ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለሐምሌ ወር ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ማህበራዊ ወዳጅነትን ማጠናከር የሚለው ነው!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐስብ እንደ ሚያቀሩ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ለሐምሌ ወር ይሆን ዘንድ ያቀረቡትን የጸሎት ሐሳብ ይፋ ባደረጉበት ወቅት የፀሎቱን ዓላማ አስመልክቶ ባቀረቡት የቪዲዮ መልእክት “ከፖለቲካዊ እና ህዝባዊነት ጋር በተያያዘ መልኩ የሚነሱትን ግጭቶች፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ውስጥ ደፋር እና በጥንካሬ ተሞልተው ውይይቶች እንዲካሄዱ እና የወዳጅነት መንፈስ እንዲስፋፋ ማደረግ የምንችል ንድፍ አውጪዎች ልንሆን እንችላለን” ለዚህም እንጸልይ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስፓኒሽ ቋንቋ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት በንግግራቸው ላይ ያተኮሩት “እውነታውን በአዲስ መንገድ የማየት ጎዳና በመሆኑ የጋራ ጥቅምን በመገንባት ረገድ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች ለመፍታት በፍቅር መኖር እንችላለን” ብለዋል። አክለውም የሚከፋፍለንን እና ተቃርኖ የሚፈጥሩትን ነገሮች እንድናቆም ጥሪ አቀርባለሁ ያሉ ሲሆን “ለጠላትም ሆነ ለጦርነት” ክፍት የሆነ ቦታ እንዳይኖር በዚህ በሐምሌ ወር ጸሎታችንን ማቅረብ ይኖርብናል ብለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቪዲዮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች በአለም አቀፉ የጸሎት አውታረመረብ በኩል ለወንድማማችነት እና ለወዳጅነት እንጸልይ በማለት በአደራ በመስጠት ነው የተለቀቀው።

በሐምሌ ወር ውስጥ በማህበረሰቡ ውስጥ እና በግለሰቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እና ምክንያቶችን ለመፍታት ሁሉም “የውይይት እና የወዳጅነት መሐንዲሶች” እንዲሆኑ ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮስ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ብዙ ግንኙነቶችን የሚያፈርስ የማያቋርጥ ተቃርኖ መፍጠር እና ማህበራዊ ጠላትነትን ማስወገድ የሚቻለው በውይይት ብቻ ነው ብለዋል።

ቅዱስ አባታችን እርስ በእርሳቸው እጃቸውን ከሚዘረጉ ወንዶችና ሴቶች ጋር የጋራ ጥቅምን እንዲገነቡ እንድንጸልይ እና በተለይም “በጣም ድሆች እና ተጋላጭ ከሆኑት ዳርቻዎችላይ  ካሉ” ሰዎች ጎን እንድንሆን ይጠይቃሉ።

ውይይት ተቃርኖን ይዋጋል

ስለ ጸሎቱ ዓላማ ከሊቀ ጳጳሱ የአለም አቀፍ የፀሎት አውታረ መረብ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደ ሚያሳየው እ.አ.አ ከ 1946 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦርነት እና የሞት ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም ፣ በማህበረሰብ ደረጃ ግጭቶች እና ሁከቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተንሰራፍተው ይገኛሉ። ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በአካል ባይገለጥም ፣ ብዙ ግንኙነቶች እስከ መበከል ድረስ የሚያበቃ ጥቃቶች እና ተቃሮዎች ቁጥር እጅግ በጣም እየጨመረ እንደ መጣ ማስተዋል እንችላለን ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.ኤ.አ. በ 2016 ዓ.ም ይህን አስመልክተው ቀደም ሲል አስጠንቅቀው የነበረ ሲሆን ለምሳሌም “በመካከላችን ያሉት እንደ የባዕድ አገር ሰዎች፣ ስደተኞች ወይም መጤ የሆኑ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ በፍጥነት ስጋት ሆኖ ፣ የጠላትነት ደረጃን ሲይዙ እናያለን” ብለው እንደ ነበረ መግለጫው የጠቀሰ ሲሆን  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተቃርኖ እና ጠላትነትም እንዲሁ የአስተሳሰብ ፣ የስሜት እና የአሠራር መንገዶቻችንን እየወረረ የመጣ “ቫይረስ” እንዴት እንደሆነ በጥልቀት እየተመለከትን እንገኛለን ብሏል።

