ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ "እኔ ወደ ኢራቅ የምሄደው፣ ወንድማማችነትን እና እርቅን በመፈለግ፣ የሰላም ነጋዲ በመሆን ነው"

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም ድረስ 33ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማደረግ ወደ ኢራቅ እንደ ሚሄዱ የሚታወቅ ሲሆን ለእዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዝግጅት ሲያደርጉ የሰላም ፣ የወንድማማችነት እና የመጽናናት መልእክት ለኢራቅ ሕዝብ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ከዛሬ ዐርብ የካቲት 26-29/2013 ዓ.ም ድረስ በኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት ትላንት ሐሙስ የካቲት 25/2013 ዓ.ም ቅዱስ አባታችን ለኢራቃውያን ባስተላለፉት መልእክት በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ደስታ እንደ ፈጠረባቸው እና በመጨረሻም ከእነሱ ጋር በአካል የመገኘትን ተስፋ ከፍ እንዳደረገው ገልጸዋል።

“በኢራቅ የምትኖሩ ውድ ወንድሞች እና እህቶች ሰላም ለእናንተ ይሁን!” በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚቀጥለው ቀን ከእናንተ መካከል እገኛለሁ፣ እናንተን ለመገናኘት፣ ፊቶቻችሁን ለማየት እና ጥንታዊ እና ልዩ የሥልጣኔ መገኛ የሆነውን ምድራችሁን ለመጎብኘት ጓጉቻለሁ” ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የቀድሞው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳስት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ በ1999 ዓ.ም መጨረሻ አከባቢ ወደ ኢራቅ ለመጓዝ አቅደው የነበረ ቢሆንም ጉዞውን ለማድረግ ግን አለመቻላቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው አሁን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ያንን ሕልም እውን የሚያደርግ እንደ ሆነም ተገልጿል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት የሦስት ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት በርካታ ከተሞችን እንደ ሚጎበኙ የተገለጸ ሲሆን እንዲሁም ከክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የሚደረግ ስብሰባዎችን ያካትታል።

የንስሐ የሰላምና የዕርቅ ነጋዲ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ከዓመታት ጦርነት እና ሽብር በኋላ ከጌታ ይቅርታን እና እርቅን ለመጠየቅ እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ ሆኜ ወደ እዚህች አገር ንግደት ለማደረግ እመጣለሁ” ያሉ ሲሆን በቅርብ ዓመታት በጦርነት ፣ በጸጥታ ችግር እና በስደት የተጎዱ ብዙ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች መኖራቸውን ገልጸው እ.አ.አ.  ከ2003 ዓ.ም በፊት በኢራቅ የነበሩ ጠንካራ ክርስቲያኖች ቁጥር ከአንድ እስከ 1.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ክርስቲያኖች በሀገሪቷ ይኖሩ እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን ነገር ግን በቅርቡ በተደረገው ጥናት መሰረት ከአስር አመታት በኋላ በኢራቅ የሚኖር የክርስቲያን ማሕበርሰብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በቁጥር በመቀነስ በአሁኑ ጊዜ ከ 300,000 እስከ 400,000 የሚሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ በአገሪቷ እንደ ሚኖሩ ተገምቷል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “እኛ ሁላችሁም ወንድማማቾች እና እህተማማቾች ነን” በማለት ይህንን ሐሳባቸውን ለማጽናት ወደ እዚያው እንደ ሚያቀኑ በመልእክታቸው የገለጹ ሲሆን በመካከላችሁ መገኘቴ እጅግ በጣም ያስደስተኛል ብለዋል። “አዎ ፣ ወንድማማችነትን ለመፈለግ የሰላም ተጓዥ ሆኜ ነው ወደ እናንተ የምመጣው፣ አብሮ ለመጸለይ እና አብሮ ለመራመድ በመጓጓት ፣ እንዲሁም ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ወንድሞችና እህቶች ጋር ፣ አባታችን በአብርሃም ሙስሊሞችን ፣ አይሁዶችን እና ክርስቲያኖችን አንድ ያደርጋል፣ ሁላችንም የአንድ ቤተሰብ ልጆች ነን” ብለዋል።

