ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ለመቀበል በኢራቅ እየተደረጉ ካሉ ዝግጅቶች መካከል አንዱ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ለመቀበል በኢራቅ እየተደረጉ ካሉ ዝግጅቶች መካከል አንዱ  

በስቃይ እና በተስፋ መካከል የሚገኝ የኢራቅ ታሪክ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እ. አ. አ. ከ1980 ዓ. ም. ጀምሮ አራት ጦርነቶች ወደ ተፈራረቁባት ኢራቅ በመሄድ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያካሂዱ መሆናቸው ታውቋል። በኢራቅ የተካሄዱ በተለይ አራቱ ጦርነቶች የራሳቸው መለያ ቢኖራቸውም ለኢራቅ ሕዝብ እጅግ እንግዳ መሆናቸውን በጣሊያን፣ ሞዴና ክፍለ ሀገር ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ ያስረዳሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ ውስጥ እ. አ. አ በ1980 ዓ. ም. የተጀመረው የባሕረ ሰላጤው ጦርነት ለአሥር ዓመታት ከዘለቀ በኋላ ልክ የዛሬ ሰላሳ ዓመት ላይ ያበቃ መሆኑ ይታወሳል። ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ከወረዱበት እ. አ. አ 2003 ዓ. ም. በኋላ ኢራቅ ለአራት ዓመታት ያህል በእስላማዊ አሸባሪዎች እጅ መውደቋም ይታወሳል። እ. አ. አ ከ2014 ዓ. ም. ጀምሮ በእስላማዊ መንግሥት አሸባሪዎች እጅ የወደቀች ኢራቅ፣ መልስ ያልተገኘላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ያሉባት አገር ስትሆን ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፣ መሣሪያ ታጣቂ ሚሊሻዎች በአገሪቱ ውስጥ መገኘትን የሚመለከት ነበር።

ኢራቅ እና ኢራን

ላለፉት ሃምሳ ዓመታ ያህል ኢራቅ ለበርካታ ጥቃቶች የተጋለጠች እና ገና መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ያሉባት አገር መሆኗ ታውቋል። ኢራቅ ውስጥ በሚገኙት ሱኒ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና በኢራን በሚገኙ የሽያ እስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለስምንት ዓመታት ያህል መቆየቱ ይታወሳል። በሳዳም ሁሴን የተመራው እና የኢራቅ ሺያ እምነት ተከታዮችን ያስተባበረው ጦርነት የጦር ኃላቸውን በኢራን የነዳጅ ምርት ላይ እንዲያነሱ በማድረግ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ ማለፉን፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ ያስረዳሉ።

በኢራቅ የተፈጠረው ሁለተኛው ግጭት

ኢራቅ በተለያዩ ዓመታት የተለያዩ ጦርነቶችን ያስተናገደች አገር መሆኗ ሲታወቅ እ.አ.አ በ1990 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው ጦርነት ምዕራባዊያንን ያሳተፈ መሆኑን የታሪክ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ ያስታውሳሉ። ወደ እስላማዊ አገር ወደ ሆነች ኢራቅ በመዝመት በጦርነቱ የተካፈሉት የአሜሪካ ጦር ኃይሎች መሆናቸውን ያስተወሱት ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ፣ ይህ ድርጊት የእስልምና እመነትን ለምትከተል ኢራቅ ከፍተኛ ኪሳራን እና የባሕል ውድቀትን እንዳስከተለባት የሚታሰብ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያናገራሉ። ከአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጋር የተካሄደው ጦርነት በኢራቅ ሕዝብ እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን በማስከተል በተለይም በጤና ተቋማት ላይም ከፍተኛ ጥፋትን ያስከተለ መሆኑን ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ አስረድተው፣ በጦርነቱ ወቅት የተጠቀሟቸው የጦር መሣሪያዎች እና ፈንጂዎች በርካታ ሕጻናትን ለካንሰር ሕመም በመዳረግ ለሞት እንዲበቁ ምክንያት የሆናቸው መሆኑን ገልጸዋል።  

እ. አ. አ የ 2003 ጦርነት

21ኛው ክፍለ ዘመን ሳዳም ሁሴንን ከስልጣን በማስወገድ የተገባደደ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ፣ በኢራቅ ውስጥ የሚገኘውን ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ክምችን ምክንያት በማድረግ የተቀሰቀሰው አመጽ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በተለይም የአሜሪካን መንግሥት ለጦርነት ያነሳሳው ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ ሳዳም ሁሴንን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከስልጣን ለማውረድ የታለመ መሆኑ ታውቋል። ይህ ጦርነትም በኢራቅ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ቁስልን በመፈጠር ለተቀረው አረብ አገራትም በመትረፍ፣ እ. አ. አ በ2014 ዓ. ም. ለተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ እስከ ዛሬ ድረስ በኢራቅ ውስጥ እስካሁን ያልተፈቱ መጠነ ሰፊ ችግሮችን አስከትሏል።

በኢራቅ ውስጥ አሸባሪነት ስለ መስፋፋት

እ. አ. አ. ከ2003 – 2014 ዓ. ም. የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በኢራቅ ውስጥ ለተከሰተው ከፍተኛ ድህነት ምክንያት ከመሆኑ በላይ ኢራቅ ከተቀረው ዓለም ተለይታ እንድትቀር አድርጓታል። በአገሪቱ ውስጥ የእርስ በእርስ አመጽ መስፋፋቱ ጥላቻን በማሳደግ በኢራቅ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ያሉት ኩርዶች፣ የሺአ እና የሱኒ እምነት ተከታይ ሕዝቦች አስ በእርስ ተቻችለው ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት እና የቆየ ታሪክ እንዲሸረሸር አድርጎታል። ይህ በመሆኑ ኢራቅ ራሷን የማስተዳደር አቅሟ በመዳከሙ በባዕዳን አገሮች እየተመራች ሕዝቦቿም በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጓታል። ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆነው እ.አ.አ 2014 ዓ. ም. አቡ ባካር አል ባግዳዲ የተባሉ ሰው ስልጣንን በመያዝ እስላማዊ ግዛት እና አስተዳደር በአካባቢው በስፋት ለመዘርጋት ያቀዱት ርዕዮተ ዓለም ከፍተኛ ተቃውሞን በማስነሳት በኢራቅ ሕዝብ መካከል ጥላቻን በመቀስቀስ ለእርስ በእርስ ጦርነት እንዲነሳሱ ያደረጋቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ አስረድተው፣ እ.አ.አ ከ2014 እስከ 2017 ድረስ የተካሄደው ጦርነት በአገሪቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች እና ሙዜሞች እንዲወድሙ ማድረጉን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት

በኢራቅ ሕዝብ መካከል በግልጽ የሚታይ የረጅም ጊዜ ስቃይ፣ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ምክንያት መሆኑን ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በኢራቅ ውስጥ የአብርሐም ምድር የሆነችውን ኡርን የሚጎበኟት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ትላልቅ የሐይማኖት ተቋማትን በማስተባበር በጋራ ድምጽ ጦርነትን እንዲቃወሙ የሚያደርግ እና እስካሁን ካደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ሁሉ የበላይ እና ተጠቃሽ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ፕሮፌሰር ጃኒ ላ ቤላ ተናግረዋል። 

02 March 2021, 22:14