ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ድሆች ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስዱ መንገዶች ናቸው አሉ!

በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አነሳሽነት ከዛሬ አራት አመት ጀምሮ አለም አቀፍ የድሆች ቀን በመከበር ላይ እንደ ሚገኝ ይታወቃል፣ በዚህም መሰረት 4ኛው አለም አቀፍ የድሆች ቀን በሕዳር 06/2013 ዓ.ም “እጆችህን ለድሆች ዘርጋ” (መጽሐፈ ሲራክ 6፡7) በሚል መሪ ቃል በመላው ዓለም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም ተከብሮ ያለፉትን አለም አቀፍ የድሆች ቀን እንደ ሚከተለው በአጭሩ እናስቃኛችዋለን ተከታተሉን።

አንደኛው ዓለም አቀፍ የድኾች ቀን በሕዳር 08/2009 ዓ.ም  በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “አባታችን ሆይ!” የሚለው ጸሎት የድኾች ጸሎት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው እኛ ሁላችን አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት “አባታችን ሆይ” በማለት ሁላችንም የአንዱ የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን በመግለጽ አባት ለልጁ እንደ ሚያደርገው ሁሉ “‘የዕለት እንጀራችንን ስጠን’ ብለን እንደ ምንጠይቀው እና እርሱም እንደ ሚሰጠን ሁሉ እኛም በየጎረቤቶቻችን እና በእየአከባቢዎቻችን የሚገኙ ርዳታ ፈላጊ ድኾች የእኛን እገዛ ፈልገው በሚማጸኑን ወቅት ሁሉ ካለን ማካፈል ይገባናል፣ በቃላት ብቻ ሳይሆን እምነታችንን በተግባር መግለጽ ይኖርብናል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በወቅቱ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ከተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ በመቀጠል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለበርካታ ድሆች እና የእኔ ቢጤዎች የምሳ ግብዣ ተደርጎላቸው እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በሮም ከተማ እና በአከባቢው የሚገኙ የምግብ ቤቶች ሳይቀር በገዛ ፈቃዳቸው ለድሆች የነጻ የምሳ ግብዣ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በሕዳር 09/2010 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ይሆን ዘንድ የመረጡት መሪ ቃል “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው” (መዝሙር 34፡7) የተሰኘው መሪ ቃል እንደ ሆነ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው” (መዝሙር 34፡7) “እነዚህ የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ጸሐፊ  ቃላት የእኛ ቃላት ሊሆኑ የሚችሉት እኛ ራሳችን በተለምዶ ስማቸው ‘ድሆች’ ተብለው የተፈረጁ ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያጋጠሟቸውን የተለያዩ መከራዎች እና መገለሎች መቋቋም  እንዲችሉ ስናደርግ ብቻ ነው።  የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ የሚናገረው ስለመከራ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን የሚናገረው በተቃራኒው ነው። ዘማሪው ዳዊት ቀጥተኛ የሆነ የድህነት ተመክሮ የነበረው ሰው ሲሆን ይህንን የድህነት ተመክሮ እግዚኣብሔርን ማመሰገኛ ወደ ሆነ መዝሙር ይቀይረዋል። ይህ መዝሙር ዛሬ ብዙ ዓይነት ድህነት ተጠናውቶን ለምንገኝ ለእኛ እውነተኛ ድሃ ማን እንደሆነ ለመረዳት እና የእነሱን ጩኸት ለመስማት እና የእነሱን ፍላጎት ለማወቅ እንደ ተጠራን እንድንገነዘብ እድሉን ይሰጠናል” ማለታቸው ይታወሳል።

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በኅዳር 07/2012 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ለእዚህ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ቅድመ ዝግጅት ይደረግ ዘንድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 06/2012 ዓ.ም “የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም” (መዝ 9፡19) በሚል መሪ ቃል መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። ይህ አለም አቀፍ የድሆች ቀን በኅዳር 07/2012 ዓ.ም በተከበረበት ወቅት በወቅቱ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስተላለፉት መልእክት “ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሕጻናት በአዲስ መልክ በተዘረጉ በርካታ ዓይነት የባርነት ቀንበር ውስጥ እንደ ሚገኙ አምነን መቀበል መቻል ይኖርብናል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

