ለመጀመርያው ለአያቶች እና ለአረጋውያን አለም አቀፍ ቀን የሚደርገው ጸሎት!

በቫቲካን የምዕመናን ፣ የቤተሰብ እና የህይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ይፋ ባደርገው መረጃ መሰረት ሐምሌ 18/2013 ዓ.ም  በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚከበረው የአለም የአረጋውያን እና የአያቶች ቀን አስመልክቶ በቪዲዮ ባስተላለፈው መልእክት በእለቱ የሚጸለየውን ጸሎት ይፋ ማድረጉ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“ጌታ ሆይ ከእኔ ጋር ሆነህ ስለአጽናናህኝ አመሰግንሃለሁ” እነዚህ የጸሎት ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከበረው የአረጋዊያን እና የአያቶች ቀን ላይ ለሚደርገው ጸሎት የመጀመሪያዎቹ የመክፈቻ ቃላት  ናቸው፣ በቫቲካን የምዕመናን ፣ የቤተሰብ እና የህይወት ጉዳዮችን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት በቪዲዮ ይፋ ባደርገው መልእክቱ እንደ ገለጸው። አርብ ዕለት ሐምሌ 16/2013 ዓ.ም በቪዲዮ ተቀርጾ በእስፓኒሽ ቋንቋ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት የተላለፈው መልእክት ጸሎቱ በፈረንሳይኛ ፣ በእንግሊዝኛ ፣ በፖርቱጋልኛ እና በጣሊያንኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንደ ሚተላለፍ የተገለጸ ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 21 አያቶች እና አረጋውያን ወንዶችና ሴቶች 4 ጥንዶችን ጨምሮ ይህ ጸሎት በቀጥታ እንደ ሚደገም ተገልጿል።  ከነዚህም መካከል የ 101 ዓመት እድሜ ያላቸው ካናዳዊው ጳጳስ ሎረን ኖል ኦፍ ይገኙበታል።

ምስጋና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በብቸኝነት ጊዜያትም እንኳ ተስፋን እና መተማመንን ስለሚሰጠን ከእኛ ጋር ሆኖ ጌታ ስለሚያጽናናን ለእዚህ ተግባሩ ጌታን ማመስገን ይገባል ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን የ 84 ዓመት እድሜ ያላቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጌታ ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምሮ እስካሁኑ እስከ ሽምግልናቸው ጊዜ ድረስ ጌታ ዓለት እና መሸሸጊያቸው እንደ ሆነ አስታውሰዋል።

በእለቱ ቤተሰብ ስጦታ ሆኖ ስለተሰጠን እና ጌታ ረጅም ህይወት በፀጋ መልክ ስለሰጠን፣ በሕይወታችን ውስጥ የገጠሙንን ደስታዎች፣ መሰናክሎች፣ ተግዳሮቶች፣ ችግሮች በጽናት እንድናልፍ ለረዳን ጌታ ምስጋና ማቅረብ እንደ ሚገባ የተገለጹ ሲሆን በተጨማሪም የሕይወት ሕልሞች እና ተስፋዎች እውን ይሆኑ ዘንድ ለመጪው ትውልድ ጸሎት እንደ ሚደረግ ተገልጿል።

የሰላም መሣሪያ

አዛውንቶች ለተጠሩበት “የታደሰ የፍሬ ጊዜ” እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። እርሱ እነርሱን የሰላም መሳሪያዎች እንዲያደርጋቸው፣ ከእነሱ የበለጠ የሚሠቃዩትን እንዲያቅፉ፣ ሕልማቸውን በጭራሽ እንዳያቆሙ እንዲያስተምራቸው እና በሕይወታቸው የገጠሟቸውን ድንቅ ነገሮች ለመጪው ትውልድ እንዲተርኩ የቪዲዮ መልእክቱ ይፋ አድርጓል።

በቫቲካን የምዕመናን ፣ የቤተሰብ እና የህይወት ጉዳዮችም የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት በቪዲዮ ይፋ ባደርገው መልእክቱ “የወንጌሉ ብርሃን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲዳረስ” በማለት የጌታን በረከት በሊቀ ጳጳሱ እና በቤተክርስቲያኑ ላይ ይዘንብ ዘንድ የተመኘ ሲሆን በእለቱ የሚደርገው ጸሎት ወረርሽኙ እንዲያበቃ ፣ ድሆች መጽናናትን እንዲያገኙ እና ዓለም የታደሰ ስፍራ ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድ እንደ ሚማጸን ተገልጿል። በተለይም ደግሞ  ጦርነቶች ቆመው መጽናናት በሁሉም የዓለም ክፍል ላይ እንዲሰፍን በእለቱ ይጸለያል።

