ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር አውታረ መረብ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር አውታረ መረብ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር የቴክኖሎጂን ዕድገት እንዲከታተል አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ነሐሴ 21/2013 ዓ. ም በቫቲካን ለተቀበሏቸው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በማደግ ላይ የሚገኘው የዘመናችን ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ የሚሰጠው የጋራ አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዘመናችን ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ማኅበራዊ ጥቅም የሚያበረክተውን አገልግሎት ተከታትሎ ማስተዳደር ከከፍተኛ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓርብ ነሐሴ 21/2013 ዓ. ም በቫቲካን ለተቀበሏቸው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋ። እ. አ. አ በ2010 ዓ. ም የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር ዋና ዓላማ፣ በአባል አገራት ውስጥ ቅድስት መንበር የምትሰጠውን የወንጌል ምስክርነት አገልግሎት መደገፍ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ማኅበሩ በቤተክርስቲያን የተልዕኮ ምስክረነት ላበረከተው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለማኅበሩ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን እና ክትባቱን በየአገራቱ ለማከፋፈል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ወረርሽኙ ዓለምን እያስጨነቀ መሆኑን ገልጸዋል። እስካሁን በዓለማችን ውስጥ በወረርሽኙ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 200 ሚሊዮን መድረሱ እና በወረርሽኙ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር አራት ሚሊዮን መድረሱ የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በኤኮኖሚው እና በማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ይህ በሆነበት ሰዓት የሕግ አውጭዎች እና የፖለቲካ መሪዎች ሚና ከምን ጊዜም በበለጠ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር ሃላፊነት ማኅበራዊ ጥቅምን ለማሳደግ መጣር መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ማኅበሩ ኃይሉን አስተባብሮ የቆመለትን ዓላማ በማደስ ለጋራ ጥቅም በርትቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ፣ ድህነት፣ የማኅበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን፣ የሥራ እና የትምህርት ዕድል ማጣትን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ችግሮች ምክንያት ምን እንደሆነ ለይቶ በማወቅ ሕዝብን በብቃት ለማገልገል የሕግ አውጭዎች ተሳትፎ እና ሚና በጣም አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የፖለቲካ መሪነት ተሰጥኦ ያላቸውን በሙሉ አመስግነው፣ የፖለቲካ መሪዎች በተጣለባቸው ሃላፊነት የግል ጥቅምን ለማስጠበቅ ከመሥራት ይልቅ ለማኅበራዊ ዕድገት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የጋራ ጥቅምን በመወከል በፍጥነት እያደጉ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዳደር ከባድ ሥራን እንደሚጠይቅ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ዘመናዊ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂዎች የኑሮ ደረጃን ያሻሻሉ ቢሆንም ትኩረት ተሰጥቶባቸው ክትትል የማይደረግባቸው ከሆነ ሰብዓዊ ክብርን በማሳነስ የሚያደርሱት ውርደት ከፍተኛ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስርድተው፣ ስለዚህ የሕግ አውጭዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ማኅበራዊ ሃላፊነታቸውን ተረድተው፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚመሩበትን ሕግ ማውጣት እንዳለባቸ አሳስበዋል።

የቴክኖሎጂ እድገቶች መመሪያዎች

“ቴክኖሎጂዎች እንዲመሩበት የሚያቀርቧቸው አስተያየቶች፣ የቴክኖሎጂን ዕድገትን ከመገደብ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሕግ አውጭዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚመሩባቸውን ትክክለኛ ፖሊሲዎች እና መመሪያ ደንቦች በማውጣት በሰብዓዊ ክብር ላይ የሚደርሱ ወጀሎችን መከላከል የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሰውን ልጅ ክብር በማጉደፍ ከሚፈጽሟቸው ወንጀሎች መካከል ጥቂቶቹ የሕፃናት ፖርኖግራፊ፣ የግል መረጃን ያለአግባብ መጠቀም ፣ ወሳኝ በሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን መፈጸም እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት መረጃዎች መስፋፋትን ገልጸው፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ለጋራ ጥቅም እና ልማት እንዲውሉ ማድረግ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

ግብረ-ገባዊ አስተሳሰብ ሊኖር ያስፈልጋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቫቲካን ለተቀበሏቸው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የሕግ አውጪዎች ማኅበር አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሕግ ባለሞያዎቹ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እድገቶች ጋር በተያያዙ አደጋዎች ላይ ከባድ እና ጥልቅ የሞራል አቋም በመውሰድ፣ በተሰጣቸው የጥበብ ጸጋ አማካይነት ማኅበራዊ ዕድገትን እንዲያመጡ ጠይቀዋል። የአቅመ ደካማ ወንድሞች እና እህቶች ችግር በጋራ ለመካፈል ተጠርተናል ብለው፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ የተጎዳውን ዓለማችንን ከአደጋ ለማዳን እና ቀጣይነት ያለውን ሁሉ አቀፍ ማኅበርሰብ ለመገንባት፣ ሃላፊነት የሚሰማው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ የጋራ ጥቅምን መርህ ያደረጉ ብቃት ያላቸው መሪዎች ያስፈልጉናል ብለዋል።         

28 August 2021, 16:07