ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ባልንጀሮቻችንን የምንከባከብ ከሆነ ይህ አዲስ አመት መልካም አመት ይሆንልናል”

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ 2020 ዓ.ም ተጠናቆ 2021 ዓ.ም ዛሬ በታኅሳስ 23/2013 ዓ.ም መጀምሩ ይታወሳል። በእዚህ እለት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች  ዘንድ አዲስ አመት እየተከበረ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ይህንን የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት” ዓመታዊ በዓል እየተከበረ ይገኛል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

ይህ አዲስ አመት እና “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት” በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ተከብሮ ማለፉ የተዘገበ ሲሆን ለእዚህ ክብረ በዓል በወጣው የቅድመ ዝግጅት እቅድ መሰረት የተካሄደውን መስዋዕተ ቅዳሴ በበላይነት እንዲመራ የታሰበው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አማካይነት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን ቅዱስነታቸው በድንገት የጀርባ አጥንት ሕመም ስላጋጠማቸው እርሳቸውን ተክተው መስዋዕተ ቅዳሴውን ያሳረጉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እንደ ነበሩ ለመረዳት ተችሏል።

በወቅቱ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቀድም ሲል በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ተዘጋጅቶ የነበረውን የእለቱን ስብከት በምንባብ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን ባልንጀሮቻችንን የምንከባከብ ከሆነ ይህ አዲስ አመት መልካም አመት ይሆንልናል ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በወቅቱ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ተክተው በጹሁፍ ያቀረቡትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

በዛሬው እለት በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የተነበቡ ንባባት ውስጥ ሶስት ግሶች ጎልተው ይታያሉ ፣ እነዚህም በእግዚአብሔር እናት ውስጥ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ሲሆን መባረክ ፣ መወለድ እና ማግኘት የተሰኙ ግሶች ናቸው።

መባረክ

በኦሪት ዘኁልቁ መጽሐፍ ውስጥ ጌታ ቅዱስ አገልጋዮቹን ሕዝቡን እንዲባርኩ ይጠይቃል እንዲህም ይላል “ እግዚአብሔር ይባርክህ፤ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፤ ይራራልህም ትላቸዋለህ (ዘኁልቅ 6፡23-24)። እሱ ሃይማኖታዊ ምክር አይደለም፣ አንድ የተወሰነ ጥያቄ ነው። እናም ዛሬም ቢሆን ካህናት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የእግዚአብሔርን ህዝብ መባረካቸው አስፈላጊ ነው ፣ እናም ምዕመኑ ሁሉ የእዚህ በረከት ተቋዳሾች እንዲሆኑ እና በተቀበሉት ቡራኬ ሌለችን እንዲባርኩ ተጠርተዋል። መባረክ እንደሚያስፈልገን ጌታ ያውቃል- ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ ያደረገው የመጀመሪያው ነገር ስለሁሉም ነገር እጅግ እንደ ተደሰተ እና ስለ እኛ በጣም በጥሩ ሁኔታ መናገር ነበር። አሁን ግን ከእግዚአብሄር ልጅ ጋር የበረከት ቃላትን ብቻ ሳይሆን በረከቱን ራሱ እንቀበላለን -ኢየሱስ የአብ በረከት ነው። በእርሱ ውስጥ ይላል ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው አብ “በበረከት ሁሉ” ይባርከናል (ኤፌ 1፡3) በማለት ይገልጸዋል። ልባችንን ለኢየሱስ በከፈትን ቁጥር የእግዚአብሔር በረከት በሕይወታችን ውስጥ ይገባል።

በጸጋው በተባረከች በእናቱ በኩል ወደ እኛ የሚመጣውን በተፈጥሮ የተባረከውን የእግዚአብሔር ልጅ ዛሬ እናከብራለን። ማርያም የእግዚአብሔርን በረከት ታመጣለች፣ እሷ ባለችበት ስፍራ ሁሉ ኢየሱስ ይመጣል፣ ስለዚህ እኛ እንደ ቅድስት ኤልሳቤጥ ልንቀበላት ያስፈልጋል፣ ወደ ቤቷ ያስገባችውን በረከቱን ወዲያው አውቃ እንዲህ አለች “ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽ ፍሬ የተባረከ ነው! (ሉቃስ 1:42)። እነዚህ ፀጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ የምንደጋግማቸው ቃላት ናቸው። ለማርያም ቦታ በመስጠታችን እንባረካለን፣ በተጨማሪም መባረክን እንማራለን። በእውነቱ እመቤታችን በረከት የምንቀበለው ለመስጠት እንደ ሆነ ታስተምረናለች። እርሷ  የተባረከችው ለሁሉም እርሷን ለሚያገኟት ሰዎች በሙሉ በረከት ነበረች፣ ለኤልሳቤጥ፣ በቃና ዘገሊላ ይኖሩ ለነበሩ አዲስ ተጋቢዎች፣ በላይኛው ክፍል ለነበሩት ሐዋርያት ...ወዘተ።  እኛም በእግዚአብሔር ስም መልካም የሆኑ ነገሮችን ብቻ እንድንናገር እና እኛም ሌሎችን እንድንባረክ ተጠርተናል። መጥፎ በመናገር እና ስለሌሎች ፣ ስለ ማህበረሰብ ፣ ስለራስ መጥፎ በማሰብ የተበከለ ዓለም ውስጥ እንገኛለን። መጥፎ ነገር መናገር ሁሉም ነገር እንዲበላሽ ያደርጋል፣ መባረክ ግን እንደገና እንዲታደስ ያደርገዋል፣ በየቀኑ በአዲስ መልክ ለመጀመር ጥንካሬ ይሰጣል። እርሷ ለእኛ እንዳለችው ሁሉ ለሌሎችም የእግዚአብሔርን በረከት በደስታ የሚሸከሙ እንዲሆኑ የእግዚአብሔርን እናት እንማጸናት።