አራተኛው አለም አቀፍ የድሆች ቀን በሕዳር 06/2013 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ በምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ተክብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን በዚህ ጹሑፍ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው ይህ አራተኛው አለም አቀፍ የድሆች ቀን “እጆችህን ለድሆች ዘርጋ” (መጽሐፈ ሲራክ 6፡7) በሚል መሪ ቃል ተክብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን ይህ አለም አቀፍ የድሆች ቀን በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ ተገልጿል፣ በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “ድሆች ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስዱን መንገዶች ናቸው” ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የዓለም ድሆች ቀን በተከበረበት ወቅት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት አክለው እንደ ገለጹት እኛ ክርስቲያኖች ይህንን ዕለት ስንዘክር እና ስናከብር ሕይወታችንን በጸሎት ፣ በበጎ አድራጎት ተግባራት እና በችግር ውስጥ ላሉትን በመርዳት የቅዱስ ወንጌልን ማዕከላዊ እሴት በተግባር ላይ በማዋል ይህንን ክርስቲያናዊ ተግባራችንን መመስከር ይኖርብናል ብለዋል።

የዓለም ድሆች ቀን እ.ኤ.አ. በ 2016 በርዕሰ ሊቀ ጳጳስ ፍራንቸስኮስ ተነሳሽነት እንዲከበር የታወጀ አለም አቀፍ ይዘት ያለው እና በየአመቱ በላቲን ስርዓተ ሊጡርጊያ ደንብ መሰረት በ 33 ኛው ሳምንት እሁድ የሚከበር አመታዊ በዓል ነው።

የዚህ ዓመት አራተኛው የአለም አቀፍ የድሆች ቀን ክስተት ነባራዊ እና አሁናዊ የሆኑ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ ሲሆን “እጃችሁን ለድሆች ዘርጋ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

ክብረ በዓሉን ለማክበር እሁድ  ዕለት ሕዳር 06/2013 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መስዋዕተ ቅዳሴ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ (ማቴ 25፡14-30) በተጠቀሰውና የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከታቸው ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ይህ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ በራሳችን ሕይወት ጅማሬ ፣ ማእከል እና መጨረሻ ላይ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ያደርጋል ብለዋል።

መጀመሪያ- የታለንት ስጦታዎች በአደራ ተሰጥተዋል

“ሁሉም ነገር የሚጀምረው ታላቅ እና መልካም በሆነ ነገር ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርእሰ ሊቀ ጳጳሱ ሕይወታችን በእግዚአብሔር ጸጋ ተጀመረ ፣ በዚህ ጊዜ እያንዳንዳችን ልዩ ልዩ ተሰጥዖዎች ተሰጥቶን ነበር ብለዋል። “እኛ ባገኘነው ነገር ላይ ሳይሆን ባለንበት ላይ የሚመረኮዝ ትልቅ ሀብት አለን ፤ የተቀበልነው ሕይወት ፣ በውስጣችን ያለው መልካም ነገር ፣ እግዚአብሄር በአምሳሉ በመፍጠር የሰጠንን የማይጠፋ ውበት እና ጤንነት” ከእግዚአብሔር ዘንድ ተሰጥቶናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አክለው እንደ ገለጹት በሕይወታችን ውስጥ የጎደሉብንን ነገሮች ለምሳሌም የተሻለ ሥራ እና ተጨማሪ ገንዘብ የማካበትን ፍላጎት እና ፈተና ማስወገድ እንደ ሚኖርብን የገለጹ ሲሆን በሕይወታችን ውስጥ ያሉትን ድንቅ ችሎታዎቻችንን በጥሩ ሁኔታ እንዳንጠቀምባቸው የሚያግደንን “ቢሆን ኖሮ” የሚሉትን ቅዤት የሚመስሉ የተሳሳቱ ቃላቶችን ማስወገድ ይኖርብናል ብለዋል።

“ጌታ” የአሁኑን ጊዜ በሚገባ እንድንጠቀም ይጠይቀናል፣ ያለፈው ጊዜ ተመልሶ እንዲመጣ መመኘት ሳይሆን አሁን ባለን ጊዜ በርትተን መሥራት ይኖርባንል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የሕይወታችን ማዕከል የአገልግሎት ሕይወት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በተጠቀሰውን ምሳሌ ዋቢ በማድረግ  በኑሮዋችን መሃከል እና በሕይወታችን ላይ “የአገልጋዮች ሥራ፣ አገልግሎት መስጠት ነው” በማለት በስብከታቸው የገለጹ ሲሆን “አገልግሎት ችሎታችን ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርግ እና ለህይወታችን ትርጉም የሚሰጥ ነው” ብለዋል፣ ለማገልገል የማይኖሩ ሰዎች፣ በሕይወታቸው ውስጥ ጥቂቱን ቢቻ እንደ ኖሩ ይቆጠራል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው እንደ ገለጹት የቅዱስ ወንጌል ታማኝ አገልጋዮች በሕይወት ዘመናቸው አደጋ ላይ የመውደቅ አዝማሚያ እንደ ሚያጋጥማቸው ግልጽ እንደ ሆነ የገልጹ ሲሆን ጥሩ አገልጋዮች ባላቸው ነገር ላይ ባለመቆየት ችሎታቸውን በጥሩ ሁኔታ ይጠቀማሉ፣ እንዲሁም ፍርሃት ወይም ጥንቃቄ የጎደላቸው አይደሉም” ስለዚህ የሚደርስባቸውን ፈተና በትዕግስት መቋቋም ይችላሉ ብለዋል።

