ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከሙታን የተነሳው ጌታ የማያሳፍር እርግጠኛ የሆነ ተስፋን ይሰጠናል አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ምዕመናን ዘንድ ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳሄ በዓል በመጋቢት 26/2013 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። በታላላቅ መንፈሳዊ በዓላት በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በሚከበርበት በገና በዓል እለት እና እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሳበት የፋሲካ በዓል እለት ልማዳዊ በሆነ መልኩ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በላቲን ቋንቋ “Urbi et Orbi” በአማሪኛው “ለከተማው (ሮም) እና ለዓለም”  የተሰኘ በዓላቱን አስመልክተው መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰ ክፍሎች ዘንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በመጋቢት 26/2013 ዓ.ም በተከበረበት ወቅት ይህንን በዓል ምክንያት በማድረግ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ከቫቲካን መልእክት ማስተላላፋቸው የተገለጸ ሲሆን ከሙታን የተነሳው ጌታ የማያሳፍር እርግጠኛ የሆነ ተስፋን ይሰጠናል አሉ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከእዚህ በታች ያለውን የማጫወቻ ቁልፍ ይጫኑ!

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና አህቶቼ እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሳችሁ!

ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሁሉ የምትገኘው ቤተክርስቲያን “ተሰቅሎ የነበረው ኢየሱስ እንደተናገረው ከሙታን ተነስቷል። ሃሌ ሉያ! ” የሚለውን አዋጅ እንደገና አስተጋብታለች። 

የትንሳኤው መልእክት በሙቀት ጊዜ ከመሬት ላይ እንደ ሚነሳ እንፋሎት ወይም የአስማት ቀመር አድርጎ አይገለጽም። እያጋጠመን ካለው አስቸጋሪ ሁኔታ ማምለጥን አያመለክትም። ወረርሽኙ አሁንም እየተስፋፋ ሲሆን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ አሁንም ከባድ ነው ፣ በተለይም ለድሆች።  የሆነ ሆኖ በትጥቅ የተደገፉ ግጭቶች አሁንም ቢሆን አላቆሙ፣ ወታደራዊ የጦር ዝግጅቶች አሁንም ቢሆን ጠናክረው እየቀጠሉ ይገኛሉ፣  ይህ ደግሞ አሳፋሪ የሆነ ነገር ነው።

በዚህ ውስብስብ እውነታ ፊት የፋሲካ በዓል መልእክት በእዚህ ሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ተስፋ ስለሚሰጠን ክስተት በአጭሩ ይናገራል “የተሰቀለው ኢየሱስ ተነስቷል” ይለናል። ይህ መልእክት ለእኛ የሚናገረው ስለ መላእክት ወይም ስለ መናፍስት ሳይሆን ስለ ሰው ፣ ስለ ሥጋ እና አጥንት ፣ ፊት እና ስም ስላለው ስለ ኢየሱስ ነው። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነኝ በማለቱ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ትዕዛዝ የተሰቀለው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተናገረው በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት በሦስተኛው ቀን እንደተነሳ ወንጌሉ ይመሰክራል።

የተሰቀለው ኢየሱስ እንጂ ሌላ ከሙታን ተነሳ ሌላ ማንም የለም። የማዳን ፈቃዱን ሙሉ በሙሉ ስለፈፀመ እግዚአብሔር አብ ልጁን ኢየሱስን ከሙታን አስነሳው። ኢየሱስ ድክመታችንን ፣ ቁስሎቻችንን፣ ሞታችንን እንኳን ሳይቀር ወስዶ ራሱ ተሸከመው። እርሱ መከራችንን ታግሶ የኃጢአታችንን ክብደት ተሸከመ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አብ ከፍ ከፍ አደረገው እናም አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ይኖራል፣ እርሱ ጌታ ነው።

