች ተተርጉሞ በ 114 አገሮች ዘንድ የሚዲያ ሽፋን የተሰጠው መሆኑ ታውቋል።

05 August 2021, 16:35