ጸሎቱ የመጀመሪያውን የዓለም የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ጭብጥ ሐሳብ በማንሳት ይጠናቀቃል ፣ ይህም የኢየሱስ ማረጋገጫ የሆነውን “እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡30) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይጠናቀቃል ማለት ነው። አረጋውያኑ በእርጅና ምክንያት ጉልበት ስለሚያንሳቸው እና ስለሚደክማቸው ቤተሰብ እና ማሕበረሰቡ እንዲደግፋቸው እና እስከ መጨረሻው ድረስ እያንዳንዱን የሕይወት ቅጽበት ሙሉ በሙሉ እንዲኖሩ ያስችላቸው ዘንድ ጌታን ይለምናሉ፣ ይማጸናሉ።

ክብረ በዓሉ

በቫቲካን የምዕመናን ፣ የቤተሰብ እና የህይወት ጉዳዮችም የሚመለከተው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ይህንን የያቶችና የአረጋውያን አለም አቀፍ ቀን እንዲያስተባብር ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህ የመጀመሪያው የአረጋዊያን እና የአያቶች አለም አቀፍ ቀን በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 4 ሰዓት ላይ በሚደርገው መስዋዕተ ቅዳሴ እንደ ሚከበር የተገለጸ ሲሆን አረጋውያንን የሚደግፉ የሐዋርያዊ እንክብካቤ ተግባራትን በሮም አገረ ስብከት ውስጥ የሚያካሂዱ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች እና ማህበራት ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴውን ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። አብዛኛዎቹ አያቶቻቸውን ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ይዘው እንደ ሚመጡ ይጠበቃል። ከነዚህም መካከል ኮቪድ -19 በተባለው ወረርሽኝ ሳቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ አመት በላይ አስገዳጅ በሆነው ከቤት ያለወጣት ሕግ ምክንያት በቤት ውስጥ ተገልለው ለመቆየት የተገደዱ አዛውንቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤታቸው ወጥተው በስፍራው እንደ ሚገኙ ይጠበቃል።

በቅዳሴው መጨረሻ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለአያቶቻቸው እና ለአዛውንቶች “እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመድገም የአበባ ስጦታ ያቀርባሉ።

በእለቱ የሚደገመው ጸሎት

ጌታ ሆይ ከእኔ ጋር ሆነህ ስለ ምታጽናናኝ አመሰግንሃለሁ፤

በብቸኝነት ጊዜ እንኳን፣ አንተ የእኔ ተስፋ እና የእኔ እምነት መተማመኛ ነህ፣

ከልጅነቴ ጀምሮ ዓለቴ እና መሸሸጊያዬ ነህ!

ቤተሰብ ስለሰጠኸኝ እና እንዲሁም ረጅም እድሜ ሰጥተህ ስለባረከኝ አመሰግንሃለሁ።

ላሳለፍኩት የደስታ እና የችግር ጊዜያት፣

በሕይወቴ ውስጥ ቀድሞውኑ ስለተፈጸሙ ሕልሞች፣

እንዲሁም ለወደፊቱ እውን ለሚሆኑ ሕልሞቼ ሁሉ አመሰግንሃለሁ።

የታደሰ ፍሬያማ ጊዜ እንዲኖረኝ ስለፈቀድክ እና ስለጠራህኝ ለዚህ አመሰግንሃለሁ።

አቤቱ ፣ እምነቴን ጨምር፣ የሰላም መሳሪያ አድርገኝ፣

ከእኔ በላይ የሚሰቃዩትን ሰዎችን ማቀፍ እችል ዘንድ፣

ሕልም ማለም እንዳላቆም፣ ድንቅ የሆኑ ነገሮችህን ለአዳዲስ ትውልዶች መናገር እችል ዘንድ አስተምረኝ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቤተክርስቲያንን ይጠብቁ እና ይመሩ ዘንድ፣

የወንጌሉን ብርሃን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲደርስ  ያደርጉ ዘንድ ጠብቅልን።

ጌታ ሆይ ዓለምን ለማደስ፣

የወረርሽኙ አውሎ ነፋስ እንዲረጋጋ ለማደረግ፣

ድሆች መፅናናትን እንዲያገኙ እና ጦርነቶች እንዲያበቁ መንፈስ ቅዱስህን ላክልን።

በድካሜ ደግፈኝ፣ ሙሉ ህይወትን እንድኖር እርዳኝ

በሰጠኸኝ በእያንዳንዱ ደቂቃ ውስጥ

በየቀኑ ከእኔ ጋር አስከ ዓለም ፍጻሜ እንደምትሆን በእርግጠኝነት እንዳምን እርዳኝ።

አሜን!

24 July 2021, 17:52