እ.አ.አ በነሐሴ 30/2016 ዓ.ም የዓለም የወጣቶች ቀን በፖላንድ በተከበረበት ወቅት እ.አ.አ በነሐሴ 30/2016 ዓ.ም የዓለም የወጣቶች ቀን በፖላንድ በተከበረበት ወቅት 

የር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ

“የፍራንቼስኮ ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት ያህል የሚካሄድ አንድ አውደ ርዕይ ሐሙስ ሕዳር 10/2013 ዓ.ም ይጀመራል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወጣት ኢኮኖሚስቶችን እና የሥራ ፈጣሪዎችን በማካተት፣ ዓለም አቀፋዊ የለውጥ ሂደትን ለማሳደግ በማሰብ በእርሳቸው ተነሳሽነት የሚካሄደው አወደ ርዕይ ነው። በሮም የካቶሊካዊው ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆነው አቶ ዶሜኒኮ ሮሲንጎሊ ይህንን በተመለከተ ሲናገር የጤናማ ኢኮኖሚ መሠረት ወንድማማችነት ነው ማለቱ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እምቢ ለአግላይ ኢኮኖሚ

የሰውን ሕይወት ክብር ለመጠበቅ ሲባል ‹‹አትግደል›› የሚለው ትዕዛዝ ግልጽ ገደብ እንደሚያስቀምጥ ሁሉ ዛሬ አግላይና አበላላጭ ኢኮኖሚ ‹‹አይኑር›› ማለት አለብን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ኢኮኖሚ ይገድላል፡፡ አንድ በረንዳ አዳሪ ሽማግሌ በችግር ሲሞት ዜና አይሆንም፣ የፋይናንስ ገበያ በሁለት ነጥብ ሲወድቅ ግን ዜና የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ የአግላይነት ማሳያ ነው፡፡ ሰዎች ተርበው ሳለ ምግብ ሲጣል እያየን በዝምታን እንቀጥል ወይ? ይህ የማበላለጥ ማሳያ ነው፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር በውድድር ሕግና ኃያላን አቅመ ቢሶችን መጠቀሚያ በሚያደርጉበት ‹የቻለ ይኑር› በሚያሰኝ ሥርዓት ሥር ወድቋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ብዙሃን ተገልለዋል፣ ርቀዋል፤ ያለ ሥራ፣ ያለ ተስፋና ያለ አንዳች ማምለጫ ቀርተዋል፡፡ ሰዎች እንደሸቀጥ ተቆጥረዋል፡፡ አሁን እየሰፋ የመጣ ‹‹የመጣል›› ባህል ፈጥረናል፡፡ ጉዳዩ የብዝበዛና የጭቆና ብቻ መሆኑ ቀርቶ አዲስ ነገር ሆኖአል፡፡  በመጨረሻም መገለል የምንኖርበት ህብረተሰብ አካል የመሆን ትርጉም  እንደሆነ ያሳያል፡፡ የተገለሉ ሰዎች የህብረተሰብ አካል እንኳ አይደሉም፡፡ የተገለሉ ሰዎች ‹‹የተጨቆኑ›› ሳይሆኑ የተጠሉ፣ ‹‹የተጣለ ፍርፋሪ›› ሆነዋል፡፡

በዚህ አገባብ፣ አንዳንድ ሰዎች “በነጻ ገበያ የተደገፈ የኢኮኖሚ ዕድገት በዓለም ውስጥ የተሻለ ፍትህና አሳታፊነትን ማምጣቱ አይቀርም” የሚለውን የመንጠባጠብ ንድፈ ሀሳብ መደገፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ በእውነታዎች ከቶ ያልተረጋገጠው ይህ አስተሳሰብ የኢኮኖሚ ሥልጣን በጨበጡ ወገኖች ቸርነትና ተንሰራፍቶ በሚገኘው የኢኮኖሚ ሥርዓት አሠራር ላይ ያለውን ያልተስተካከለና ገራገር እምነት ያንፀባርቃል፡፡ የተገለሉ ወገኖች ግን አሁንም በተስፋ እየጠበቁ ነው፡፡ ሌሎችን የሚያገልል የአኗኗር ዘዴ ለመከተል ወይም ያንን የራስ ወዳድነት ዓላማ ለማሳካት የሚረዳ የግድ የለሽነት ዓለም ተፈጥሮአል፡፡ ከዚህም የተነሣ ሳናስተውለው የድሆችን ጩኸት ሰምቶ የመራራት፣ የሌሎች ሰዎችን ሕመም አይቶ የማልቀስና እነርሱንም የመርዳት ስሜት እናጣለን፡፡ ይህ ሁሉ የራሳችን ሳይሆን የሌላ ሰው ኃላፊነት እንደሆነ አድርገን እንቆጥራለን፡፡ የብልጽግና ባህል ይገድለናል፤ ገበያ የምንገዛውን አዲስ ነገር ሲሰጠን እንደነቃለን፤ ተስፋ አጥተው የቀጨጩ እነዚያ ሕይወቶች አያሳስቡንም፡፡

