ከአፍጋኒስታን ስደተኞች መካከል ከአፍጋኒስታን ስደተኞች መካከል  

ጦርነትን አስወግዶ ሰላምን ማንገሥ የሚቻል መሆኑ ተነገረ

ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ በአፍጋኒስታ ውስጥ የሚታየውን የሕዝብ መፈናቀል፣ ስደት እና መከራን በመገንዘብ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዋርያዊ አስተምህሮን መሠረት ያደረገ የቤተክርስቲያን አቋም፣ የሕዝቦችን ኑሮ በማናጋት ወደ መከራ የሚዳርግ ጦርነትን በማስወገድ ወደ ሰላም ጎዳና መድረስ የሚቻል መሆኑ ተነገረ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአምስት ዓመት በፊት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ላ ክሯ “La Croix” ከተሰኘ የፈረንሳይ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የኢራቅን ሕዝብ በመምራት ላይ በሚገኝ ማዕከላዊ መንግሥት ምትክ አዲስ የምዕራባዊያን ዴሞክራሲ ሥርዓት መዘርጋቱን አስታውሰዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሊቢያም ቢሆን የአገሩ ሕዝብ የሚመራበት ባሕላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ተወግዶ አዲስ የምዕራባዊያን የአስተዳደር ሥርዓት እንዲዘረጋ መደረጉን አስታውሰው፣ የአንድ አገር ባሕል እና የአስተዳደር ሥርዓትን የሚቃወም አዲስ ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ እና ትክክል አለመሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በግልጽ እንደታየው፣ ከሃያ ዓመታት ወዲህ በአፍጋኒስታን ውስጥ ሰላምን ለማስፈን በሚል እሳቤ ጥረት ሲያደርግ የቆየው የአሜሪካ መንግሥት ያለ ውጤት መቅረቱ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ መቅረቡ ታውቋል። ጦርነት የአንድን አገር ሰላም በማወክ፣ የሕዝቦችን ሰላማዊ ሕይወት በማናጋት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን የር. ሊ. ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተምህሮች ያስረዳሉ። ቅራኔን ለማስፋፋት ከመሞከር ይልቅ ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚደረግ ጥረት ከፍተኛ ድፍረትን እንደሚጠይቅ፣ ከአመጽ ይልቅ ለጋራ ውይይት መዘጋጀት ከፍተኛ ድፍረትን እንደሚጠይቅ፣ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጥፋትን ከማድረስ ይልቅ የሰላም ድርድሮችን ማካሄድ ከፍተኛ ድፍረትን እንደሚጠይቅ፣ ከጦርነት ትንኮሳ ይልቅ የሰላም ስምምነቶችን ማክበር እና ቅንነት ከፍተኛ ድፍረትን እና አቅምን እንደሚጠይቅ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2014 ዓ. ም መናገራቸው ይታወሳል።

ሰላም ያስፈለገበት ምክንያት

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ “ሰላም በምድር” በማለት እ. አ. አ 1963 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ሰነድ፣ የሰላም አስፈላጊነት ከማንኛውም የግል ጥቅም ፍላጎት እና የጦር መሣሪያ ኃይል ይበልጣል በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ ለሚታየው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ሕዝቡ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳይገባ ትልቅ ምክር የሚሰጥ ሐዋርያዊ መልዕክት መሆኑ ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ በአፍጋኒስታን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የመግባት አዝማሚያ ቢታይም የሕዝቡ ጥረት መሆን ያለበት የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ ልዩ ልዩ ጎሳዎች እና የእምነት ተቋማት በሰላም እና በመከባበር አብሮ መኖር የሚቻልባትን አገር መገንባት እንደሚያስፈልግ ታውቋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ 1992 ዓ. ም በቅድስት መንበር በኩል ለተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በከባድ የጦር መሣሪያዎች በመታገዝ የአንድን አገር እድገት ማረጋገጥ እንደማይቻል መናገራቸው ይታወሳል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ 1991 ዓ. ም ይህን መልዕክታችውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት በዩጎዝላቪያ ሕዝብ ላይ የደረሰው አሳዛኝ የጦርነት ስቃይ በፎቶግራፍ ምስሎች በመላው ዓለም መሰራጨቱ ይታወሳል።        

