ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን ተወካዮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን ተወካዮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “አንድነትን ለማምጣት በምናደርገው ጥረት ኢየሱስ ከእኛ ጋር ነው”!

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሰኔ 18/2013 ዓ. ም ከዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን ተወካዮች ጋር ተገናኝተዋል። በቫቲካን ውስጥ ለተቀበሏቸው የፌዴሬሽኑ ተወካዮች ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በሉተራን ቤተክርስቲያን መካከል የሚደረገው የጋራ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው፣ ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በልበ ሙሉነት ማቅረብን በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነት ጎልቶ እንዲታይ የሚያግዙ የጋራ ቸርነት ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው “ወደ ውህደት የምናደርገው ጉዞ ረጅም እና ውስብስብ ውይይቶችን የሚጠይቅ ቢሆንም ለአንድነት ብለን በምናደርገው ጥረት መካከል ኢየሱስ ከእኛ ጋር ሆኖ ይደግፈናል” በማለት በቫቲካን ለተገኙት የዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን ተወካዮች አስረድተው፣ ጥረታችን በአንድነት መካከል ልዩነቶች መኖራቸውን በመገንዘብ ወደ እርቅ መድረስ ነው ብለዋል። እ. አ. አ 2016 ዓ. ም በስዊድን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ በሉንድ ከተማ በሚገኝ የሉተራን ካቴድራል ውስጥ ተገናኝተው የኅብረት ጸሎት ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ስዊድን ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የማይረሳ ታሪካዊ ጉብኝት መባሉ ሲታወስ፣ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በመካከላችን የጋራ ውይይቶችን በማድረግ እና ምስክርነቶችን በመስጠት ወደ እርቅ የሚመራንን የወንጌል ኃይል ተመልክተናል ብለው ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አንዱ ለሌላው እንግዳ ሳይሆን ወድንማማቾች ነን በማለት ወደ አንድነት የሚመሩ መንገዶችን መመኘታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

አንድ የሚያደርገንን እምነት መናዘዝ

በመካከላችን የሚታዩ ችግሮች የምንፈልገውን መፍትሄ እንድናገኝ ያግዘናል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በመካከላችን ለዘመናት ያህል የቆዩት ችግሮች ወደ አንድነት የሚያደርሱ መፍትሄዎችን ለማግኘት ያግዙናል ብለው፣ መፍትሄን ለማግኘት ችግር ሊኖር ይገባል ብለው፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚታይ ችግር የእግዚአብሔር በረከት ነው ብለዋል።

በክርስቲያኖች መካከል ሙሉ አንድነት እንዲመጣ በጋራ መጸለይ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ በሰኔ ወር 1980 ዓ. ም “Confessio Augustana” የተባለ ሰነድ ይፋ የሆነበት 450ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሰው፣ ሰነዱ የሉተራን ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ለሌሎች አብያት ክርስቲያናት እምነት እና ሕይወት የሚጠቅም መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸዋል።

እ. አ. አ ሰኔ 25/2030 ዓ. ም ሰነዱ ይፋ የሆነበት 500ኛ ዓመት የሚከበር መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ  ገልጸው “Confessio Augustana” የተባለ ሰነድ ዛሬ በዘመናችንም ወደ አንድነት ጎዳና የሚመልሰውን የእምነት ምስጢር በጋራ መናዘዝ እንድንችል ያግዘናል ብለው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ፣ በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካል እና አንድ ተስፋ አለ፤ እንዲሁም አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት እና አንድ ጥምቀት አለ (ኤፌ. 4: 4-5) ማለቱንም አስታውሰዋል።   

አንድ አምላክ ብቻ

ሰነዱ በመጀመሪያ ምዕራፉ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት አንድ እና የቅድስት ስላሴ ምስጢር የተገለጠበት መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የኒቂያ ጉባኤን አስታውሰዋል።   በኒቂያው ጉባኤ ወቅት የጸደቀው የእምነት መግለጫ መንገድ የሚያገለግለው ለካቶሊክ እና ለሉተራን አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን ወንድም ከሆነው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና ከሌሎችም በርካታ የክርስትና እምነቶች ጋር የሚያተሳስር የእምነት መግለጫ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። የኒቂያው ታላቅ ጉባኤ የተካሄደበት 1700ኛ ዓመት እ. አ. አ 2025 ዓ. ም የሚከበር መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የጉባኤው ፍሬ የእግዚአብሔር ስጦታ፣ ለክርስቲያኖች ኅብረት አዲስ ኃይል የሚሰጥ እና ወደማይቀለበስ የአንድነት ጎዳና የሚመራ መሆኑን አስረድተዋል።