ቅዱስ አባታችን በቪዲዮ መልእክታቸው እንዳመለከቱት ዛሬ “የፓለቲካ፣ የኅብረተሰባችን እና የመገናኛ ብዙሃን አካላት ሳይቀሩ የጠላትነት እና የጥላቻ ስሜቶችን ለመዝራት እና ለመፍጠር በከፍተኛ ሁኔታ እየሰሩ የሚገኙትን ተግባራት እንመለከታለን” ብለዋል። ለዚህም ነው “በጥሩ መንፈስ አብሮ ለመኖር በጣም አስፈላጊ የሆነውን ማህበራዊ ወዳጅነት መገንባት” ያለብን ፣ የመገናኘት ባህል መፍጠሩን ለመቀጠል እንደ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ወዳጅነት ፣ ከሁሉም በላይ ለቅርብ ሰዎች ቅርብ እንድንሆን የሚያደርገን በችግር ላይ ያሉ ፣ በጣም ድኸ እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ይቻለን ዘንድ ውይይት ማድረግ እና ማሕበራዊ ወዳጅነትን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።

የጋራ ጥቅምን መገንባት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጣሊያነኛ ቋንቋ ፍራቴሊ ቱቲ ( ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) በሚለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው ውስጥ ስድስተኛውን ምዕራፍ “ማሕበራዊ ውይይት እና ወዳጅነት” የሚል አርዕስት ሰጥተው ነበር።

"ትክክለኛ ማህበራዊ ውይይቶች የሌላውን አመለካከት የማክበር ችሎታን ያካትታል እናም ጥርጣሬዎችን እና ጭንቀቶችን ሊያስወግድ ይችላል" በማለት የገለጹ ሲሆን በዚሁ ለሐምሌ ወር ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ወይም ዓላማ ፣ ይህንን ውይይት አጠናክሮ በመቀጠል ውይይቱ “እውነታውን በአዲስ መንገድ ለማየት ትልቅ ዕድል መሆኑን ያረጋግጣል ፣ ስለሆነም የጋራ ጥቅምን በመገንባት ረገድ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በፍቅር በመኖር መሻገር እንችላለን” በማለት አረጋግጧል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ኔትወርክ እንዳመለከተው ለውይይት ቅድሚያ መስጠት ማለት የተቃርኖ አመክንዮን በመተው እና ይህንን በአክብሮት መተካት ማለት እንደ ሆነ የገለጸ ሲሆን ሌሎችን ለማጥፋት መፈለግ ማለት አይደለም፣ በልዩነቶች ውስጥ ብልጽግና ሊኖር ይችላል ፣ ነገር ግን ውይይት ከሌለ ወደ ጠላትነት ፣ ዛቻ እና አመፅ እንዲናመራ ሊያደረግ ይችላል ብሏል።

ከብዙ ዓመታት በፊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “እኛ ከሩቅ አገሮች የመጣን ነን ፤ እኛ የተለያዩ ባህሎች ፣ የቆዳ ቀለም ፣ ቋንቋዎች እና ማህበራዊ ዳራዎች አሉን፣ እኛ በተለየ መንገድ እናስባለን፣ እምነታችንን በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እናከብራለን። ከእነዚህ አንዳቸውም ጠላት አያደርጉንም፣ ይልቁንም ትልቁ ሀብታችን ናቸው” ማለታቸው ይታወሳል።

07 July 2021, 15:42