ለሰላም ከፍተኛ ዋጋን እና ትኩረት መስጠት

ዛሬም ቢሆን ከአፍጋኒስታን የሚሰራጩ የፎቶግራፍ ምስሎች በአገሪቱ ውስጥ የሕዝቦች ማኅበራዊ ሕይወት እና የፖለቲካዊ አለመረጋጋት መኖሩን የሚያመለክቱ መሆናቸው ታውቋል። በሕዝቡ ላይ የደረሰውን አስከፊ ማኅበራዊ ቀውስ በግልጽ ከሚያሳዩ ምስሎች መካከል ሁለቱ የብዙዎችን ልብ በመስበር የሕሊና ጸጸት ማስከተሉ ታውቋል። ከእነዚህ ሁለት የፎቶግራፍ ምስሎች መካከል የመጀመሪያው አንዲት እናት ልጇን ታቅፋ ከሚደርስበት አደጋ ለማትረፍ ስትሞክር የሚያሳይ እና አንድ አባት ሕጻን ልጁን ከሞት ለማትረፍ ከአጥር ማዶ ላለው ወታደር ሲያቃብል የሚያሳይ ምስል መሆኑ ታውቋል። የአፍጋኒስታንን ሕዝብ ብሶት ከሚገልጹ የፎቶግራፍ ምስሎች መካከል ሌላው፣ ከካቡል አየር ጣቢያ በሚነሱ አውሮፕላኖች ላይ የሚንጠለጠሉ ሰዎች ምስል በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በመገናኛ ብዙሃን በስፋት መታየቱ ይታወሳል። የጦርነት ደመና በሚታይበት፣ የሕዝቦች ስቃይ ጥልቅ በሆነበት ሥፍራ ሁሉ ዘወትር የሰላም ተስፋ መኖሩን የገለጸው የር. ሊ. ጳ ሐዋርያዊ አስተምህሮ፣ ለሰላም ከፍተኛ ዋጋን እና ትኩረትን መስጠት እንደሚያስፈልግ ያሳስባል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ 2013 ዓ. ም ለሶርያ ሰላም በቀረበው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ከህመም እና ከሞት አደጋ ወጥቶ በሰላም ጎዳና ላይ መራመድ እንደሚቻል መናገራቸው ይታወሳል። በሰላም ጎድና ላይ መራመድ የሚቻለውም፣ እያንዳንዱ ሰው ራሱን በጥልቀት መመልከት ሲጀምር እና ህሊናው የሚናገረውን ለማዳመጥ እራስን ሲያዘጋጅ ነው በማለት አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ እያንዳንዱ ሰው ልብን ከሚያበላሽ የስግብግብነት ስሜት በመላቀቅ፣ ግድ የለሽነት በማሸነፍ፣ ለሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት ከሚሆኑ የጥፋት ተልዕኮ ተመልሶ ለውይይት እና ለእርቅ እራስን ዝግጁ እንዲያደርግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው አክለውም የሌሎችን ስቃይ በመመልከት፣  እጆችን ከጥፋት ተግባር በመመለስ ሰላማዊ የጋራ ሕይወትን ለመመስረት የሚያስችል ተስፋን መሰነቅ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ከእንግዲህ ጦርነት አይኑር

ለችግር እና ለስቃይ የተጋለጠው የአፍጋኒስታን ሕዝብም ቢሆን፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እ. አ. አ በ1965 ዓ. ም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ “ከእንግዲህ ጦርነት አይኑር !” በማለት የላኩትን መልዕክት በማስታወስ፣ የጋራ መጋባባት ያለበት ሰላማዊ ማኅበራዊ ሕይወትን መገንባት እንደሚኖርበት የር. ሊ. ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተንህሮ ያሳስባል። ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በመልዕክታቸው፣ የሕዝቦች ሕይወት እና መላው ሰብዓዊ ፍጡር ሊመራ የሚገባው በሰላም እንደሆነ አሳስበው፣ የጦር መሣሪያ መቼም ቢሆን ሰላማዊ መፍትሄን ሊያመጣ የማይችል መሆኑን ገልጸዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ ጥር ወር 1991 ዓ. ም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ለነበሩት ጆርጅ ቡሽ በላኩት መልዕክት፣ “ወደ ኋላ ሊመለሱ የማይችሉ ውሳኔዎችን ለማስወገድ ጥረቶችን እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ምክር ዋጋ ሳይሰጠው ቀርቶ፣ በኢራቅ ሕዝብ ውስጥ እስካሁን ሊወገድ ያልቻለ ከፍተኛ ስቃይ እና ሕመም ማስከተሉ ታውቋል።

በሰላም መኖር ይመረጣል

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ እ. አ. አ በ2013 ዓ. ም እንዳሳሰቡት የአፍጋኒስታን ሕዝብ ያለ ሰላም ወደ ፊት መራመድ እንደማይችል ገልጸው፣ ሰላም በሰው ልጅ ጥረት የሚገለጽ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። “እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው ከሁሉም በላይ ሕዝቦች በእግዚአብሔር ስም የአንድ ቤተሰብ አባል መሆናቸው ሲረዱት ነው” በማለት ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ መናገራቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በነሐሴ ወር 2021 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት፣ የአፍጋኒስታንን ሕዝብ በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአፍጋኒስታን ሰላም ሊወርድ የሚችለው፣ የጦር ማሣሪያዎች ድምጽ ቆሞ በጠረጴዛው ዙሪያ ሰላማዊ ውይይት ሲደረግ ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ሰዎች በሙሉ፣ ሴቶች፣ ሕጻናት እና አዛውንት ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው በሰላም መኖር የሚችሉት እርስ በእርስ በመከባበር ነው ማለታቸው ይታወሳል።       

26 August 2021, 16:31