VATICAN-RELIGION-POPE VATICAN-RELIGION-POPE 

ካርዲናል ጆርጅ ፔል፥ “እውነት የፍትህ መሠረት ነው”!

የአውስትራሊያው አቡን፣ ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል፣ ለ400 ቀናት ያህል በእስር ቤት ከቆዩ በኋላ በነጻ ተለቀው ወደ ሮም መምጣታቸው ታውቋል። በህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽመዋል በመባል ክስ የተመሰረተባቸው ካርዲናል ጆርጅ ፔል፣ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የአውስትራሊያው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የቀረበባቸው ክስ ሐሰተኛ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በነጻ ማሰናበታቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ጥቅምት 2/2013 ዓ. ም.፣ ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅን በቫቲካን ተቀብለው ሰላምታ ካቀርቡላቸው በኋላ ለምስክርነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የ79 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ2014 እስከ 2019 ዓ. ም. ድረስ በቅድስት መንበር የኤኮኖሚ ክፍል ሃላፊ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል፣ በተመሰረተባቸው ክስ ምክንያት፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በሐምሌ ወር 2017 ዓ. ም. ከቫቲካን ወጥተው ወደ አውስትራሊያ መሄዳቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል የተመሰረተባቸውን ክስ ተከራክረው ራስን የሚከላከሉበት የበቂ ጊዜ ፍቃድ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰጧቸው መሆኑ ይታወሳል።

ካርዲናል ጆርጅ፣ በመጀመሪያ ክስ ጥፋተኛ ተብለው ነበር፤

ካርዲናል ጆርጅ፣ በአውስትራሊያ የሜልቦርን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት፣ በህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽመዋል በመባል ሁለት ክሶች የቀረቡባቸው መሆኑ ሲነገር የመጀመሪያው ክስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1996 ዓ. ም. እና ሁለተኛው ክስ በ1997 ዓ. ም. የተመሰረተባቸው መሆኑ ይታወሳል። የመጀመሪያው የፍርድ ሂደት የተካሄደው በዚያ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ እንደነበር ይታወሳል። በታህሳስ ወር ላይ የሜልቦርን ፍርድ ቤት ካርዲናል ጆርጅ ፔልን ጥፋተኛ በማድረጉ የተፈረደባቸውን የስድስት ዓመት የቅጣት ጊዜን ለማሳለፍ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በየካቲት ወር 2019 ዓ. ም. ወደ ወህኒ መውረዳቸው ይታወሳል።

ጆርጅ ፔል “እኔ ከጥፋት ንፁህ ነኝ”

ይሁን እንጂ ብጹዕ ካርዲናል ጆርግ ፔል የተመሰረተባቸው ክስ አሳፋሪ እና በዝምታ ሊቀበሉት የማይችሉት በመሆኑ ይግባኝ ማለታቸው ታውቋል። ሕጋዊ ጠበቆቻቸውም የተሰጣችው ፍርድ፣ ምክንያት የሌለው፣ ማስረጃ ቢስ በመሆኑ ይግባኝ ለማለት ዕድል የተሰጣቸው መሆኑ ታውቋል።

ቅድስት መንበርም ተጨባጭ ማስረጃ ይቀርብ ከሆነ ብላ ትጠብቅ ነበር፤

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል እንዳስታወቀው፣ ቅድስት መንበር ለአውስትራሊያው ፍርድ ሥርዓት ያላትን ከፍተኛ አክብሮት ስትገልጽ መቆየቷን አስታውቆ ከዚህም በተጨማሪ ያለፉትን የፍርድ ሂደቶች በጽሞና በመከታተል፣ ካርዲናል ጆርጅ ከተመሰረተባቸው ክስ ነጻ መሆናቸውን ለፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ሊከራከሩ የሚችሉ መሆኑንም ስትከታተል ቆይታ የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔውን ስትጠባበቅ መቆየቷ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ቤተክርስቲያን፣ በህጻናት ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት በጽኑ ስታወግዝ መቆየቷም ይታወቃል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በወሰዱት አቋም፣ ካርዲናል ጆርጅ የፍርድ ሂደት እስኪጣራ ድረስ ከማንኛውም የቤተክርስቲያን አገልግሎት በመታቀብ፣ ከሕጻናትም ጋር ሳይገናኙ እንዲቆዩ ማዘዛቸው ይታወሳል። የአውስትራሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትም በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ በካርዲናል ጆርጅ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት ምዕመናኖቻቸው ድንጋጤ እና ስጋት እንዳይዛቸው በማለት ሲያጽናኑ መቆየታቸው ታውቋል።

