ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔርን አስደናቂነት ለማወቅ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ሰኔ 27/2013 ዓ. ም በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት ከማር. 6፡ 1 - 6 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማቅረባቸው በፊት ባቀረቡት ስብከት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ አገሩ በናዝሬት ከነዋሪዎቹ እና ከደቀመዛሙርቱም ጭምር ተቃውሞ እንደደረሰበት በሚገልጽ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። የናዝሬት ነዋሪዎች እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ በመካከላቸው ለመሆን መምጣቱን ባለማመናቸው የተነሳ ተቃውሞ የደረሰበት መሆኑን አስታውሰው “የግል ምቾት እና የጥላቻ መንገድ መጓዝ በምንመርጥበት ጊዜ እኛም እንደ እነርሱ እንሆናለን” ብለዋል።

ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ከዚህ ቀጥሎ፣ ቀደም ብሎ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተነተን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

እሑድ ሰኔ 27/2013 ዓ. ም ከማር. 6: 1 -6 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ መንደሩ ሰዎች ተቃውሞ እንደገጠመው እና በእርሱ አለማመናቸውን ይናገረናል። ኢየሱስ በገሊላ እና ሌሎች አካባቢዎችም ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ከእናት ማርያም እና ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ወዳደገባት ወደ ናዝሬት ከተማ መጣ። ወደ ምኩራብም ገብቶ ማስተማር ጀመረ። ትምህርቱንም ይከታተሉ የነበሩ በርካታ ሰዎች፣ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘ? በሠፈራችን በደንብ የምናውቃቸው የአናጺው የዮሴፍ እና የማርያም ልጅ አይደለምን በማለት ራሳቸውን መጠየቅ ጀመሩ (ማር. 6፡ 1-3)። ኢየሱስም ይህን በማወቅ ከዚህ በፊት በሕዝቡ መካከል ሳይታወቅ የቆየውን አንድ እውነት እንዲህ በማለት አረጋገጠላቸው፥ “ነቢይ በሌሎች ዘንድ ይከበራል፤ በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹና በቤተሰቡ መካከል ግን ይናቃል” ብሎ መለሰላቸው። ይህን እኛም ብዙ ጊዜ እንላለን ።

የኢየሱስ መንደር ሰዎች አስተሳሰብን እንመልከት። ኢየሱስን ያውቁታል እንል ይሆናል። ነገር ግን ኢየሱስን በሚገባ አልተገነዘቡትም። በማወቅ እና በመገንዘብ ወይም በመረዳት መካከል ልዩነት አለ። ከአስተሳሰቡ ጀምሮ ስለ አንድ ሰው ብዙ ነገሮችን ልናውቅ እንችላለን። ሌሎች ሰዎች የሚሉትን በማከል ስለ አንድ ሰው ብዙ ነገሮችን ልናውቅ እንችላለን። ከዚህም አልፎ ተርፎ ያንን ግለ ሰብ በአካልም ልናገኘው እንችላለን። ነገር ግን የዚያን ሰው ማንነት ለማወቅ ይህ ሁሉ በቂ አይደለም። ስለ አንድ ግለ ሰብ ያለንን ተራ ዕውቀት ይገልጽ ይሆናል እንጂ እውነተኛ ማንነቱን አይገልጽም። ይህ ሁላችንንም የሚያጋጥም ስህተት ነው። ስለ አንድ ሰው በጣም የምናውቅ ይመስለናል ፣ ከዚህም በከፋ ፣ ልዩ ስም እና መለያ እናወጣለታለን። በውስጣችን በተፈጠረው የተሳሰተ ግምት የተነሳ ከዚያ ሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረን እናደርጋለን። የናዝሬት አካባቢ ሰዎችም ለሰላሳ ዓመታት ኢየሱስን ያወቁት በዚህ መንገድ ነው። ስለ ኢየሱስ ሁሉን ነገር ያወቁ ይመስላቸው ነበር። “ይህ በመካከላችን ያደገ፣ የእንጨት ጠራቢው ዮሴፍ ልጅ፣ የማርያምም ልጅ አይደለምን? ይህን ሁሉ ጥበብ ታዲያ ከየት አገኘው?” ይሉ ነበር። የመንደሩ ሰዎች ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ በጭራሽ አልተገነዘቡም። እርሱን የሚያውቁት በስሱ እንጂ የእርሱ እውነተኛ ማንነት፣ በእርሱ ውስጥ ያለውን አዲስ ነገር ለማወቅ ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም።