እምቢ ለአዲስ የገንዘብ አምልኮ

ለዚህ ሁኔታ አንዱ መነሻ ምክንያት የሆነው ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ነው፤ ምክንያቱም ገንዘብ ራሳችንንና ኅብረተሰቦቻችንን እንዲቆጣጠር በጸጥታ ስለምንቀበለው ነው፡፡ የአሁኑ የፋይናንስ ቀውስ ከጥልቅ ሰብአዊ ቀውስ፣ ይኸውም፣ የሰውን ቀዳሚነት ከመካድ የመጣ የመሆኑን እውነታ እንዳናስተውል ሊያደርገን ይችላል፡፡ እኛ አዳዲስ ጣኦታትን ፈጥረናል፡፡ የጥንቱ የወርቅ ጥጃ አምልኮ (ንጽ.ዘጸ.32፡1-35) በአዲስና ስውር በሆነ መልኩ በገንዘብ አምልኮና እውነተኛ ሰብአዊ ዓላማ በሌለውና ኢ-ሰብአዊ በሆነ የኢኮኖሚ አምባገነንነት ተመልሶ መጥቷል። ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ የእነርሱን ኢ-ሚዛናዊነትና፣ ከሁሉም በላይ፣ ለሰው ልጆች ደንታ ቢስ መሆናቸውን አጉልቶ ያሳያል፡፡ ሰው ወደ ፍጆታ ደረጃ ብቻ ዝቅ ተደርጓል።

የጥቂቶች ገቢ በብዙ እጥፍ ሲያድግ በብዙሃኑና በጥቂቶች ደስተኛ ባለጸጎች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ይህ ኢ-ሚዛናዊነት የገበያ ቦታንና የፋይናንስ ግምትን ፍጹም ነጻነት በሚደግፉ ርእዮተ ዓለሞች የተፈጠረ ነው፡፡ በመሆኑም የጋራ ጥቅምን በመጠበቅ ሰበብ መንግሥታት ማንኛውንም ዓይነት ቁጥጥር የማድረግ መብት እንዳላቸው አይቀበሉም፡፡ ከዚህም የተነሣ በተናጠልና ያለመታከት የራሱን ሕጎችና ደንቦች በሌሎች ላይ የሚጭን ስውርና ብዙውን ጊዜ የማይታወቅ አዲስ የጭቆና አገዛዝ ተፈጥሮአል፡፡ የዕዳና የወለድ መከማቸትም አገሮችን የራሳቸውን ኢኮኖሚዎች እምቅ ኃይል እንዳይጠቀሙ ችግር ይፈጥርባቸዋል፡፡ ዜጎችም እውነተኛ የመግዛት አቅማቸውን እንዳይጠቀሙም  ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ላይ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያላቸውን የሙስና መንሰራፋትና ራስን የሚጠቅም የታክስ ስወራን ማከል እንችላለን፡፡ የሥልጣንና የሀብት ጥማት ገደብ የለውም፡፡ እየጨመረ የሚሄደውን ትርፍ የሚገታውን ማንኛውንም ነገር በሚበላው በዚህ ሥርዓት ውስጥ አካባቢን የመሰለ ነገር ሁሉ ብቸኛ ገዥ በሆነውና በሚመለከው ገበያ ፊት አቅም አይኖረውም፡፡

19 November 2020, 12:29