የጥፋተኝነት ብይን ከዳኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ሰኔ ወር 2019 ዓ. ም. በቪክቶሪያ ፍርድ ቤት በዋለው ሁለተኛ ችሎት፣ የካርዲናሉ ጠበቃ የመጀመሪያ ዙር የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ምክንያት የሌለው፣ የፍርድ አሰጣጥም ሥርዓትን የተከተለ አይደለም በማለት መከራከራቸው ታውቋል። ፍርዱን የተቃወሙት ዳኛ ማርክ ዌይንበርግ፣ አንድ ተከሳሽ ግልጽ ማስረጃ እስካልቀረበበት ድረስ ፍርድ ሊሰጠው አይችልም በማለት ተቃውሞአቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል።

ቅድስት መንበር የፍርድ ሂደቱን መጠናቀቅ ትጠብቅ ነበር፤

ቅድስት መንበር የአውስትራሊያውን የፍርድ ሥርዓት ባወደሰችበት መልዕክቷ፣ የፍርድ ሂደቱን በቅርብ በመከታተል እና ካርዲናል ጆርጅ ፔል ከጥፋት ነጻ መሆናቸውን ጠብቀው መቆየታቸውን በቅርብ ስትከታተል መቆየቷ ታውቋል።

ከፍተኛ ፍ / ቤቱ ካርዲናል ፔልን በሙሉ ድምፅ ነፃ አድርጓል፤

በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር መጋቢት ወር 2020 ዓ. ም. የአውስትራሊያው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጠራው የመጨረሻ ችሎት፣ ፍርዱን የተቃወሙት ዳኛ ማርክ ዌይንበርግ ያቀረቡትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ሰባት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በሚያዝያ 7/2020 ዓ. ም. በጋራ ባወጡት የፍርድ ውሳኔ፣ ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል ፈጽመዋል ለተባሉት ጥፋት ምንም ዓይነት ማስረጃ ባለመቅረቡ፣ ከ400 ቀናት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ካርዲናሉን በነጻ ማሰናበቱ ታውቋል።

ካርዲናል ጆርጅ ፔል፥ ፍትህ ማለት እውነትን ለሁሉ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ነው፤

ካርዲናል ጆርጅ ፔል ከእስር ነጻ ከወጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በከሳሾቻቸው ላይ መጥፎ አመለካከት እንደሌላቸው ገልጸው አክለውም ለረጅም ጊዜ ፈውስ ብቸኛው መሠረቱ እውነት ነው ብለው፣ እውነት የፍትህም መሠረት፣ ፍትህ ማለት ደግሞ እውነት ለሁሉም ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ፍትህ ለጎደላቸው ሁሉ ይጸልያሉ፤

ባለፈው ዓመት የጾም ወራት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደተናገሩት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የደረሰውን ስቃይ በማስታወስ፣ የሕግ አዋቂዎች እና መምህራን፣ በኢየሱስ ላይ ምንም ጥፋት ባያገኝበትም ለስቃይ እንዲበቃ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ቅድስት መንበር የካርዲናል ነፃ መውጣትን በደስታ ተቀብላለች፤

የብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል ነጻ መውጣትን ቅድስት መንበር በደስታ የተቀበለችው መሆኑን ገልጻ፣ በአውስትራሊያ የፍትህ ባለስልጣን ላይ ያላትን እምነት ገልጻለች። ብጹዕ ካርዲናል ጆርጅ ፔል በበኩላቸው ከጥፋት ነጻ መሆናቸውን አምነው እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥበትን ቀን  በትዕግስት ጠብቀው መቆየታቸውን ገልጸዋል።    

13 October 2020, 11:10