ምስክሮቹ አንድ አስፈላጊ የሆነ መረጃ ይዘረዝራሉ-ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በእጆቹ ፣ በእግሮቹ እና በጎኖቹ ላይ የነበሩትን የቁስል ምልክቶች ተመልክተዋል። እነዚህ ቁስሎች ለእኛ ያለው ፍቅር የዘላለም ማኅተም ናቸው። በአካል ወይም በመንፈስ አሳማሚ የሆነ ፈተና ያጋጠማቸው ሁሉ በእነዚህ ቁስሎች ውስጥ መጠጊያ ማግኘት ይችላሉ ፣ እናም በእነሱም የማያሳዝን የተስፋ ጸጋን ይቀበላሉ።

ከሞት የተነሳው ክርስቶስ በወረርሽኙ እየተሰቃዩ ለሚገኙት ሁሉ በሽተኞችም ሆኑ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች ተስፋ ነው። ጌታ መጽናናትን ይስጣቸው እንዲሁም የዶክተሮችን እና የነርሶችን ብርቱ ጥረት ያጠናክር። እያንዳንዱ ሰው ፣ በተለይም በመካከላችን በጣም ተጋላጭ የሆነው ሰው እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን አስፈላጊ እንክብካቤ የማግኘት መብት አለው። ሁላችንም ወረርሽኙን ለመዋጋት በተጠራንበት በእነዚህ ጊዜያት ይህ የበለጠ ግልፅ ነው። ክትባቶች በዚህ ትግል ውስጥ አስፈላጊ መሳሪያ ናቸው። መላው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዓለም አቀፍ ኃላፊነት መንፈስ የክትባቶችን ስርጭት መዘግየትን በማስወገድ ስርጭቱን በተለይም በድሃ ሀገሮች ላይ ለማመቻቸት ቁርጠኛ እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ።

የተሰቀለው እና ከሞት የተነሳው ጌታ ከሥራ ለተፈናቀሉ ወይም ከባድ የኢኮኖሚ ችግሮች ላጋጠሟቸው እና በቂ ማህበራዊ ጥበቃ የሌላቸውን ሰዎች ያጽናና። የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሁሉም ሰው በተለይም በጣም የተቸገሩ ቤተሰቦች ለተስተካከለ የኑሮ ደረጃ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንዲያገኙ ከሙታን የተነሳው ጌታ ያነሳሳቸው። የሚያሳዝነው ግን ወረርሽኙ የድሆችን ቁጥር እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተስፋ መቁረጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።

“የሁሉም ዓይነት ድህነት ተስፋ በድጋሚ እንዲለመልም አንድ ጊዜ በድጋሚ በአዲስ መልክ መጀመር ይገባል”። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሃይቲ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እነዚህን ቃላት ተናግረው ነበር። በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሀሳቤ የሚመላለሱት ተወዳጅ የሆኑ የሃይቲ ህዝቦች ናቸው። በችግሮች እንዳይዋጡ ፣ የወደፊቱን በልበ ሙሉነት እና በተስፋ እንዲመለከቱ አሳስባቸዋለሁ።

ከሞት የተነሳው ኢየሱስም ትምህርት ቤት ወይም ዩኒቨርስቲ ሂደው ሳይማሩ ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ እንዳያሳልፉ ለተገደዱት ወጣቶች ሁሉ ተስፋ ነው። በበይነ መረብ አማካይነት በሚደረጉ ግንኙነቶች ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ሰብአዊ ግንኙነቶችን መለማመድ ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ነገር ነው ፣ በተለይም የአንድ ሰው ባህሪ እና ስብዕና በሚፈጠርበት በወጣትነት ዕድሜ ላይ። ጥላቻን በፍቅር ብቻ ማስወገድ እንደሚቻል በማወቅ በዓለም ዙሪያ ለወጣቶች ያለኝን ቅርበት እገልጻለሁ ፣ በእነዚህ ቀናት በተለይም ዴሞክራሲን ለመደገፍ እና ድምፃቸውን በሰላም ለማሰማት ለሚያምኑ ወጣቶች ያለኝን አጋርነት ለመግለጽ እወዳለሁ።