መወለድ የሚለው ሁለተኛው ግስ ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው የእግዚአብሔር ልጅ “ከሴት የተወለደ” መሆኑን ገልጧል (ገላቲያ 4፡4)። በአጭሩ አንድ አስደናቂ ነገር ይነግረናል -ጌታ እንደ እኛ መወለዱን ይነግረናል። እሱ እንደ ትልቅ ሰው ሆኖ አልተገለጸም፣ ነገር ግን እንደ ልጅ ሆኖ መጣ፣ እርሱ ብቻውን ወደ ዓለም አልመጣም ፣ ነገር ግን ከዘጠኝ ወር በኋላ በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንዲሆን ከፈቀደው እግዚአብሄር ከሴት ተወለደ። የጌታ ልብ በማርያም ውስጥ መምታት ጀመረ፣ የሕይወት አምላክ ኦክስጅንን ከእሷ ወሰደ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ማርያም ከእግዚአብሄር ጋር ተሳሰረች፣ ምክንያቱም በእሷ ውስጥ እግዚአብሔር ከሥጋችን ጋር ስለተሳሰረ እና ከዚያ በኋላም መተሳሰሩን አላቋረጠም ወይም አልተወም። ማርያም ቅዱስ ፍራንቸስኮስ እንደ ሚናገረው  “ወንድማችንን የግርማዊ ጌታ አደረገው” ማለት ትወድ እንደ ነበረ ይናገር ነበር። እርሷ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለች ድልድይ ብቻ አይደለችም፣ እግዚአብሔር እኛን ለመገናኘት የሄደበት መንገድ ስትሆን እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ለመገናኘት መጓዝ ያለብን መንገድ ማርያም እርሷ ናት። በማርያም በኩል እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ሁነን ልንገኝ እንችላለን፣ በእርጋታ፣ በጠበቀ ቅርበት ፣ በሥጋ እርሱን በማርያም በኩል ልንገናኝ አንችላለን። አዎ ፣ ኢየሱስ ረቂቅ ሀሳብ ስላልሆነ እርሱ ተጨባጭ ነው ፣ ሰው ነው ፣ ከሴት ተወልዶ በትዕግስት አድጓል። ሴቶች የእዚህን ሁኔታ ተጨባጭነት ያውቃሉ እኛ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ረቂቅ ነን፣ እናም ወዲያውኑ አንድ ነገር እንፈልጋለን። ሴቶች ተጨባጭ ናቸው፣ እናም የሕይወትን መስመር በትዕግስት እንዴት በማለፍ እንደሚሸለሙ ያውቃሉ። ስንት ሴቶች ፣ ስንት እናቶች በዚህ መንገድ ይወልዳሉ፣ እንደገና ይወለዳሉ ሕይወት ለአለም እና ለመጪ ጊዜ ይሰጣሉ!