አንድ ጥምቀት ብቻ

ቅዱስ ጥምቀት ለሁሉም የክርስትና እምነቶች በጋራ የተሰጠ መለኮታዊ ስጦታ፣ ወደ ሙሉ አንድነት ለመድረስ ለምናደርገው ጥረት ቀዳሚ ምልክት መሆኑን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ ጥረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማሻሻል የሚደረግ ጥረት ሳይሆን በኅብረት እንድንጓዝ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ጸጋ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ምስጢረ ጥምቀት በሰዎች ሽምግልና እና ስምምነቶች ላይ የሚወሰን ሳይሆን ልብን በሚያጸዳው በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ በመመስረት ግትርነትን በማሸነፍ ወደ አዲስ ኅብረት የሚመራን መንገድ ነው ብለዋል። 

የቅዱስ ጥምቀት ምስጢር ወደ ታይታ ስምምነት ወይም እርቅ የሚመራ ሳይሆን በልዩነቶች መካከል ወደ እርቅ የሚመራ የእውነተኛ አንድነት መንገድ ነው ብለዋል። በመሆኑም በዚህ ብርሃን በመመራት በካቶሊክ እና በሉተራን ቤተክርስቲያናት መካከል የሚደረገው የጋራ ውይይት መልካም ፍሬን ያፈራ ዘንድ የማያቁርጥ ጸሎትን በእምነት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ፣ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነት ጎልቶ እንዲታይ የሚያግዙ የጋራ ቸርነት ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አንድ አካል ብቻ

በክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ምን ያህል ሕመም እንዳስከተለ ስናሳስብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በደቀ ማዛሙርቱ መካከል ያየውን ልዩነት እኛም በመካከላችን እያየን እንገኛልን ብለው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት መሳተፍን የሚገልጽ የጽዋ ስጦታ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በአንድ መንበረ ታቦት ዙሪያ አለመሰብሰባችን ሕመምን አስከትሎብናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያኖች አንድነት በመፈለግ ወደ አባቱ ዘንድ ጸሎት ማቅረቡን አስታውሰዋል።

ኢየሱስ ከእኛ ጋር ነው!

ቀጣዩ ጥረት በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት፣ ሐዋርያዊ አገልግሎትን እና ቅዱስ ቁርባንን የሚመለከት እንደሚሆን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በእነዚህን የጋራ ቅርሶች ላይ መንፈሳዊ ትህትናን አክለን የማንመለከታቸው ከሆነ ስነ-መለኮታዊ አመለካከቶች አንዳንድ ጊዜ ወደ ልዩነቶች ሊመሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል። የዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን እ. አ. አ በ2023 ዓ. ም የሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ካለፈው አሳዛኝ ታሪክ በመውጣት፣ እግዚአብሔር በሁሉ ሥፍራ እና ለዘመናት ሁሉ እንድንገለገልባቸው ለሰጠን በርካታ መንፈሳዊ እሴቶች ዋጋን መስጠት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሙሳ፥ ዕርቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ ነው

ከር. ሊ.  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር ቀጥለው የተናገሩት የዓለም ሉተራን ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍሊቡስ ሙሳ በበኩላቸው የዕርቅ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የሚገለጥበት መንገድ እንደሆነ ገልጸው፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ፊታችንን ወደ ባልንጀራችን እንድንመልስ ያደርገናል ብለዋል። ከፍቅር የተነሳ እምነትም የበለጠ ጠናካራ ይሆናል ብለው፣ በድሆች፣ በማኅበረሰቡ መካከል ተረስተው በቀሩት፣ በዓለም በተበዘበዙት በኩል ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት የሚቻል መሆኑን አስረድተው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ እና የሉተራን አብያተ ክርስቲያናት በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዴት መኖር እንደሚቻል ለማወቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

26 June 2021, 16:33