ጦርነት እና ከፍተኛ ድህነትን ሸሽተው ለሚሰደዱ ስደተኞች የዳግም ልደት ምንጭ የሆነው የኢየሱስ ብርሃን ይከተላቸው። ወደ ቀራንዮ በሚወስደው መንገድ ላይ ሲራመድ የነበረውን የጌታን የተበላሸ እና በመከራ የተጎሳቆለ ፊት በፊታቸው ላይ ተመልክተን እንለይ። በእነዚህ ቀን የምናከብረው በሞት ላይ የሕይወት ድል ያደረገበት ቃል የሚገቡ ተጨባጭ የአብሮነት እና የሰው ልጅ ወንድማማችነት ምልክቶች በጭራሽ አይጉደልባቸው። እየተሰቃዩ የሚገኙ እና መጠጊያ የሚፈልጉ ሰዎችን በልግስና እየተቀበሉ የሚገኙ አገሮችን አመሰግናለሁ። በተለይ በሶሪያ እየተከሰተ የሚገኘውን ግጭት በመሸሽ እየተሰደዱ የሚገኙ በርካታ ስደተኞችን እየተቀበሉ የሚገኙትን ሊባኖስ እና ዮርዳኖስ ማመስገን እፈልጋለሁ።

በችግር እና ያለመተማመን ጊዜያት ውስጥ እያለፈ ያለው የሊባኖስ ህዝብ የትንሳኤው ጌታ መፅናኛ ይከተላቸው ዘንድ እየተመኘሁኝ፣ አብሮ የመኖር እና የብዙሃነት ሀገር እንድትሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርባለሁ።

ሰላማችን ክርስቶስ በመጨረሻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ኢ-ሰብዓዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በሚኖሩባት በተወደደች እና በጦርነት በምትታመሰው ሶሪያ በጦር መሳሪያ አማካይነት እየተደርጉ የሚገኙ ፍጥጫዎች ያበቁ ዘንድ፣ ኢሰባዊ በሆነ መልኩ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ በሚገኙባት የመን፣ ይህችን አገር በተመለከተ እየተደረገ ያለው አሳፋሪ ዝምታ ምክንያት እየታመሰች በምትገኘው አገር ውስጥ ሰላም ይመጣ ዘንድ፣ በሊቢያ ውስጥ በመጨረሻ ለአስር ዓመታት ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ጦርነቶች ወደ ማብቂያቸው ሊመጡ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ግጭቶችን ለማስቆም እና በጦርነት የደከሙ ህዝቦች በሰላም እንዲኖሩ እና አገራቸውን መልሶ መገንባት እንዲጀምሩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉም በብቃት ይሳተፉ ዘንድ ጥሪ አቀርባለሁ።

የትንሳሄው በዓል በተፈጥሮው ወደ ኢየሩሳሌም ይወስደናል። በኢየሩሳሌም ላይ ጌታ ሰላምን እና ደህንነትን እንዲያመጣ እንጠይቃለን (መዝ 122) ፣ ስለሆነም ሁሉም እርስ በርሳቸው እንደ ወንድም እና እህቶች የሚገናኙበት ፣ እስራኤል እና ፍልስጤማውያን እንደገና የሚታወቁበት የመገናኛው ቦታ እንድትሆን የምታቅርበውን ጥሪ እንቀበል፣ ሁለቱ ክልሎች በሰላምና በብልፅግና ጎን ለጎን እንዲኖሩ የሚያስችለውን የተረጋጋ መፍትሄ ላይ ለመድረስ የውይይት ኃይል አስፈላጊ ነው።

በዚህ የፋሲካ በዓል ቀን ሀሳቤም ባለፈው ወር በመጎብኘቴ ደስታን ወዳጎናጸፈኝ ወደ ኢራቅ ይመለሳል። በሰላም ጎዳና ላይ እንዲቀጥሉ እፀልያለሁ፣ እናም በዚህም ለሰብአዊ ቤተሰብ እንግዳ ተቀባይ እና ለሁሉም ልጆቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ የሚለው የእግዚአብሔርን ህልም ይፈጽማል።