እኛ በዓለም ውስጥ የምንኖረው ለመሞት ሳይሆን ህይወትን ለማመንጨት ነው። በዙሪያችን ላሉት ነገሮች ሕይወት ለመስጠት የመጀመሪያው እርምጃ በውስጣችን መውደድ መሆኑን ቅድስት የእግዚአብሔር እናት ታስተምረናለች። እሷ የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚናገረው “እርሷ ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር” (ሉቃስ 2፡19)። እናም ጥሩ ነገር የሚወለደው ከልብ ነው - ልብን በንጽህና መጠበቅ ፣ የውስጥ ህይወትን መጠበቅ ፣ ጸሎትን መለማመድ ምን ያህል አስፈላጊ ነው! ልብን ለመንከባከብ ፣ ሰዎችን እና ነገሮችን ለመንከባከብ ማስተማር ምን ያህል አስፈላጊ ነው። ሁሉም የሚጀምረው ከዚህ ነው ፣ ሌሎችን መንከባከብ፣ ዓለምን፣ ፍጥረታትን መንከባከብ። እኛ ካልተንከባከብናቸው ብዙ ሰዎችን እና ብዙ ነገሮችን ማወቅ አንችልም። በዚህ ዓመት ዳግመኛ መወለድን እና አዲስ ሕክምና እንደ ሚመጣ ተስፋ እያደረግን ፣ የሚመጣውን ፈውስ ችላ አንልም። ምክንያቱም ለሰውነት ከሚሰጠው ክትባት በሻገር ልባችንም ክትባት ያስፈልገዋል፣ እናም ይህ ክትባት ፈውስ ያመጣል። እመቤታችን ከእኛ ጋር እንዳደረገችው ሁሉ ሌሎችን የምንከባከብ ከሆነ ጥሩ አመት ይሆናል።

ሦስተኛው ግስ መፈለግ የሚለው ነው።

ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚናገረው እረኞቹ “ማርያምንና ዮሴፍን እና ሕፃኑን አገኙ” ይላል (ሉቃስ 2፡16)። ቀለል ያለ ቤተሰብ እንጂ ምንም አስገራሚ እና አስደናቂ ምልክቶች አላገኙም ነበር። እዚያ ግን በእውነቱ በትንሽነት ታላቅነት ፣ ርህሩ ነገር ግን ጠንካራ የሆነውን እግዚአብሔርን በእውነት አገኙ። ነገር ግን እረኞቹ ይህንን የማይታይ ምልክት እንዴት አገኙት? እነሱ የተጠሩት በመልአክቶች ነበር። እኛ በጸጋ ካልተጠራን በስተቀር እኛም እግዚአብሔርን አናገኝም ነበር። እንደዚህ ዓይነት ከሴት የተወለደ እና በታሪክ በለሆሳስ ለውጥ የሚያመጣውን አምላክ መገመት አቃተን ፣ ግን በጸጋ አገኘነው። እናም የእርሱ ይቅርታ ዳግም እንድንወልድ እንደሚያደርግ ፣ መጽናናቱ ተስፋን እንደሚያበራ እና የእርሱ መገኘት የማይቀለበስ ደስታን እንደሚሰጠን አውቀናል። አገኘነው ግን በዐይኑ እንዲያየን ማድረግ አለብን። በእርግጥ ጌታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ብቻ አልተገለጠለንም፣ ነገር ግን በየቀኑ ሊገኝ ይገባል። ስለዚህ ቅዱስ ወንጌል ሁል ጊዜ በፍለጋ ፣ በእንቅስቃሴ ላይ ስለነበሩት እረኞች ይገልጻል “እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ፣ እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ” (ሉቃስ 2፡16-17፣20)። እነሱ ፈዛዦች አልነበሩም ፣ ምክንያቱም ጸጋን ለመቀበል አንድ ሰው ንቁ ሆኖ መቆየት አለበትና።

እናም በዓመቱ መጀመርያ ላይ ምን ለማግኘት ተጠርተናል? ለአንድ ሰው ጊዜ ማግኘቱ ጥሩ ይሆናል። ጊዜ ሁላችንም ያለን ሀብት ነው ፣ ነገር ግን ቅናት አለብን፣ ምክንያቱም ለራሳችን ብቻ ልንጠቀምበት እንፈልጋለንና። ጊዜን የማግኘት ጸጋ መጠየቅ ያለብን፣ ለእግዚአብሄር እና ለጎረቤቶቻችን፣ ብቻቸውን ለሆኑት ፣ ለሚሰቃዩት ፣ ለመደመጥ እና እንክብካቤ ለሚፈልጉ ሰዎች ጊዜ መስጠት ይኖርብናል። ለመስጠት ጊዜ ካገኘን እንደ እረኞቹ መደነቅ እና ደስተኞች እንሆናለን። እግዚአብሔርን በጊዜው ያመጣችው እመቤታችን ጊዜያችንን እንድንሰጥ ትርዳን። ቅድስት የእግዚአብሔር እናት አዲሱን ዓመት ለአንቺ በአደራ እንሰጣለን። አንቺ በልብ ውስጥ ነገሮችን እንዴት ማሰላሰል እንደ ሚገባን የምታውቂ እናት ነሽና እኛም በልባችን ውስጥ ማሰላሰል እንችል ዘንድ እርጂን። ጊዜያችንን ባሪኪ እና ለእግዚአብሄር እና ለሌሎች ጊዜ እንዲኖረን አስተምርን።  በደስታ እና በመተማመን እናመሰግንሻለን -ቅድስት የእግዚአብሔር እናት!

01 January 2021, 16:56