ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚአብሔር ሁል ጊዜም የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ ማወጅ እና ማስታወስ አለብን” አሉ!

ርዕሰ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሰሜን አሜሪካ በሎስ አንጀለስ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዘጋጅነት ለ 2021 ዓ.ም የሃይማኖት ትምህርት ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቅርቡ እ.አ.አ በ2021 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ በሎስ አንጀለስ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተናጋጅነት እ.አ.አ ለ 2021 ዓ.ም የሃይማኖት ትምህርት ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል። ይህ ዓመት የኮንግረሱ 65 ኛ ዓመት እና የወጣቶች ቀን 50 ኛ አመት በአገረ ስብከት ደረጃ የሚከበርበት ወቅት ነው። በአሜሪካ ዙሪያ የሚገኙ 56 ተጋባዥ እንግዶች በኮንፈረንሱ ላይ እንደ ሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስ ወንጌልን በማወጅ ፣ ለፍትህ ድምጻቸውን በማሰማት እና ሌሎችን በማገልገል የቤተክርስቲያን አባላትን ለማነሳሳት እና ለመለወጥ ተስፋ የተጣለበት ኮንፈረንስ እንደ ሆነም ተነግሯል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ በቫቲካን

የዘንድሮው የሃይማኖት ትምህርት ኮንግረስ ተሳታፊዎች “ተስፋውን አውጁ!” በሚል መሪ ሀሳብ ላይ ውይይት እያደረጉ እንደ ሚገኙ ተገልጿል። ህይወታችን እና ዓለማችን በእግዚአብሔር ተስፋ የተደገፉ መሆናቸውን ለማመን ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ጥሪ እና ግብዣ የሚያቀርብ ኮንፈረንስ እንደ ሚሆን ከወዲሁ ይጠበቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኮንግረሱ መጀመሪያ ላይ በበይነ መረብ አማካይነት በእስፓኒሽ ቋንቋ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት “የእግዚአብሔር ተስፋ እንዳለን እና እግዚአብሔር ሁል ጊዜም የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ ማወጅ እና ማስታወስ አለብን ” ብለዋል።

በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ እያንዳንዱ ሴት እና ወንድ “ለአዳዲስ ግንኙነቶች ፣ ምሁራዊ ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ኃይሎች ተስፋን እንደሚያመጣ” በመልእክታቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በተከሰተው ወረርሽኝ እና በሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት ዓለም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ጊዜዎችን በማሳለፍ ላይ እንደ ምትገኝ የገለጹ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ይህ በበይነ መረብ አማካይነት በቪዲዮ የሚደርገው ኮንፈረንስ ተስፋ በመቁረጥ ላይ ለሚገኘው የዓለም ሕዝብ ተስፋ አንደ ሚጭር አክለው ገልጸዋል። ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ  እንዳሉት አሁን ያለው ቀውስ ተስፋ ከመሆን እና የሁሉንም ሰው ቁርጠኝነት ፣ ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት የሚስብ የወደፊቱን ጊዜ ከመመልከት ሊያግደን አይገባም ያሉ ሲሆን በወንበዴዎች ተደብድቦ በመንገድ ላይ ወድቆ የነበረው ሰው ባጋጠመው ስቃይ የተማረከውን የደጉ ሳምራዊን አብነት በመከተል የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት እርምጃ መውሰድ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

“እኛ እንደ ደጉ ሳምራዊው ሰው መስራት አለብን፣ ይህ ማለት እኔ የምመለከተው ነገር እንዲነካኝ መፍቀድ ማለት ነው ፣ ሥቃዩ እንደሚቀይረኝ እና ከሌሎች ሥቃይ ጋር መሳተፍ እንዳለብኝ ማመን ማለት ነው” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ የዘመናችን ጥሩ ሳምራውያን “ወንድማማችነትን ለማጠናቀር መቀራረብ ፣ መተሳሰብ ፣ አብሮ መኖር እና መስዋእትነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በማስተማር በህሊና እና በህብረተሰባችን ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳድረዋል” ብለዋል። ይህ እውነታ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያውጃል እና ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋል በማለት አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዲሁ ጨምረው እንደ ተናገሩት “Fratelli tutti” (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን) በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክታቸው ውስጥ እንደ ተገለጸው የወንድማማችነት መንፈስ ካልተጠናከረ በስተቀር “በጭራሽ ከእዚህ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ለመውጣት እንችልም” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን የሰው ልጅ ክብር “ወደፊት ከሚጠብቀን እና እርስ በርሳችን መረዳዳት እንዳለብን የምንረዳበት ማህበረሰብ” በመፍጠር ችግሮችን በጋራ መቋቋም እንደ ምንችል ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

በጋራ ማለም እና የወደፊቱን መመልከት አስፈላጊ ነው!”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት አክለው እንደ ገለጹት ሁላችንም የጋራ ሕልም እና የወደፊቱ ሁኔታ በተስፋ መመልከት እንደ ሚገባን የገለጹ ሲሆን ወጣቶች ተስፋ ማደረጋቸውን እንዲቀጥሉና “የአዲሱ የሰው ልጅ ውበት ፣ የወንድማማችነት እና ወዳጃዊ ውበት መሆናቸውን” እንዲገነዘቡ አበረታተዋል። ሕልሞች አንድ ላይ መገንባት አለባቸው ብለዋል "እንደ አንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ ፣ አብረን እንደ ምንጓዝ መንገደኞች፣ አንድ የጋራ መኖሪያችን የሆነ የአንድ ምድር ልጆች እንደመሆናችን መጠን እያንዳንዳችን እንደየ ቤተ እምነቶቻችን” ያለንን የጋራ እሴቶች በማዳበር ወንድማማችነትን ማጠናከር ይኖርብናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

19 February 2021, 12:30