በአገር ውስጥ በሚፈጠሩ ግጭቶች እና እንዲሆም በዓለም አቀፍ የሽብር መረብ በሚቃጡ ጥቃቶች ምክንያት የወደፊቱ መጻይ ጊዜያቸው አደጋ ላይ የወደቁ በተለይም በሳህል እና በናይጄሪያ እንዲሁም በትግራይና በካቦ ዴልጋዶ ክልል ውስጥ በሚገኙ የአፍሪካ ሕዝቦችን ከሙታን የተነሳው ጌታ ይደግፋቸው። ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደርገው ጥረት ለሰብአዊ መብቶችና ቅዱስ ለሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ክብር በመስጠት ቅድስና፣ በእርቅና በእውነተኛ አብሮነት መንፈስ በወንድማማች እና ገንቢ በሆነ ውይይት እንዲቀጥል ጥሪ አቀርባለሁ።

በዓለም ላይ አሁንም ብዙ ጦርነቶች እና በጣም ብዙ ሁከቶች አሉ! የጦርነትን አስተሳሰብ እንድናሸንፍ ሰላማችን የሆነው ጌታ ይርዳን። በተለይም በምስራቅ ዩክሬን እና ናጎርኖ-ካራባክ የግጭቶች የተነሳ ለእስር የተጋለጡ እስረኞች በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ እና የአለም መሪዎች በአዲስ መልክ የጦር መሳሪያን ላማጋበስ የሚያደርጉትን ውድድርን እንዲያቆሙ ከሙታን የተነሳው ጌታ ያበረታታ። በዛሬው እለት መጋቢት 26/2013 ዓ.ም የፀረ-የሰው ፈንጂዎችን በተመለከተ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ፣ በየአመቱ ብዙ ንፁሃንን የሚገድሉ ወይም የአካል ጉዳት የሚያደርሱ እና በሰው ልጆች ላይ “የጥፋት እና የሞት ስጋት ተወግዶ ሰዎች ሳይፈሩ በህይወት ጎዳናዎች ላይ አብረው እንዳይራመዱ” ተግዳሮት የሆነው አሰቃቂ አደጋ የምያስከትሉ መሳሪያዎች ይወገዱ ዘንድ ምኞቴ ነው፣ እነዚህ የሞት መሣሪያዎች ባይኖሩ ኖሮ ዓለማችን ምንኛ የተሻለች ቦታ ትሆን ነበር!

ውድ ወንድሞች እና እህቶች በዚህ አመት እንደገና በተለያዩ ቦታዎች ብዙ ክርስቲያኖች ፋሲካን በከባድ እገዳዎች ያከበሩ ሲሆን አልፎ አልፎም በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓታ ላይ መገኘት አልቻሉም። እነዚያ ገደቦች እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በአምልኮና በሃይማኖት ነፃነት ላይ ሁሉም ገደቦች እንዲነሱ እና ሁሉም ሰው በነፃነት ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ እና እርሱን እንዲያወድስ እንዲፈቀድ እንጸልያለን።

በምንጸናባቸው ብዙ ችግሮች መካከል ፣ በክርስቶስ ቁስሎች እንደተፈወስን መዘንጋት የለብንም (1 ጴጥ 2፡24)። በተነሳው ጌታ ብርሃን ፣ የእኛ ሥቃይ አሁን ተለወጠ። ሞት በነበረበት ቦታ አሁን ሕይወት አለ። ሐዘን በነበረበት ቦታ አሁን ማጽናኛ አለ። ኢየሱስ መስቀልን በማቀፍ ለስቃያችን ትርጉም ሰጠ፣ እናም አሁን የዚያ ፈውስ ጥቅሞች በዓለም ዙሪያ እንዲስፋፉ እንጸልያለን። ለሁላችሁም መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!

04 April 2021, 15:13