ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ከወቅቱ ችግር የምንወጣበት ብቸኛው መንገድ በመተባበር ነው”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት የሚያቀርቡትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በማከታተል ለዛሬ መስከረም 13/2013 ዓ. ም. ያዘጋጁትን አስተምህሮ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ዳማሶ ቅጥር ግቢ በዛሬው ዕለት ያቀረቡት ሳምንታዊ አስተምህሮ፣ ባሁኑ ጊዜ ዓለማችንን እጅግ እያስጨነቃት በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለማጽናናት በማሰብ “ዓለምን መፈወስ” በሚል ዐብይ አርዕስት የጀመሩት አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል መሆኑ ታውቋል። በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ስምንተኛው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ከደረስብን የወቅቱ ችግር መውጣት የሚቻለው፣ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል፣ ደሃ ወይም ሃብታም ሳይባል ሁሉም ሰው የበኩሉን ሚና ሲጫወት፣ የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ እና አንድነቱን ሲገልጽ ነው ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተምህሮን መሠረት በማድረግ ባቀረቡት አስተምህሮ፣ “ከኮቪድ-19 ወረርሽም ቢሆን መላቀቅ የምንችለው፣ ቤተክርስቲያን እንደምታስተምረን ሁሉ፣ እያንዳንዳችን የተጠራንበትን የአገልግሎት ድርሻ ተቀብለን የበኩላችንን አስተዋጽዖን ስናደርግ ነው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ “ማኅበራዊ መረጋጋትን ለማምጣት የእያንዳንዱ የማሕበረሰብ አባል ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ፣ የተሰጠው ስጦታም እንዲከበርለት ያስፈልጋል” ብለዋል።

እ. አ. አ. በ1929 ዓ. ም. ዓለማችንን ያጋጠመውን ታላቁን የኤኮኖሚ ድቀት ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በወቅቱ የነበሩት ር. ሊ. ጳ. ፒዮስ 11ኛ፣ ከደረሰው የኤኮኖሚ ውድቀት ለመነሳት የሚያግዝ ብቸኛው መንገድ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የታቀፉት በሙሉ፣ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት አባላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ፣ የሥራ ድርሻቸውንም በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

“በዚህ ወቅት ካጋጠመን ችግር የምንወጣበት ብቸኛው መንገድ በመተባበር ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “እያንዳንዱ ሰው የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት እንዲችል፣ ድርሻቸውንም በሚገባ እንዲወጣ፣ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደርጃ ላይ የሚገኙት ሰዎች፣ ያላቸው ችሎታ እና የሚጫወቱት ሚና ሳይናቅ ተገቢው አድናቆት ሊቸርለት ይገባል” ብለዋል። “ይህም እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል በደስታ እንዲሳተፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በችግር ውስጥ የሚገኘውን ዓለማችንን በመፈወስ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር ያግዛል” ብለዋል። “ባሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ይህን ዕድል በመነፈግ፣ ከማኅበረሰቡ በመገለል እና በመረሳት፣ ዓለምን ወደ መልካም ደረጃ ለማድረስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ መሳተፍ አልቻሉም” ብለዋል።

አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች በኤኮኖሚ አቅም ማነስ ወይም ማኅበራዊ ጫና በስቶባቸው የበኩላቸውን ድጋፍ ማበርከት አልቻሉም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በሌሎች ማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ሰዎች እምነታቸውን እና ባሕላዊ እሴቶቻቸውንም ሳይቀር በነጻነት መግለጽ አይችሉም ብለዋል። በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ በርካታ ሰዎች የስነ-ምግባር እና የሐይማኖት ነጻነታቸው መረገጡን አስታውሰው፣ እንዲህ ዓይነት አካሄድ ከሚደርስባቸው ማሕበራዊ ችግር ለመላቀቅ ምንም የማያግዝ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

“በኤኮኖሚ እና በማኅበራዊ ሕይወት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ መንግሥታት በማደግ ላይ ለሚገኙ መንግሥታት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ዕድገትን እንዲያመጡ መርዳት ይኖርባቸውል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኤኮኖሚ የበለጸጉት አገሮች ሕዝባዊ ተቋማት የሚችሉትን ዕርዳታ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውሰው፣ የሕዝብ መሪዎች ለእነዚህ ዕርዳታዎች አድናቆትን በመስጠት ወደ ተረጂው ክፍል በሥርዓቱ መድረሳቸውንም መከታተል ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዜጎች ለማኅበራዊ ተሳትፎአቸው በቂ እውቅና እንደማይሰጣቸው ገልጸው፣ ሰፋፊ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ቢሆኑ በየጊዜው በሚወስዷቸው ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች፣ በኤኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍል የሚዘነጓቸው መሆኑን ገልጸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒት ለማምረት የሚደረገውን ውድድር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ሰፋፊ የመድኃኒት አምራች ኩባኒያዎች፣ በሕክምና መስጫ ማዕከላት እና በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በግንባር ቀደምትነት ተሰማርተው የሚገኙትን የጤና ባለሞያዎች አቤቱታን አለማዳመጥ ጥሩ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሐዋ. ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ፣ በምዕ. 12:22 ላይ “አንዱ የአካል ክፍል ሌላውን አታስፈልገኝም ሊለው አይችልም” ማለቱን ጠቅሰው፣ የመተጋገዝ መሠታዊ ሃሳብ የሚመነጨው እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል፣ ደሃ ወይም ሃብታም ሳይባል ሁሉም ሰው የበኩሉን ሚና ሲጫወት፣ የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ በሕመም ውስጥ የምትገኝ ዓለማችንን በመፈወስ ወደ ብርሃን ማሻገር ነው ብለዋል። ይህን መርህ ተግባራዊ ማድረግ ተስፋን በመስጠት ጤናማ እና ፍትሃዊ ሕይወት ለመኖር የሚያግዝ በመሆኑ መልካምን በማሰብ፣ አመለካከታችንን በማስፋት፣ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በብቃት ማሳተፍ ያስፈልጋል ብለው አነሰም በዛ ሰዎች ለሚያደርጉት ማኅበራዊ ተሳትፎ እውቅናን እና አድናቆትን መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። ባሁኑ ጊዜ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ሕይወታቸውን እስከ መስጠት የደረሱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኛ ሰራተኞች መኖራቸውን አስታውሰው፣ ለእነዚህ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

23 September 2020, 18:51