ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ምሕረትን ከአምላክ እንደ ተቀበልን፣ እኛም ምሕረት አድራጊዎች እንሁን አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን የተነሳበት የትንሳሄ በዓል በመጋቢት 26/2013 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ይህ የትንሳኤ በዓል ከተከበረ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ደግሞ እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ ሞት እና ትንሳሴ አማካይነት ለእኛ ለሰው ልጆች ሁሉ ያደረገው ምሕረት የሚታወስበት “የመለኮታዊ ምሕረት” እለተ ሰንበት በሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ የመለኮታዊ ምሕረት ሰንበት በሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ምሕረትን ከአምላክ እንደ ተቀበልን፣ እኛም ምሕረት አድራጊዎች እንሁን ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ከሞት የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለበርካታ ጊዜያት ለደቀ መዛሙርቱ ታየ። በጭንቀት ተውጦ የነበረውን  ልባቸውን በትዕግስት አረጋጋ። እርሱ ራሱ ከሞት ከተነሳ በኋላ አሁን ደግሞ “ለደቀ መዛሙርቱ ትንሣኤ” ያመጣል። እሱ መንፈሳቸውን ከፍ ያደርገዋል እና ህይወታቸውን ይለውጣል። ቀደም ሲል የጌታ ቃላት እና እርሱ ያሳያቸው ምሳሌዎች እነሱን ለመለወጥ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። አሁን በፋሲካ አንድ አዲስ ነገር ይከሰታል ፣ ይህም የሚከሰተው በምህረት ብርሃን ውስጥ ነው። ኢየሱስ በምሕረት አሳድጓቸዋል። ያንን ምህረት ከተቀበሉ በኋላ እነሱ ራሳቸው በተራቸው ምሕረት በማዳረግ ይኖራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ምሕረትን የተቀበልኩበት ተሞክሮ ከሌለኝ መሐሪ መሆን ከባድ ነው።

በመጀመሪያ በሶስት ስጦታዎች አማካይነት ምህረትን ይቀበላሉ። በመጀመሪያ ኢየሱስ ሰላምን ፣ ከዚያም መንፈስን እና በመጨረሻም ቁስሎቹን ይሰጣቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ ተበሳጭተው ነበር። በፍርሃት ፣ በቁጥጥር ስር እንዳይውሉ እና ፍጻሜያቸው እንደ ጌታቸው እንዳይሆን ስለፈሩ በቤት ውስጥ በር ቆልፈው ተዘግተው ነበር። ነገር ግን እነሱ በአንድ ክፍል ውስጥ አንድ ላይ ተሰብስበው ብቻ የነበሩ ሳይሆን እነርሱም በበኩላቸው በራሳቸው ጸጸት ተውጠው ነበር። ኢየሱስን ብቻውን ትተው እና ክደውት ነበር። አቅመ ቢስ፣ የተጣሉ ፣ ለምንም ጥሩ የማይጠቅሙ እንደ ሆኑ ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ኢየሱስ ደርሶ ሁለት ጊዜ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እሱ ችግሮቻችንን ማስወገ የሚችል  ሰላምን አያመጣም ፣ ነገር ግን በውስጣችን መተማመንን የሚያመጣ ሰላምን ነው የሚሰጠን። የውጫዊ ሰላም ሳይሆን የልብ ሰላም ነው የሚሰጠን። እርሱም “ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን! አብ እንደ ላከኝ እኔም ደግሞ እናንተን እልክላችኋለሁ ”(ዮሐ 20፡21) “በእናንተ ስለተማመንኩኝ እልካችኋለሁ” እንደ ማለት ነው። እነዚያ ተስፋ የቆረጡ ደቀ መዛሙርት ከራሳቸው ጋር በሰላም ተገኙ። የኢየሱስ ሰላም ከንስሐ ወደ ተልዕኮ እንዲተላለፉ አድርጓቸዋል። የኢየሱስ ሰላም ተልዕኮን ያነቃቃል። ኢየሱስ የሚሰጠን ሰላም እፎይታ እና ማጽናኛን ብቻ የሚያመጣልን ሰላም ሳይሆን፣ ነገር ግን ከእራሳችን ለመላቀቅ የምናደርገውን ፈታኝ ጎዞ ያቃልልልናል። የኢየሱስ ሰላም ሽባ ከሚያደርገው በራስ ከመሳብ ስሜት ነፃ ይወጣል፤ ልብ እንዲታሰር የሚያደርጉትን እስራቶችን ይሰብራል። ደቀመዛሙርቱ ምህረት እንደተደረገላቸው ተገነዘቡ - እግዚአብሔር እነሱን እንዳልኮነነ ወይም ዝቅ እንደማያደርግ፣ ይልቁኑ በእነሱ እንዳመነ ተገነዘቡ። እግዚአብሔር በእውነቱ እኛ በራሳችን ከምንተማመን በላይ በእኛም ያምናል። እኛ ራሳችንን ከምንወደው በተሻለ ሁኔታ እርሱ ይወደናል። እግዚአብሄር እንደ ሚያምነው በእርሱ ፊት ማንም ጥቅም የሌለው፣ የተናቀ ወይም የተገለለ ሰው የለም። ዛሬ ኢየሱስም እንዲሁ “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አንተ በዓይኔ ውስጥ ውድ ነህ። ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን! እናንተ ለእኔ አስፈላጊ ናችሁ። ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን! ተልእኮ ትቀበላላችሁ። ማንም ቦታዎን ሊወስድ አይችልም። ምትክ የለህም። እኔ በአንተ አምናለሁ ” ይለናል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን በመስጠት ምህረትን አሳይቷል። ለኃጢአት ይቅርታ መንፈስን ሰጠ (ዮሐንስ 20፡ 22-23)። ደቀ መዛሙርቱ ጥፋተኞች ነበሩ፤ ሸሽተው ነበር ፣ ጌታቸውን ትተውት ሂደዋል። ኃጢአት ሥቃይን ያመጣል፣ ክፋት ዋጋ ያስከፍላል። ኃጢአታችን ዘማሪው እንዳለው (መዝሙር 51፡5) ሁል ጊዜ ከፊታችን ነው። እኛ ከራሳችን ፣ ማስወገድ አንችልም። ከችግራችን ጥልቅ ውስጥ እንድንወጣ ሊያደርገን የሚችለው የእግዚአብሔር ምሕረት ብቻ ነው፣ የሚፈውሰን የእርሱ ምህረት ብቻ ነው። እንደ እነዚያ ደቀመዛሙርት ከልባችን የጌታ ምህረትን ለመጠየቅ ይቅር እንድንባል ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። ይቅር እንዲለን ልባችንን መክፈት ያስፈልገናል። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ይቅርታን መቀበል ማለት በውስጣችን ትንሳኤን የሚያነቃቃ የፋሲካ ስጦታ ነው። ያንን ስጦታ ለመቀበል ፣ የይቅርታ ምስጢር የሆነውን ምስጢረ ንስሐ በሕይወታችን ለመለማመድ  እና ምሕረቱን ለመቀበል ጸጋውን እንለምን። መናዘዝ ስለራሳችን እና ስለ ኃጢአታችን ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር እና ስለምህረቱ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። ለመነሣት እንጂ ራሳችንን ለማዋረድ አንናዘዝ። እኛ ሁላችንም ይህንን በጣም እንፈልጋለን። ልክ እንደ ትንንሽ ልጆች ፣ በወደቁ ቁጥር በአባቶቻቸው መነሳት እንደሚያስፈልጋቸው ፣ እኛ ይህንን እንፈልጋለን። እኛም በተደጋጋሚ እንወድቃለን። እናም የአባታችን እጅ እንደገና በእግራችን እንድንቆም ሊያደርገን እና እንድንራመድ ለማድረግ ዝግጁ ነው። ያ እርግጠኛ እና እምነት የሚጣልበት እጅ ምስጢረ ንስሐ ነው። መናዘዝ እኛን ከፍ የሚያደርግ ምስጢር ነው፣ በወደቅንባቸው ጠጣር ድንጋዮች ላይ እያለቀስን እንድንቆይ በምድር ላይ አይተወንም። መናዘዝ የትንሳኤ ምልክት ነው፣ ንጹህ ምህረት የምናገኝበት ሂደት ነው። ምስጢረ ንስሐን የሚያዳምጡ ሰዎች ሁሉ የምህረትን ጣፋጭነት ማስተላለፍ አለባቸው። ምስጢረ ንስሐ የሚያስገቡ ሰዎች ሁሉ ማዳረግ የሚኖርባቸው ነገር ይህ ነው - ሁሉንም ነገር ይቅር የሚል የኢየሱስን ምህረት ጣፋጭነት ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል። እግዚአብሔር ሁሉን ይቅር ይላል።

ኢየሱስ ከሚያድሰን ሰላም እና ከፍ ከፍ ከሚያደርገን ይቅርባይነት ጋር ለደቀ መዛሙርቱ ሦስተኛ የምሕረት ስጦታ ሰጣቸው-ቁስሎቹን አሳያቸው። በእነዚያ ቁስሎች ተፈወስን (1 ጴጥ 2፡24 ፤ ኢሳ 53፡5)። ነገር ግን ቁስሎች እንዴት ይድኑናል? በምህረት! በእነዚያ ቁስሎች ውስጥ ፣ እንደ ቶማስ ፣ እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር እንደወደደን እውነታውን ቃል በቃል መንካት እንችላለን። ቁስሎቻችንን የእርሱ አድርጎ የእኛን ድክመቶች በገዛ አካሉ ተሸክሟል። ቁስሎቹ በመከራችን ላይ ምህረትን በማፍሰስ በእኛ እና በእርሱ መካከል የተዘረጉ የምሕረት መንገዶች ናቸው። የእርሱ ቁስሎች እግዚአብሔር ወደ ርህራሄ ፍቅር እንድንገባ እና እርሱ ማን እንደ ሆነ በእውነት እንድንነካው የከፈታቸው መንገዶች ናቸው። ዳግም ምህረቱን አንጠራጠር። ቁስሎቹን በማክበር እና በመሳም ፣ በርህራሄ ፍቅራችን ሁሉ ድክመቶቻችን ሁሉ ተቀባይነት እንዳላቸው እንገነዘባለን። ይህ በእያንዳንዱ መስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስረዓት ላይ ይከሰታል ፣ ኢየሱስ የቆሰለውን እና የተነሳውን አካሉን እዚያው ያቀርብልናል።  እኛ እንነካዋለን እርሱ ሕይወታችንን ይነካል። ሰማይ ወደ እኛ እንድትወርድ ያደርጋታል። የእርሱ ቁስሎች ነፀብራቅ በውስጣችን የምንሸከማቸውን ጨለማ ያስወግዳሉ። እንደ ቶማስ እግዚአብሔርን እናገኛለን፣ እርሱ ለእኛ ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ እናውቃለን እናም “ጌታዬ እና አምላኬ!” ለማለት እንነሳሳለን። (ዮሐ 20፡28) ሁሉም ነገር ከዚህ የሚመነጨው ከምሕረት መቀበል ጸጋ ነው። ይህ የክርስቲያናዊ ጉዞዋችን መነሻ ነው። ነገር ግን በራሳችን ችሎታ፣ በመዋቅሮቻችን እና በፕሮጀክቶቻችን ውጤታማነት የምንተማመን ከሆነ ሩቅ አንሄድም። የእግዚአብሔርን ፍቅር ከተቀበልን ብቻ ለዓለም አዲስ ነገር ማቅረብ የምንችለው።