መልካምነት በሥራ ላይ መዋል ካልቻለ በቀላሉ ልናጣው የምንችለው ጸጋ እንደ ሆነ በስብከታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው እናም የህይወታችን ታላቅነት የሚለካው በምናከናውነው ተግባር ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በምናመጣው ውጤት ወይም ፍሬ ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው፣ መልካም ከማድረግ ይልቅ ሀብት በማከማቸት ላይ ያተኮረ ሕይወት ባዶ ነው ፣ ስጦታዎች የተቀበልንበት ምክንያት እኛ ስጦታዎች እንድንሆን ነው በማለት አክለው ገልጸዋል።

 “እንግዲያውስ እግዚአብሔር እንድናገለግለው በሚፈልገው መልኩ እርሱን እንዴት ማገልገል እንችላለን?” በማለት ጥያቄ በማንሳት ስበከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በኢየሱስ ምሳሌ መሠረት ጌታው የሰጠውን ስጦታ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ከማድረግ ይልቅ፣ ጌታው በሚመጣበት ወቅት ታለንቱ (ገንዘቡ) ወለድ ያስገኝ ዘንድ በባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ መሬት ቆፍሮ እንደ ቀበረው ሰነፍ አገልጋይ መሆን የለብንም፣ የተሰጠን ስጦታ ፍሬያማ እንዲሆን የተቻለንን ሁሉ ማድረ ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጿል።

“ድሆች ዘላለማዊ ሕይወትን የሚያረጋግጡልን መንገዶች ናቸው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “አሁን እንኳን የፍቅር ሀብታም እንድንሆን ይረዱናል፣ መታገል የሚገባን እጅግ ክፉ የሆነ ድህነት  የፍቅር ድህነት ነው” ብለዋል።

ቅዱስ አባታችን አክለው ክርስቲያኖች የጎደለንን ከመጠየቅ ይልቅ እጃችንን ለድሆች በመዘርጋት ብቻ የእኛን ተሰጦታ በተሻለ መልኩ ፍሬያማ ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

መጨረሻ: ስኬት ከፍቅር ጋር

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት የኢየሱስ ምሳሌ ስለራሳችን ሕይወት ፍጻሜ በሚነግረን ነገር ላይ ተንፀባርቀዋል ያሉ ሲሆን ህይወታችን ሲያበቃ እና እውነቱ ሲገለጥ “የዚህ ዓለም አስመሳይነት፣ ስኬት ፣ ኃይል እና ገንዘብ ትርጉም ያለው ሕይወት ይሰጡናል የሚለው እሳቤ ይደበዝዛል፣ ፍቅር በተለይም ለሌሎች ያሳየነው ፍቅር ግን እውነት ሆኖ ይገለጣል፣ በእውነት ታላቅ የሕይወት ሀብት ፍቅር መሆኑን እንገነዘባለን” ብለዋል። “ደካማ የሆነ ሕይወት መኖር ካልፈለግን ኢየሱስን በድሆች ውስጥ ለማየት ፣ በድሆች ውስጥ ኢየሱስን ለማገልገል ጸጋን እንለምን” ካሉ ብለዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ አክለው እንደ ገለጹት “ኢየሱስ ቀኑን የሚጀምረው የእግዚአብሔር ስጦታዎችን ለመቀበል የሚያስችለውን ጸሎት በማድረግ እንደ ነበረ” የገለጹ ሲሆን የተቀበለው ፍቅር ፍሬ እንዲያፈራ ለማድረግ ያስችለው ዘንድ የሕይወቱ ማእከል ያድረገው የበጎ አድራጎት ተግባር ነበር፣ በእዚህ ሁኔታ ታማኝ የቅዱስ ወንጌል አገልጋይ ሆኖ አልፏል፣ እኛም ታማኝ የቅዱስ ወንጌል አገልጋዮች መሆን እንችል ዘንድ የፍቅር ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ ልንማጸነው የገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የእለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

15 November 2020, 11:26