ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ማንም ሰው በቂ ውሃ እና ምግብ ሊጎድለው አይገባም አሉ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ኮሚሽን ተባብረው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የረሃብ መንስኤዎች እንዲወገዱ፣ ሰብዓዊ ክብር እና የምድራችን ደህንነት እንዲጠበቅ በማለት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረቡትን ጥሪ በቪዲዮ ፊልም አማካይነት ይፋ አድረገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በረሃብ ዙሪያ በርካታ አቅጣጫዎችን በመዳሰስ ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በዓለማችን ውስጥ የብዙዎችን ሕይወት እያሰቃየ ያለው ረሃብ የጋራ ችግር በመሆኑ በጋራ ጥረት ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል። አካባቢያችንን ከጉዳት የማንከላከል ከሆነ፣ ሰብዓዊ ቤተሰብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ  የሚመጣ ከሆነ፣ በአንድ ወገን ሰዎች ጠግበው ሲያድሩ በሌላ ወገን ባዶ ሆዳቸውን የሚያድሩ ከሆነ ረሃብን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ሊሆን አይችልም በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ መሠረት በማድረግ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ኮሚሽን በመተባበር ይፋ ያደረጉት የቪዲዮ መልዕክት፣ በምግብ ሥርዓት ዙሪያ በሮም ከሐምሌ 19 - 21/2013 ዓ. ም. ድረስ ከተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ አስቀድሞ መሆኑ ታውቋል። 

በምርት መጠን እና በአመጋገብ ሥርዓት ላይ ለውጥ ማድረግ

የቪዲዮ ቅንብሩ የተለያዩ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት በተለያዩ ሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ዘመናቸው ያቀረቡትን አስተምህሮ በቅደም ተከተል የሚገልጽ ሲሆን፣ ከእነዚህ አስተምህሮች መካከል ር. ሊ. ጳ ፍራችስኮስ እጅግ ውስብስብ በሆነው የዓለማችን የምግብ ሥርዓት ለውጥን በማስመልከት ያቀረቡትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2014 ዓ. ም በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ባዘጋጀው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ “የሰው ልጅ በልቶ የማደር መብቱ የሚረጋገጠው በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚሰቃይ የሰው ልጅ ከዚህ ችግር ነጻ ሲሆን ብቻ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት እ. አ. አ በ2017 ዓ. ም. በጠራው ጉባኤ ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የሰው ልጅ በአኗኗር ዘይቤው ፣ በሀብት አጠቃቀም ፣ በምርት መመዘኛዎች እና በፍጆታ መጠን ላይ ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል” በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የምግብ መጉደል የሚያስከትለው ስቃይ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም በተከበረው ዓለም አቀፍ የምግብ ቀን ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ምግብ ማምረት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን የሁሉን ሰው ጤናን የሚያሟላ ዘላቂነት ያለው የምግብ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ማሳሰባቸው ይታወሳል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ92ኛው የአመጋገብ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ የተትረፈረፈ ምግብ ለሁሉም እንዲኖር ብለው ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ፣ ለዓለማችን ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ቢኖርም በርካቶች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ የካቲት ወር 2015 ዓ. ም ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት መግለጻቸው ይታወሳል። እ. አ. አ መጋቢት 27/2019 ዓ. ም ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በረሃብ ምክንያት ሰብዓዊ ክብርን ማጣት እጅግ የከፋ ነው ብለው፣ ዛሬም ቢሆን በርካታ እናቶች እና አባቶች ለልጆቻቸው የዕለት ዳቦን ሳያቀርቡ በረሃብ እየተሰቃዩ ያድራሉ ብለዋል።

ለራስ ጥንቃቄን በማድረግ የለውጥ መንገድ መከተል ያስፈልጋል

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ኮሚሽን በመተባበር ይፋ ያደረጉት የቪዲዮ መልዕክት፣ በድሃ ወንድሞቻችን እና እናታችን ላይ ለደረሰው እና በመድረስ ላይ ላለው ኢፍትሃዊነት፣ እንዲሁም በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂዎች እኛው ነን” ማለታቸውን ገልጾ፣ ቅዱስነታቸው የለውጥ መንገድን መከተል ለራሳችን እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን ማድረግ ያስፈልጋል” በማለት ማሳሰባቸውን ገልጿል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በ “አባታችን ሆይ” ጸሎት ዙሪያ ባቀረቡት አስተምህሮ “እግዚአብሔር አባታችን ለሁላችንም የሚያስፈልገንን የዕለት እንጀራን እንደሚሰጥ፣ ይህም ውሃን፣ መድኃኒትን፣ መኖሪያ ቤትን እና ሥራን የሚያካትት መሆኑን አስታውሰው ከእኛ የሚጠበቀው ለመኖር የሚያስፈልገንን በእምነት መጠየቅ እንደሆነ እ. አ. አ በመስከረም 16/2020 ዓ. ም ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸው ገልጸዋል። ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት እ. አ. አ በ2013 ዓ. ም ይዞ በተነሳው መሪ ቃሉ፣ እንዲሁም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት “አንድ እና ብቸኛ ሰብዓዊ ቤተሰብእንዳለ፣ ለሁሉም የሚሆን ምግብ” እንዲኖር በማለት መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።  

29 July 2021, 16:28