ደቀመዛሙርቱም ያደረጉት ያ ነው፣ ምህረትን በመቀበል እነሱ ደግሞ ምህረት አደረጉ። ይህንን በመጀመሪያው ንባብ ውስጥ እናየዋለን። የሐዋርያት ሥራ እንደ ሚነግረን “ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም”  (4፡32) በማለት ይነግረናል። ይህ ኮሚኒዝም ሳይሆን ንፁህ ክርስትና ነው። እነዚያ ቀደም ሲል ስለ ሽልማቶች እና ልዩ ስፍራ ስለማግኘት እየተከራከሩ የነበሩ እነዚያም ደቀ መዛሙርት ናቸው ብለን ስናስብ በጣም የሚያስደንቀው ነገር ነው (ማቴ 10፡37 ፣ ሉቃ 22፡24)። አሁን ሁሉንም ነገር ይጋራሉ፣ እነሱ አሁን “አንድ ልብ እና አንድ ነፍስ” ነበራቸው (የሐዋ. ሥራ 4፡32)። እንዴት እንደዚህ ያለ ለውጥ ለማምጣት ቻሉ? አሁን የራሳቸውን ሕይወት የቀየረውን ተመሳሳይ ምህረት በሌሎች ላይ ማሳየት ጀመሩ። ተልዕኮውን ፣ የኢየሱስን ይቅርታን እና የኢየሱስን አካል እንደተካፈሉ ተገንዝበዋል ፣ ስለሆነም ምድራዊ ንብረቶቻቸውን ማካፈል ተፈጥሯዊ መስሎ ታያቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲቀጥል “ከእነሱ መካከል ችግረኛ ሰው አልነበረም” (የሐዋርያት ሥራ 4፡34) በማለት ይናገራል። ፍርሃታቸው የጌታን ቁስሎች በመንካት ተሽሮ ነበር ፣ እናም አሁን በችግረኞች ላይ የሚደርሰውን ቁስለት ለመፈወስ የማይፈሩ ናቸው። ምክንያቱም እዚያ ኢየሱስን ያዩታል ። ምክንያቱም ኢየሱስ እዚያ ከእነሩ ጋር ነው ፣ በችግር ውስጥ ባሉ ቁስሎች ውስጥ እርሱ በእዚያ ይገኛል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እግዚአብሔር ሕይወታችሁን እንደነካ ማረጋገጫ ትፈልጋላችሁ ወይ? የሌሎችን ቁስሎች ለማሰር ጎንበስ ማለት ከቻላችሁ ይህንን ትገነዘባላችሁ። “እኔ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሰላም ፣ ምሕረቱን የተቀበልኩ ፣ ለሌሎች የምራራ ሰው እኔ ነኝ ወይ ? ብለን ራሳችንን የምንጠይቅበት ጊዜው አሁን ነው። በኢየሱስ አካል ብዙ ጊዜ ርሴን የምመግበው እኔ የድሆችን ረሃብ ለማስታገስ ማንኛውንም ጥረት አደርጋለሁ ወይ? ” ግዴለሽ እንሁን። የአንድ አቅጣጫ እምነት ፣ የሚቀበል ግን የማይሰጥ እምነት ፣ ስጦታን የሚቀበል ግን በምላሹ የማይሰጥ እምነት አይኑረን። ምሕረትን ከተቀበልን በኋላ አሁን መሐሪዎች እንሁን። ፍቅር ስለ ራሳችን ብቻ ማሰብ ከሆነ እምነት ደረቅ ፣ መካን እና ስሜታዊ ይሆናል። ያለ ሌሎች እምነት እንዲያው ሥጋ አልባ ይሆናል። ያለ ምሕረት ሥራዎች እምነት ይሞታል (ያዕ. 2፡17)። ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ በምህረቱ ኢየሱስ በሰላም ፣ በይቅርታ እና በቁስሎቹ እንዲያድሰን እንጠይቅ። የምህረት ምስክሮች እንድንሆን ጸጋውን እንለምን። በዚህ መንገድ ብቻ ነው እምነታችን ሕያው ሆኖ ሕይወታችን የተዋሃደ የሚሆነው። የምህረት ወንጌል የሆነውን የእግዚአብሔርን ወንጌል በዚህ መንገድ ብቻ እናውጃለን።

11 April 2021, 10:53