ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆነ በቅድሚያ ባልንጀሮቻችንን መውደድ ይኖርብናል አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በትላናትናው እለት ማለትም በጥቅምት 15/2013 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በማቴዎስ ወንጌል 22፡34-40 ላይ በተጠቀስውና “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልጅንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን “በእውነት እግዚአብሔርን ወዳለሁ የምንል ከሆነ በቅድሚያ ባልንጀሮቻችንን መውደድ ይኖርብናል” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተልው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ምንባብ (ማቴ 22፡34-40) አንድ የሕግ መምህር ኢየሱስን “ታላቁ ትእዛዝ” ምንድነው (ማቴ 22፡ 36) ማለትም የሁሉም መለኮታዊ ሕግ ዋና ትእዛዝ የቱ ነው በማለት ይጠይቀዋል። ኢየሱስ በቀላሉ ይመልሳል-“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ ፣ በሙሉ ነፍስህ ፣ በሙሉ አእምሮህ ውደድ” (ቁ. 37)። እናም ወዲያውኑ ያክላል-“ሁለተኛው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው-“ ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ”(ቁ 39) የሚሉት ናቸው በማለት ይመልሳል።

የኢየሱስ ምላሽ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለሕዝቡ የሰጣቸውን ሁለት መሠረታዊ መመሪያዎችን የሚይዝ እና አንድ የሚያደርግ ነው (ዘዑልቁ 6፡5 ፣ ዘሌ 19፡18) እንደ ተገለጸው። እናም “እሱን ለመፈተን” የተሰጠውን ወጥመድ ያሸንፋል (ቁጥር 35) ፡፡ ለእርሱ ይህንን ጥያቄ ያቀረበለት ሰው በእውነቱ በሕግ ባለሙያዎች መካከል እርሱ የሚሰጠውን መልስ ለመስማት ፈልጎ እና እርሱን ለማዋረድ በማሰብ ይህንን ሐሳብ ለማቅረብ ይሞክራል። ኢየሱስ ግን ሁል ጊዜ ላሉት አማኞች ሁለት አስፈላጊ እና መሰረታዊ የሆኑ ማዕከላትን ያዘጋጃል፣ እነዚህም ለህይወታችን የሚያስፈልጉ ሁለት ዋና አስፈላጊ ምሶሶዎች ናቸው። የመጀመሪያው ሥነ ምግባራዊ እና ሃይማኖታዊ ሕይወት ወደ ጭንቀት እና በግዳጅ መታዘዝ ሊቀየር እንደማይችል ያሳያል። ትዕዛዛትን በጭንቀት ወይም በግዳጅ ለመፈፀም የሚሞክሩ ሰዎች አሉ ፣ እናም ኢየሱስ የሞራል እና የሃይማኖት ሕይወት ወደ ጭንቀት እና በግዳጅ መታዘዝ ሊቀነስ እንደማይችል እንድንገነዘብ ያደርገናል፣ ነገር ግን እንደ መርህ አድርገን ልንይዘው የሚገባው ነገር ቢኖር ፍቅር ነው። ሁለተኛው መሰረታዊ ነገር ፍቅር በአንድነት ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ባልንጀሮቻችን በማይለያይ መልኩ ለመግለጽ መጣር አለበት የሚል ነው። ይህ የኢየሱስ ትምህርት ዋና ዋና ከሆኑት መካከል አንዱ ነው፣ እናም ለባልነጀሮቹ ፍቅር የማይገለጽ እውነተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር አለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፣ እናም በተመሳሳይ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ግንኙነት የማይወጣ ፍቅር እውነተኛ የባልንጀራ ፍቅር አይደለም።

“ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው” (ማቴ 22፡40) በማለት ኢየሱስ ምላሹን በእነዚህ ቃላት ይደመድማል። ይህ ማለት ጌታ ለህዝቦቹ የሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ ከእግዚአብሄር እና ከጎረቤት ፍቅር ጋር መዛመድ አለባቸው ማለት ነው። ያንን እጥፍ የማይነጠል ፍቅርን ለመግለጽ በእርግጥ ሁሉም ትእዛዛት ለመተግበር ያገለግላሉ። ለእግዚአብሄር ያለን ፍቅር ከሁሉም በላይ በጸሎት በተለይም በስግደት ይገለጻል። የእግዚአብሔርን አምልኮ በጣም ቸል እንላለን። የምስጋና ጸሎትን እናቀርባለን፣ አንድ ነገር ለመጠየቅ እንለምናለን ... ነገር ግን አምልኮን ችላ እንላለን። የጸሎት እምብርት እግዚአብሔርን ማምለክ ነው። እናም ለባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ፣ ወንድማዊ ምጽዋት ተብሎም ይጠራል ፣ ቅርበት ፣ ማዳመጥ ፣ መጋራት ፣ ሌላውን መንከባከብ የሚያካትት ስለሆነ። እናም ብዙ ጊዜ እሱ አሰልቺ ስለሆነ ወይም ጊዜዬን ስለሚወስድብኝ ሌላውን ለመስማት ቸል እንላለን ፣ ወይም በሕመሙ ውስጥ ፣ በፈተናዎቹ ውስጥ አብረነው ለመጓዝ እንታክታለን ...  ነገር ግን ሁል ጊዜ ወሬ ለማውራት ጊዜ እናገኛለን ፣ ሁሌም! የተቸገሩትን ለማፅናናት ጊዜ የለንም ለማውራት ግን ብዙ ጊዜ አለን። እንጠንቀቅ! ሐዋርያው ​​ዮሐንስ “የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ የማያየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልም” (1 ዮሐ 4 20) ሲል ገልጾታል። ስለዚህ የእነዚህ ሁለት ትእዛዛት አንድነት እናያለን።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደገና ወደ ህያው እና ወደ አፍቃሪ የፍቅር ምንጭ እንድንሄድ ኢየሱስ ይረዳናል። እናም ይህ ምንጭ ምንም እና ማንም ሊሰብረው በማይችለው ህብረት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የሚወደደው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ህብረት ማለት በየቀኑ የሚሰጥ ስጦታ ሲሆን ነገር ግን ህይወታችን እራሱን በአለም ጣዖታት እና በባርነት ውስጥ ተቆልፎ እንዳይኖር እና በዚህ ውስጥ እንዳንወድቅ የምናደርገው የግል ቃልኪዳን ጭምር ነው። እናም የመለወጥ እና የቅድስና ጉዞዋችን ማረጋገጫ ሁል ጊዜም ቢሆን ለባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ነው። ማረጋገጫው ይህ ነው-“እግዚአብሔርን እወዳለሁ” ካልኩ እና ጎረቤቴን ካልወደድኩ አይሰራም ፡፡ እግዚአብሔርን እወዳለሁ የሚለው ማረጋገጫ ባልጅንጀራዬን መውደዴ ነው። ልባችንን የምንዘጋበት ወንድም ወይም እህት እስካለ ድረስ ኢየሱስ እንደሚጠይቀን ደቀ መዛሙርት ከመሆን እንርቃለን። ነገር ግን የእርሱ መለኮታዊ ምህረት ተስፋ እንድንቆርጥ አይፈቅድልንም፣ በተቃራኒው ደግሞ በወጥነት ወንጌልን ለመኖር በየቀኑ እንድንጀምር ይጠራናል ፡፡

የእግዚአብሔርን ሕግ ሁሉ ጠቅለል አድርጎ የሚይዘውን መዳናችን የተመካበትን “ታላቁን ትእዛዝ” የፍቅር ድርብ ትእዛዛትን ለመቀበል ቅድስት ድንግል ማርያም ልባችንን እንድትከፍት አማላጅነቷን እንማጸን።

25 October 2020, 11:40