ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሲደረገላቸው የነበረውን ሕክምና ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቫቲካን ተመለሱ! ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሲደረገላቸው የነበረውን ሕክምና ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቫቲካን ተመለሱ! 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሲደረገላቸው የነበረውን ሕክምና ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቫቲካን ተመለሱ!

የቫቲካን ፕሬስ ጽ / ቤት ዋና ዳይሬክተር በሐምሌ 07/2013 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስገነዘበው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኘው ጄሜሊ በመባል በሚታወቀው ሆስፒታል ውስጥ ሲደረግላቸው የነበረውን የሕክምና እርዳታ አጠናቀው እኩለ ቀን አካባቢ ወደ ቫቲካን መመለሳቸውን መግለጫው ይፋ አድርጓል። ቅዱስነታቸው ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት በሮም ከተማ ውስጥ ወደ ሚገኘውም ሳንታ ማርያ ማጆሬ በመባል ወደ ሚታወቀው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ሂደው በመሳለም፣ አመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሕመማቸው ወቅት ከእርሳቸው ጋር ሆና ስላጽናናቻቸው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን በሆስፒታል የነበራቸው ቆይታ ደስ የሚያሰኝ ውጤት በማስገኘቱ እና በእነዚህ ቀናት ውስጥ የተገናኟቸው የታመሙትን ሰዎች ሁሉ በማስታወስ ጽሎት ማድረጋቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አስቀድሞ በተያዘላቸው ቀጠሮ መሠረት እሑድ ሰኔ 27/2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ የሕክምና ዕርዳታን ለማግኘት ወደ ሆስፒታል አቅንተው እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው የአንጀት ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ባሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሆናቸው እና ከሕመማቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለማገገም በመብቃታቸው ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል።

ይህንን በተመለከተ የቫቲካን ፕሬስ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ማቲዎ ብሩኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ዛሬ በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 11፡30 ላይ ቅዱስነታቸው ወደ ቫቲካን መመለሳቸውን የተናገሩ ሲሆን እንደ ተለመደው ቅዱስነታቸው ማንኛውንም ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት እና ማነኛውንም ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሮም ከተማ በሚመለሱበት ወቅት እና እንዲሁም ሕመምን ጨምሮ አንዳንድ ጉዳዮች በሚያጋጥሟቸው ወቅት በሮም ከተማ እንብርት ላይ በሚገኘው በማርያም ስም ከተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በአውሮፓ አህጉር በትልቅነቱ እና በጥንታዊነቱ በሚታወቀው “ሳንታ ማርያ ማጆሬ” በመባል በሚታወቀው ባዚሊካ ውስጥ ተገኝተው፣ በዚያው “በሳናታ ማርያ ማጆሬ” ባዚሊካ ውስጥ በሚገኘው ባላቲን ቋንቋ “Salus Populi Romani” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የሮም ከተማ ሕዝቦች አዳኝ ወይም ጠባቂ” በመባል የምታወቀው እና በአብዛኞቹ  የሮም ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕጻኑን ኢየሱስን በእጆቹዋ ላይ አቅፋ መያዙዋን የሚያሳየው ቅዱስ የሆነ ምስል ስር በመገኘት የተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና መልካም ውጤት በማሳየቱ ለማመስገን እና ለታመሙ ሁሉ ጸሎት ፣ በተለይም በሆስፒታል ውስጥ በነበሩበት ወቅት ያጋጠሟቸው በሽተኛ ሰዎች ሁሉ በጸሎት እንዳሰቧቸው አክለው ገልጸዋል።

በቅርቡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊደረግላቸው ወደ ሆስፒታል በመግባታቸው የተነሳ የዓለም ዓይኖች ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወደ ጄሜሊ ሆስፒታል አሥረኛ ፎቅ የተዘዋወረበት የአንድ ሳምንት ጊዜ አሁን ተጠናቋል። ቅዱስነታቸው በሆስፒታል በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ የተቀበሏቸውን በርካታ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶችን አስታውሰው መልካምን ለተመኙላቸው ሁሉ ልባዊ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል። ለቅዱስነታቸው የመልካም ምኞት መልዕክት ከላኩት መካከል የአርመኒያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ዳግማዊ ይገኙባቸዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ካሬኪን ዳግማዊ “በክርስቶስ የተወደድክ ወንድሜ” ባሉት መዕክታቸው በሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ወቅት የእግዚአብሔርን ጥበቃ እና ምሕረት፣ ፍሬያማ ሐዋርያዊ አገልግሎትን የሚያቀርቡበት ረጅም ዕድሜን እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

በርካታ አገራት መሪዎችም እና እንዲሁም የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ለቅዱስነታቸው መልካም ምኞታቸውን የገለጹላቸው ሲሆን፣ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የታይዋን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ትሳይ ኢንግ-ዌን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ. ም. መልዕክት መላካቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ስለተደረገላቸው ጸሎት እና ስለተላከላቸው የመልካም መግለጫ መልእክት ሁሉንም ማመስገናቸው ተገልጿል።

14 July 2021, 15:18