ለቤተክርስቲያን መጽናኛ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ በአስቸጋሪ ፈተናዎች መካከል በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት ለመሰከሩ ወደ ብዙ ክርስቲያኖችን ሀሳባቸውን በማዞር ለእነሱ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ አንዳንድ አባታዊ የማጽናኛ ቃላትን ያቀረቡ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ይህንን ገድል የፈጸሙትን ክርስቲያኖች ለማየት በጉጉት እጠብቃለሁ” ብለዋል። “ሰማዕት ከሆነች ቤተክርስቲያን ጋር በመገናኘቴ ክብር ይሰማኛል፣ ስለ ምስክርነታችሁ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል ብዙ ኢራቃውያን ክርስቲያን ማኅበረሰቦች አሁንም ድረስ “የፈረሱ ቤቶቻቸውን እና የፈራረሱ አብያተ ክርስቲያናት” በአገሪቷ እንደ ሚገኙ የገለጹ ሲሆን በአገሪቷ ሰማዕት የሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች እንደ ሚገኙ ገልጸው “በፍቅር በትሕትና እንድንጸና ሊረዱን” እንደሚችሉ አክለው የገለጹ ሲሆን “ለእነሱ እና ሰማዕት እየሆነች ለምትገኘው በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ ቅርብ መሆናቸውን እነርሱንም በፍቅር እንደ ሚያስቧቸው” ገልጸው በብርታት ወደ ፊት መጓዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በጣም አሳዛኝ እና የደረሰባችሁ አስከፊ ሥቃይ እንዲያሸንፋችሁ አትፍቀዱ” ሲሉ ያሳሰቡ ሲሆን “በክፉ መንፈስ ፊት ለፊት መንበርከክ በፍጹም አይገባም” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ኢራቃውያን የጥንት የጥበብ ምንጮቻቸውን እንዲጠብቁ በማበረታታት የአብርሃምን ምሳሌ አስታውሰዋል፣ ምንም እንኳን ሁሉንም ነገር ትቶ እግዚአብሔር ወደ አሳየው ስፍራ የተጓዘ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ተስፋ ሳይቆርጥ በመጓዙ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዙ ዘሮችን መውለድ መቻሉን ገልጸዋል። “ውድ ወንድሞች እና እህቶች ወደ ኮከቦች እንመልከት፣ የተገባልን ቃል አለ ”ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት አክለው ገልጸዋል።

መከራ ቢኖርም ተስፋ መቁረጥ አይገባም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባለፉት ዓመታት ለተሰቃዩ እና ሕይወታቸው በጦርነት ላለፈ ሰዎች ሁሉ የተሰማቸውን ሐዘን በመልእክታቸው የገለጹ ሲሆን በጦርነቱ ብዙ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ በተለይም ብዙ የተጎዱት የዛይዲ ማሕበረሰቦች መኖራቸውን” ገልጸዋል።ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም “ወደ የተባረከ እና የተጎዳ ምድርህ የተስፋ ነጋዲ ሆኜ ነው የምመጣው” ብለዋል። ጥፋትን ያስቀረውንና የእግዚአብሔርን ተስፋ በአዲስ መልክ ያመጣውን የዮናስን ትንቢት በነነዌ ውስጥ እናገኘዋለን” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ተስፋቸውን እንደገና እንዲገነቡ እና እንደገና እንደ አዲስ እንዲጀመሩ በሚያበረታታ በዚህ ተስፋ” ሁሉም ሰው እንዲበረታታ በመልእክታቸው የገለጹ ሲሆን ወንድማማችነታችንን ለማጠንከር እና የወደፊቱን ሰላም አብሮ በጋራ ለመገንባት በተለይም በእዚህ የኮሮና ቫይረስ በተስፋፋበት ወቅት በጋራ በአንድነት ተግዳሮቶችን መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅዱስ አባታችን መልዕክታቸውን ሲያጠናቅቁ አብርሃም ከሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የጀመረውን ጉዞ መቀጠል የእኛ ድርሻ መሆኑን፣ በሰላም ጎዳናዎች ሁሉ ላይ በአንድነት መመላለስ እንዳለብን ስለ እያንዳንዱ ሃይማኖታዊ ባህል በመገንዘብ ወንድሞችና እህቶች መሆናችንን መረዳት ይገባል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ሁላችሁም እንደ አብርሃም ተመሳሳይ ነገር እንድታደርጉ እጠይቃለሁ፣ በተስፋ መራመድ እና ኮከቦችን መመልከት በጭራሽ አታቁሙ” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የእግዚአብሔርን በረከቶች በሁሉም ላይ እንዲመጣ የተማጸኑ ሲሆን ሁሉም ሰው በጸሎት ከእርሳቸው ጋር እንዲሆን ጥሪ በማቅረብ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

04 March 2021, 10:10