ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ሰላም የሚገኘው በመሣሪያ ኃይል ሳይሆን በውይይት እና በድርድር ነው”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ መስከረም 17/2013 ዓ. ም ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ካጠናቀቁ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰው ለምዕመናኑ አጭር ንግግር አድርገዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ለሁለቱ አገሮች መሪዎች፣ ለአርመኒያ እና አዘርባጃን መሪዎች ባቀረቡት ጥሪያቸው በአገሮቹ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በመልካም ውይይት በመታገዝ መፍትሄን እንዲያመጣ እና በአካባቢው ለተፈጠረው ቀውስ በጎ ምላሽ እንዲሆን አደራ ብለዋል። ወደ ጦርነት የገቡት የአርመንያ እና የአዘአርባጃን መንግሥታት በወንድማማችነት እና በመልካም ፍላጎት ተነሳስተው፣ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት አስወግደው ሰላማዊ መፍትሄን እንዲያገኙ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም እንዲወርድ ጸሎት የሚያደርጉ መሆኑንም ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም “ሰላም የሚገኘው በመሣሪያ ኃይል ሳይሆን በውይይት እና በድርድር ነው” ብለው በሁለቱ አገሮች መካከል እና በአካባቢው ሰላም እንዲወርድ ክርስቲያኖች በጸሎት እንዲተባበሯቸው ጠይቀዋል።

ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

መስከረም 17/2013 ዓ. ም ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፣ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙ ምዕመናን መካከል ከተለያዩ አገሮች ለመጡ የሮም እና አካባቢው ነዋሪ ለሆኑት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ለዘንድሮ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ ባሰሙት ንግግር፣ በሁኑ ጊዜ በበርካታ አገሮች ውስጥ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው እና አካባቢያቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ብዙ ቤተሰቦች መኖራቸውን አስታውሰው፣ “እነዚህ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ የበቁት ኢየሱስ ከቤተሰቡ ጋር እንዲፈናቀል ያስገስደደው መከራ ዓይነት ስላጋጠማቸው ነው” ብለው፣ ተፈናቃዮችን ሆነ ተፈናቃዮች ተቀብለው መጠለያን እና የተለያዩ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ የሚገኙትን በሙሉ በጸሎት እናስታውሳቸዋለን ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን አስታውሰዋል፤

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊ ውድቀት ያጋጠመውን የቱሪዝም ዘርፍ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁትን ቤተሰቦች በንግግራቸው አጽናንተዋል። መስከረም 17/2013 ዓ. ም ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር ባሁኑ ጊዜ በዘርፉ የተሰማሩት በአነስተኛ ማኅበራት የተደራጁ ወጣቶች እና የቤተሰብ ክፍሎች በኮቪድ-19 ምክንያት   በአገልግሎት መዳከም ምክንያት ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አስታውሰው፣ ከአጭር ጊዜ በኋላ ችግሩ ተቃልሎ ወደ ነበረበት እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከጡት ካንሰር የተፈወሱ ሴቶችን አጽናንተዋል፤

በዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን መካከል ከጡት ካንሰር የዳኑት ሴቶች መኖራቸውን የተመለከቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጡት ካንሰር የሚሰቃዩ ሴቶችን እና በሽታውን ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ በርካታ ማኅበራት መኖራቸውን አስታውሰው “እግዚአብሔር ለጥረታቸው ድጋፍ እንዲሆናቸው” በማለት በጸሎት አስታውሰዋል።               

28 September 2020, 11:47