ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የስደተኞችን መጠለያ በጎበኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የስደተኞችን መጠለያ በጎበኙበት ወቅት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ኢየሱስን ልናውቀው የምንችለው በድሆች ሕይወት ነው” አሉ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። “ድሆች ዘወትር ከእናንተ ጋር ናቸው” በሚል መሪ ቃል ለመላው ዓለም ክርስቲያኖች እና የዓለም መንግሥታት መሪዎች ይፋ ባደርጉት መልዕክታቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችም የድሆችን ጉስቁልና ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ በማድረጉ፣ ድሆችን መርዳት ያስፈልጋል ብለዋል። እርዳታችንን ማቅረብ የምንችለው አንዳንድ የኑሮ ልማዶችን በሚገባ ተመልክተን ድህነትን የሚያመጣ ራስ ወዳድነትን በማስወገድ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን መልዕክታቸው፣ በማር. 14:7 ላይ “ድሆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስለሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ” የሚለውን ጥቅስ አስታውሰው፣ የሚያምኑት በሙሉ ክርስቶስን ማየት፣ በእጃቸውም መዳሰስ ከፈለጉ ከወዴት እንደሚገኝ ያውቃሉ ብለው፣ ድሆች ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታይባቸው እና የእርሱን ማንነት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ለድሆች ቀዳሚ ቦታን ትሰጣለች

ር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ በማር. ምዕ. 14 ላይ በተጠቀሰው እና በቢታንያ ውስጥ ኢየሱስን በከበረ የናርዶስ ሽቶ የቀባችውን ሴት ታሪክ አስታውሰው፣ ከሐዋርያት መካከል ይሁዳ፣ ይህ ሽቶ በከንቱ መባከኑ ለምንድነው? ከሦስት መቶ ብር በላይ ተሽጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበር እኮ” በማለት ሴቲቱን መንቀፉን አስታውሰዋል። ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ “ይሁዳ ይህን ያለው ለድሆች በመጨነቅ ሳይሆን ገንዘቡን በእርሱ ዘንድ የምታስቀምጡ ከሆነ ሊሰርቃችሁ ፈልጎ ነው” ማለቱን አስታውሰዋል። “ኢየሱስ ግን ‘ተውአት፣ ስለምን ታስጨንቋታላችሁ? እርሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ፣ እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እዚህ አልገኝም’” ማለቱን አስታውሰው፣ “የድሆችን መከራ የማይረዱ በርካታ ሰዎች የኢየሱስን ትምህርት ይክዳሉ፣ ደቀ መዛሙርቱም መሆን አይችሉም” ብለው፣ ቤተክርስቲያን ለድሆች ቀዳሚ ቦታን የምትሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የድሆች ቁጥር ጨምሯል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ምንም እንኳን ወረርሽኙ ብዙዎችን ለመከራና ለሞት አሳልፎ ባይሰጥም ድህነትን እንደሚጨምር ገልጸው በሚቀጥሉት ወራት የድሆች ቁጥር የሚጨምር መሆኑንም ገልጸዋል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በዚህ የተነሳ የድህነት ሕይወት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የዕለት ምግባቸውንም ማግኘት ያልቻሉ መሆኑን አስርድተዋል።

ፈጣን መፍትሄን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ ከመፍትሄዎቹ መካከል ቀዳሚው የለግል ጥቅም ከመሽቀዳደም ይልቅ ወረርሽኙን ከዓለም ገጽ ለማስወገድ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሥራ አጥነት አንዱ ችግር መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው በርካታ የቤተሰብ መሪዎች፣ ወጣት ሴቶች እና ወንዶች በሥራ እጦት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። በማኅበረሰቡ መካከል እኩል መብት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው የተነሳ ሴቶች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አስታውሰው፣ በወንጌላት እንደተጠቀሰው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታሪክ፣ ሴቶች ቀዳሚ ተዋንያን መሆናችውን አስታውሰዋል።

ድህነት የራስ ወዳድነት ውጤት እንጂ የመጨረሻ ፍሬ አይደለም

ያልተመጣጠነ የኑሮ ልማድ እና ራስ ወዳድነት ለድህነት መስፋፋት ምክንያት መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህም በድሆች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫናን እንደሚያስከትል አስረድተው፣ “ድህነት የተመኙት የመጨረሻ ውጤት ሳይሆን የራስ ወዳድነት ወይም የስግብግብነት ውጤት ነው” ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባስተላለፉት ጥብቅ መልዕክታቸው፣ ጠቃሚ የሆኑ ማኅበራዊ ሞዴሎችን በመከተል፣ በዓለም ላይ የተከሰቱትን አዳዲስ የድህነት ዓይነቶችን በመጪዎቹ አሥርተ ዓመታት ውስጥ መታገል የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ድህነትን ለመቅረፍ ከማሰብ ይልቅ የድሆችን ቁጥር መገመት ይቀለናል ብለው፣ “ድህነት በተቃራኒው፣ የፈጠራ እቅዶችን ተግባራዊ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል” ብለዋል።

ዕርዳታን መስጠት ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት መጋራት ያስፈልጋል

ኢየሱስ ክርስቶስ በማር. ምዕ. 14 ላይ “ድሆች ዘወትር ከእናንተ ጋር ናቸው” ያለው፣ ለሌሎች መልካም ማድረግ የምንችልበት ዕድል እንዳያመልጠን ማሳሰቡን ቅዱስነታቸው አስረድተው፣ “ለድሆች አንድ ጊዜ በምንሰጠው ዕርዳታ ከመርካት ይልቅ ዕርዳታችን ዘላቂነት ያለው፣ ልዩነትን የሚያስወግድ እና በድሆች ጫንቃ ላይ የወደቀውን ኢፍትሃዊነት የሚያስወግድ መሆን አለበት” ብለዋል።

ክርስቶስን የምናውቀው በድሆች ሕይወት ውስጥ ነው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ላይ በኢየሱስ፣ በድሆች እና በወንጌል አገልግሎት መካከል የማይነጠል ግንኙነት መኖሩን ክርስቲያኖች ሊያውቁት ይገባል ብለው፣ የእግዚአብሔር መልክ የአባትነት እና ዘወትር ለድሆች ቅርብ መሆኑን የሚገልጽበት መሆኑን አስረድተው፣ “የኢየሱስ ሥራዎች በሙሉ እርሱ ራሱ በመካከላችን መገኘቱን የሚያሳይ ተጨባጭ ምልክት ነው” ብለዋል። ኢየሱስን በሁሉም ሥፍራ የምናገኘው ቢሆንም ከልባችን ልናውቀው የምንችለው በድሆች ሕይወት ውስጥ፣ በሚደርስባቸው ስቃይ እና ለመኖር በሚገደዱባቸው አንዳንድ ኢሰብአዊ ሁኔታዎች በኩል መሆኑን አስረድተዋል። 

ድሆችን መውደድ እንጂ መቁጠር አያስፈልግም

ር. ሊ. ጳ ፍራንችኮስ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ “ድሆች ማን እንደሆኑ እና ምን ያህል እንደሆኑ መጠየቅ ለድሆች የምሰጠውን ትኩረት ለመቀነስ ሰበብ ስለሚሆንብኝ ድሆችን በጭራሽ አልቆጠርኩም ብለው፣ ድሆችን ማቀፍ፣ መውደድ እና በዘላቂነት ሊረዱ ይገባል እንጂ መቆጠር የለባቸውም” ብለዋል።

15 June 2021, 16:23