ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ችግር የበዛበት፣ አመጽ እና ሕመም ያለበት ነው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ችግር የበዛበት፣ አመጽ እና ሕመም ያለበት ነው 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ ለሰው ልጅ ትኩረትን የሚሰጥ መሆኑን አስገነዘቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓርብ ሐምሌ 23/2013 ዓ. ም የተከበረውን ጸረ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቀረት የሚቻለው ለሰው ልጅ ትኩረትን በመስጠት መሆኑን አስገንዝበዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕለቱ በየዓመቱ እንዲከበር እ. አ. አ በ2013 ዓ. ም መወሰኑ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው የወንጀሉ ሰለባ የሆኑትን ነጻ ማውጣት የሚቻለው በጋራ በመሥራት መሆኑን አስረድተዋል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት ከተለያዩ ካቶሊካዊ ደናግል ማኅበራት የተወጣጡ ከሦስት ሺህ በላይ አባላት ያሉበት “ታሊታ ኩም” የተሰኘ ማኅበር እስያን፣ ደቡብ አሜሪካን እና አፍሪቃን ጨምሮ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊትም ባስተላለፉት መልዕክታቸው ሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል በማኅበረሰብ መካከል የማግለል ባሕልን ማስወገድ፣ የቸርነት ተግባራትን ማሳደግ እና ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል። በሁሉም አገራት በሚገኙ ሴቶች እና ወንዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም፣ ሐምሌ 23 ቀን በየዓመቱ እንዲከበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ  መወሰኑ ይታወሳል። “ታሊታ ኩም” የተሰኘው ዓለም አቀፍ የገዳማዊያት ማኅበር “ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዳይፈጸም ጥንቃቄን እናድርግ” በሚለው የዘንድሮ መሪ ቃል ከአንድ ሳምንት በፊት ዘመቻ መጀመሩ ታውቋል። ዓላማውም ለወንጀሉ የተጋለጡትን እና ከወንጀሉ ላመለጡት አስፈላጊውን እንክብካቤን ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። “ታሊታ ኩም” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ማኅበሩ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበበ በመምጣት ከእስያ አህጉር ጀምሮ እስከ ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ኮሎምቢያ ድረስ በመንቀሳቀስ መልካም ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ መሆኑ ታውቋል።

“ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያት ማኅበር ዋና አስተባባር የሆኑት እህት ገብርኤላ ቦታኒ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በእስያ አህጉር ውስጥ የተጀመረው እና የተስፋ ዘርን በመስጠት ላይ የሚገኘው መልካም ተነሳሽነት ከወንጀሉ ያመለጡት በሙሉ የወጣባቸውን ቁስል ሳይዘነጉ እና ራሳቸውንም እንደገና ለጉዳት ሳያጋልጡ፣ የሚያጋጥማቸውን ችግር በመቋቋም፣ ዘወትር ብርሃንን በመፈለግ አዲስ ሕይወት መጀመር እንዲችሉ የሚያደርጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ  እስያ የሚገኙ ወጣቶች “ታሊታ ኩም” ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያት ማኅበር ጋር ግንኙነት መፍጠር መቻላቸውን የገለጡት እህት ገብርኤላ ቦታኒ ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችሉ መርሃ ግብሮችን ተቀብለው ለተግባራዊነት መነሳታቸውን ገልጸዋል። መርሃ ግብራቸውን በተግባር መተርጎም እንዲችሉ ዓለም አቀፉ ማኅበራቸው በአባላቶቻቸው በኩል ድጋፍ የሚያደርግላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ በተነሳሽነታቸው መካከል እንቅፋቶችን የፈጠረ ቢሆንም ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም እውነታውን መጋፈጥ አስፈላጊ መሆኑን አክለው አስረድተዋል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ችግር የበዛበት፣ አመጽ እና ሕመም ያለበት ቢሆንም በኅብረት ተዋግቶ ለማሸነፍ የሚያስችል ትልቅ ተስፋ ያለበት መሆኑንም እህት ገብርኤላ ቦታኒ ገልጸዋል። ወጣቶች ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ተስፋን በመሰነቅ ምስክርነትን ለመስጠት መዘጋጀት ያለባቸው መሆኑን ተናግረው፣ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን በሰጠን ውበት ላይ ጸንተን በመቆም፣ ምኞታችንን እውን የምናደርግበትን ልብ መያዝ እጅግ አስፈላጊ፣ መሠረታዊ እና አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ኮሎምቢያ የሚገኙ እህቶች ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል፣ ለወንጀሉ የተጋለጡትን እና ከወንጀሉ ያመለጡትን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት መልካም ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ መሆናቸውን የገለጹት እህት ገብርኤላ ቦታኒ፣ የወንጀሉን አስከፊነት በቃላት እንዲገልጹ የተጋበዙት ሰዎች ሕይወታቸውን በማስመልከት በግጥም የሚያቀርቡት ምስክርነት ያስገረማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የተከበረውን ጸረ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ለሰው ልጆች እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የጋራ ጥረቱ በህጎች የሚመራው እና በልዩ ፍላጎቶች ላይ ሳይሆን ፍትሕን በሚያበረታቱ ተግባራት ላይ የሚመካ መሆኑን አስረድተዋል።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በኒዮሊበራል ካፒታሊዝም በመመራት ለስኬታማነቱ መልካም አጋጣሚዎችን የሚያገኝ፣ ሥነ-ምግባር በጎደለ መልኩ ትርፋማነትን ያለ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ገደቦች ለማሳደግ ያለመ የገበያ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል። ይህን ሥርዓት መከተሉ ጥቅም እና ጉዳት መኖሩን ገልጸው ነገር ግን ምርጫዎቹ በስነ ምግባር መመዘኛዎች ላይ ሳይሆን በፍላጎቶች ላይ ሲመሠረቱ፣ ከላይ ሲታዩ ለሰው ልጆች እና ለሥነ ምኅዳር ጠቃሚ መስለው ነገር ግን ለጭቆና እና ለብዝበዛ ጥሩ ዕድሎችን ያመቻቻሉ ብለዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበት ኤኮኖሚ፣ የሰውን ልጅ ማዕከል በማድረግ በሕይወቱ ላይ ጫናን ሳይፈጥር፣ የአጭር ጊዜን ብቻ ሳይሆን የረጅም ጊዜን ችግር ለመፍታት ጥረት የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል። 

31 July 2021, 14:57