ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሴቶች በቤተክስቲያን ውስጥ ከፍተኛ የሃላፊነት ሚና እንዲኖራቸው እንጸልይ አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የወንጌል ተልዕኮ ወር በሆነው የጥቅምት ወር፣ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፣ ምዕመናን በቤተክስቲያን ውስጥ ያላቸው የአገልግሎት ድርሻ፣ በተለይም የሴቶች የሃላፊነት ሚኖ ማደግ አለበት ብለዋል።     

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጥቅምት ወር የያዘጋጁት የጸሎት ሃሳብ በቪዲዮ ምስል ይፋ የተደረገው መስከረም 28/2013 ዓ. ም. በዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽ/ቤት በኩል መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የምዕመናን የወንጌል ተልዕኮ የሚታሰብበትን የጥቅምት ወር ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምዕመናን በወንጌል ምስክርነት ተልዕኮ ጠንካራ ተዋናይ መሆናቸውን አስረድተዋል። በተለይ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ሚና ሊያድግ እንደሚገባ እና ሰፊ የሃላፊነት ድርሻ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጥቅምት ወር የቪዲዮ መልዕክትን በማዘጋጀት የተባበሩት በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ከፍተኛ የቫቲካን ባለስልጣናት እና የቫቲካን ሚዲያ ባለሞያዎች መሆናቸው ታውቋል።

ሴቶች የሚሳተፉባቸውን የቤተክርስቲያን አገልግሎቶችን ማስፋፋት፤

ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ሰፊ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ ተሳትፎአቸው አንዳንድ ጊዜ ሲዘነጋ ይስተዋላል ብለዋል። ቅዱስነታቸው፣ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው በማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች ማሳሰባቸው ይታወቃል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት ውሳኔ፣ መቅደላዊት ማርያም በቤተክርስቲያን በዓላት እንድትታወስ እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅትም “የሐዋርያት ሐዋርያ” ተብላ እንዲትጠቀስ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህን ያደረጉትም፣ "መቅደላዊት ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን መካከል ተለይቶ ከተነሳ በኋላ በቅድሚያ ያየች በመሆኗ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በስሟ የጠራት በመሆኗ እና ትንሳኤውን እንድትመሰክር ከየኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳሚ ተልዕኮ የተሰጣት ስለሆነች ነው" በማለት አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በሐዋርያዊ ሥልጣን መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና ማደግ ይኖርበታል በማለት፣ ብዙ ሴቶችን በከፍተኛ የሃላፊነት ሚና እንዲያገለግሉ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ እንደገለጹት፣ ቅዱስነታቸው ከጎርጎሮሳዊያኑ 2013 ዓ. ም. ጀምሮ ሴቶች በቤተክርስቶያን ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት እና የሃላፊነት ሚና ከፍ ለማድረግ ብዙ ጥረቶችን ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ወደ ፊትም ብዙ መደረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” የተሰኘ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን በመጥቀስ እንዳስረዱት፣ “የወንዶችን እና የሴቶችን እኩልነት መሠረት ያደረገ ሕጋዊ የሴቶች መብት ጥያቄ እንዲከበር፣ ወደ ጎን ሊባሉ የማይገቡ ጥልቅ እና መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች በቤተክርስቲያን ውስጥ መኖራቸውን” አስታውሰዋል (ከወንጌል የሚገኝ ደስታ 104)። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጥቅምት ወር በማለት የላኩትን የጸሎት ሃሳብ መልዕክት በማስመልከት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ እንደገለጹት፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያዊ ልዑክ በመሆን፣ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበልን ሁላችን ወንጌልን በታማኝነት ለመመስከር መጠራታችንን አስረድተዋል። ሆኖም በማውቅም ሆነ ባለ ማወቅ፣ በምዕመናን መካከል፣ በተለይ ሴቶች በሐዋርያዊ አገልግሎቶች ውስጥ በብቃት እንዳይሳተፉ ዕድል ሳይሰጣቸው መቆየቱን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውድ አማዞኒያ” ባሉት መልዕክታቸው፣ በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሴቶች፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተነሳስተው፣ ለእምነት ባላቸው ጥልቅ ፍቅር፣ የቤተክርስቲያንን ሕይወት በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል። በመሆኑም ሴቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ውሳኔን መስጠት በሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ሥር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ እና በጸሎት ኃይል የሚመጣ የእኛ መለወጥ ሊኖር ያስፈልጋል።

የምስጢረ ጥምቀት ትርጉም እና የቤተክርስቲያን ተልዕኮ፤               

በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥቅምት ወር 2013 ዓ. ም. በላኩት የቪዲዮ መልዕክት ላይ እንዳስተነተኑት፣ ቅዱስነታቸው ስለ ምስጢረ ጥምቀት በማስረዳት መልዕክት ማስተላለፋቸው፣ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የምዕመናን ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማስረዳት እንደሆነ ገልጸው፣ በተለይም ሴቶችን በሃላፊነት ቦታ ማሰማራት እንደ ሌሎች ሕዝባዊ ሃላፊነቶች መቆጠር እንደሌለበት፣ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ወይም በምዕመናን እና በቤተክህነት መካከል የሚደረግ የስልጣን ክፍፍል አለመሆኑን አስረድተዋል። በሌላ አገላለጽ ለሴቶች የሥራ ዕድልን እንደመፍጠር መታየት የለበትም ብለዋል። ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ በማከልም፣ እያንዳንዳችን ስለተቀበልነው የጥምቀት ምስጢር ትክክለኛ ትርጉሙን የምናውቅ ከሆነ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለንን ድርሻ በሚገባ ማወቅ እንችላለን ብለዋል። አክለውም ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያሰኛት ምዕመናን የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ እና ድጋፍ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ አስተዋጽዖ ሴቶች በጥሪአቸው ማዕከላዊውን ስፍራ የሚይዙ መሆናቸውን አስረድተዋል።   

11 October 2020, 09:40