ይህ መሆኑን ስናስተውል ወደ እውነተኛ ችግር ውስጥ መግባት እንጀምራለን። ለእኛ ብቻ በሚመቸን መንገድ ማሰብ ስንጀምር፣ በጥላቻ እና የበላይነት ስሜት ውስጥ ስንገኝ፣ ልባችንን እና አዕምሮአችንን ከፍተን አዲስ ነገር ለማወቅ ያለን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ይጠፋና አመለካከታችንን መቆጣጠር ሳንችል ቀርተን በጭፍን ጥላቻ ውስጥ ለመኖር እንገደዳለን። ይህ ደግሞ በዕለታዊ ሕይወታችን ሊከሰት የሚችል ገጠመኝ ነው። ይህን ዝንባሌ ለመለወጥ ጥረት ሳናደርግ ቀርተን ከራሳችን ሀሳብ ጋር ከሚስማሙ ሰዎች ጋር ብቻ መሆንን እንመርጣለን። ይህ ሁኔታ “ኢየሱስን እናውቃለን፣ ስለ ኢየሱስ ቀድሞውኑ ብዙ ስለሰማን ተመሳሳይ ነገሮችን መድገም በቂ ነው” ብለን በምናስብ በእኛ በአማኞች መካከልም ሊታይ ይችላል። ነገር ግን እንዲህ ብሎ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ በቂ አይደለም። አዲስ ነገርን ለመረዳት፣ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራ ለማወቅ ዝግጁ የማንሆን ከሆነ እምነት ቀስ በቀስ ይደክም እና ማህበራዊ ልማድ ብቻ ሆኖ የሚቀር ይሆናል።

ለመሆኑ “የእግዚአብሔር አስደናቂነት” ስንል ምን ማለታችን ነው? የእግዚአብሔርን አስደናቂነት የምናውቀው ከእርሱ ጋር ስንገናኝ ነው። “እግዚአብሔርን አግኝቼዋለሁ” እንላለን። ከቅዱስ ወንጌል እንደምንረዳው፣ ብዙ ጊዜ ኢየሱስን ያገኙት እና እሱን የተረዱት ሰዎች በጣም ሲገረሙ እናያለን። እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ስንገናኝ ሊገርመን እና በእርሱ ልንደነቅ ይገባል። ይህ ከሆነ እግዚአብሔርን የምናውቀው በልማድ ሳይሆን በእውነት እንደምናምን የምናረጋግጥበት ማስረጃ አለን ማለት ነው።

የኢየሱስ መንደር ሰዎች ኢየሱስ ማን መሆኑን ያልተገነዘቡት እና በእርሱ ያላመኑት ለምን ይመስላችኋል? ምክንያታቸውስ ምንድነው? ብለን ብንጠቅ መልሱ በአጭሩ፥ እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ በመካከላቸው መሆኑን ባለማመናቸው ነው። ቃል ስጋን በመልበስ በሰዎች መካከል የመገለጡን ምስጢር አያውቁም ነበር። አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ምስጢሩን አልተቀበሉትም ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር በትንሹ ስጋችን በኩል ተገልጦ ማየት ውርደት ይመስላቸው ነበር። በሰፈራቸው ውስጥ የሚያቁት አናጺ ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ማግኘት፣ የእግዚአብሔር መለኮታዊነት በሰው ልጅ ስጋ ውስጥ ተደብቆ መኖር፣ የእግዚአብሔር መልክ፣ የእግዚአብሔር ቃል እና መላው ገጽታ በትንሽ ሰው በኩል ይገለጣል ብለው ፈጽሞ ስላልጠበቁ ማመን አቅቶአቸዋል። እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ በሰዎች ዕለታዊ ሕይወት መካከል መገለጡን እንደ ውርደት ይቆጥሩት ነበር። እግዚአብሔር በናዝሬቱ ኢየሱስ በኩል ስጋን ለብሶ ሰው በመሆን ከመካከል አንዱ ሆኖ መገኘትን መረጠ። በዚህም “ከመካከላችን አንዱ ነህ” ብለን ለኢየሱስ በጸሎት ልንገልጽለት እንችላለን። ይህን የምንለው እርሱ ስለሚያውቀን፣ ስለሚጠብቀን፣ ይቅር ስለሚለን፣ ስለሚወደን እና ሌሎች ብዙ መልካም ነገሮችን ስለሚያደርግልን ነው።

በዓይናችን የማናየውን፣ በሁኔታዎች ሁሉ የማይሳተፈውን፣ ከማኅበራዊ ሕይወታችን ርቆ የሚገኘውን እግዚአብሔር፣ ነገር ግን በሕይወታችን ውስጥ ዘወትር አስደናቂ ነገሮችን በሚፈጽም በእግዚአብሔር ላይ እምነታችንን ማድረግ ያስፈልጋል። ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ በመካከላችን የተገኘው ትሑት ሆኖ ወደ እኛ በመቅረብነው። በየዕለቱ ከእኛ ጋር ይኖራል። የናዝሬት ከተማ እና አካባቢው ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ የመንደራቸውም ሰው ሆኖ ማንነቱን በትክክል እንዳላወቁት ሁሉ፣ እኛም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር እየተጓዘ ማወቅ እና መረዳት በማንችልበት ሁኔታ ላይ ልንገኝ እንችላለን።

በመሆኑም በናዝሬት ውስጥ በዕለታዊ ሕይወቷ የእግዚአብሔርን ምስጢር ተቀብላ የኖረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራዎች መመልከት የምንችልበትን ዓይን እና ልብ እንድትሰጠን በጸሎታችን እንጠይቃታለን።"             

05 July 2021, 19:37