ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ኢፍትሃዊነትን በድፍረት የሚቃወሙ ክርስቲያኖች ያስፈልጋሉ”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘወትር ርቡዕ ዕለት የሚያቀርቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸውን መስከረም 27/2013 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመስብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን አቅርበዋል። ዛሬ ያቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ከዚህ በፊት ጀምረውት የነበረውን እና ስለ ጸሎት ሲያቀርቡ የቆዩት አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል ሲሆን፣ “ጸሎት የግል ነፍሳችንን ብቻ የምንመግበት ሳይሆን የሰውን ልጅ በሙሉ ለማገልገል የሚያስችለንን ኃይል ከእግዚአብሔር የምናገኝበት መንገድ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ከ1ኛ ነገሥት ምዕ. 19፡11-13 ተወስዶ የተነበበውን የዛሬውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የጠቀሱት ቅዱነታቸው፣ ነብዩ ኤልያስ ኢፍትሃዊ መንገድ ይከተል የነበረውን ንጉሥ በድፍረት ይቃወም እንደነበር አስታውሰው፣ እንደ ነብዩ ኤልያስ የመሪዎችን ኢፍትሃዊ ተግባሮችን በድፍረት በመቃወም፣ ስህተታቸውንም መናገር የሚችሉ ክርስቲያኖች ያስፈልጋሉ ብለዋል። ስለ ጸሎት ባቀረቡት አስተምህሮአቸውም፣ ነብዩ ኤልያስ ጠንካራ የጸሎት ሕይወት የነበረው ነብይ መሆኑን አስታውሰዋል።

ክርስቲያኖች በአንድ ሃሳብ እንዲጸኑ መጠራታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እምነትን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ እርሱ ለአገልግሎት ወደሚልከን ማንኛውም ቦታ በደስታ ለመሄድ ራስን ነጻ ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል። ጸሎት የግል ነፍስን ብቻ ለመንከባከብ ሲባል ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ግንኙነት ከሆነ፣ ይህ እውነተኛ ጸሎት ሊሆን እንደማይችል አስረድተው፣ ጸሎት ማለት እግዚአብሔር በፈለገው ጊዜ እና ሥፍራ ወንድሞችን እና እህቶችን ለማገልገል በሚጠራን ጊዜ ራስን ነጻ እና ዝግጁ አድርጎ መቅረብ ነው ብለዋል።  የጸሎት መለኪያው ለጎረቤቶቻችን ተጨባጭ ፍቅር ማሳየት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ክርስቲያኖች በቅድሚያ በሚፈልጉት ነገር ማስተንተን እና ቀጥሎም በጸሎት መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለው ይህ ካልሆነ ግን በርካታ ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ ብለዋል። ምክንያቱም ምን ማድረግ ወይም ምን መሥራት እንዳለባቸው አስቀድመው እግዚአብሔርን በጸሎት ስለማይጠይቁ ነው ብለዋል።

በእግዚአብሔር ታምኖ መሰማራት፤

በዕለት በተነበበው በመጽ. ነገሥት ምዕ. 19 ላይ ነብዩ ኤልያስ፣ ምንም እንኳን ብዙ ፈተናዎች እና ማስፈራሪያዎች ቢደርሱበትም ጽኑ እና ጠንካራ እምነት ያለው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ መሆኑን አስረድተዋል። ነብዩ ኤልያስ ከእግዚአብሔር የቀረበለትን ጥሪ በሚገባ የሚያውቅ፣ ፈተናን እና መከራን ተቋቁመው ማለፍ የቻሉት ሰዎች ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል።            

የነብዩ ኤልያስ የእምነት ጽናት የታወቀው እስከ ኮሬብ ተራራ ድረስ ባጋጠመው የምድር መናወጥ እና የመከራ ጉዞ ውስጥ ጽኑ በመሆኑ ሳይሆን እግዚአብሔር ባመጣው እና ጸጥታ በሰፈነበት ነፋስ ውስጥ እንደነበር ገልጸው፣ በመጽሐፈ ነገሥታት ውስጥ የተጠቀሰው የነብዩ ኤልያስ ታሪክ ለእኛ የተጻፈ መልዕክት ይመስላል ብለው፣ አንዳንድ ጊዜ እኛም እንደ ነብዩ ኤልያስ የብቸኝነት ስሜት ሊሰማን ይችላል ብለው ቢሆንም የጸሎት ኃይል ልባችንን በማንኳኳት፣ ተሳስተን ቢሆን፣ ጥቃት ቢሰነዘርብን፣ በፍርሃት ውስጥ ብንገኝ እንኳ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስንቀርብ ጸጥታን እና ሰላምን ማግኘት እንደምንችል አስረድተው የነብዩ ኤልያስ ምሳሌም ይህን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የብርታት ጊዜ እንዳለ ሁሉ የስቃይ ጊዜም አለ፤

ነብዩ ኤልያስ እምነቱን በእግዚአብሔር ያደረገ ሰው ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ድክመቶች እንደሚታዩበት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጸሎትን በሚያዘወትር ሰው ሕይወት ውስጥ ደካማነት ከደስታ ጊዜ በላይ ዋጋ ያለው መሆኑን አስረድተው፣ ጥንካሬን የምናገኝባቸው የጸሎት ጊዜ፣ ስቃይ እና ፈተና የሚታይባቸው የጸሎት ጊዜያትም መኖራቸውን አስታውሰዋል። ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ የሚያግዘን፣ አንዳንዴም በፈተና ውስጥ ሊከተን የሚችል መሆኑንም አስታውሰዋል።

ነብዩ ኤልያስ፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች ሁሉ በላይ አስደናቂ ታሪክ ያለው፣ በዘመናት ሁሉ ሲታወስ የኖረ፣ በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥም እንደተጠቀሰው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ከሙሴ ጋር አብሮ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ መስከረም 27/2013 ዓ. ም. ያቀረቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከመጀመራቸው በፊት በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተገኙት ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበው፣ በቅርቡ ምስጢረ ክህነትን ለተቀበሉ ካህናት እና በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙት ሐዋርያዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ ለሚገኙት ቆሞሳት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።  

07 October 2020, 18:37