ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ እንደ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ኢየሱስ እንዲገዳደረን ልንፈቅድለት ይገባል አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሰኔ 22/2012 ዓ.ም የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ አመታዊ በዓል ተክብሮ ማለፉ ይታወሳል።ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደረጉት ስብከት በምድር ላይ አንድነት እንዲፈጠር የምንሰራ እና  የእግዚአብሔርን ምንግሥት በምድር ላይ የምንመስከር ነቢያት እንድንሆን ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ እንዲሳተፉ የተደረጉት ደግሞ ጥቂት ምዕመናን ሲሆኑ ይህም የተደረገበት ምክንያት አሁን በስፋት የሚታየውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ለመከላከል እንደ ሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር ላይ በተገነባው መንበረ ታቦት ላይ መስዋዕተ ቅዳሴውን በማሳረግ የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል አክብረዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ያደረጉት ስብከት “አንድነት” እና “ትንቢት” በተሰኙ ጭብጦች ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ ነበር።

ሕብረት የጸሎት ውጤት ነው

ምንም እንኳን በእውቀት እና በባህሪ በጣም የተለያዩ ቢሆኑም ጴጥሮስ እና ጳውሎስ እንደ ወንድማማቾች አንድ እንደነበሩ በስብከታቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው አንዳቸው ለሌላው የነበራቸው ቅርበት የተፈጥሮ ዝንባሌ ውጤት አለመሆኑን ያብራሩ ሲሆን ነገር ግን እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ካዘዘን ከእግዚአብሔር የመጣ ነው ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “አንድ የሚያደርገን እርሱ ነው፣ ይህ አንድነት የሚገነባ በብዝሃነት ነው” ብለዋል፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የአንድነት ምንጭ ጸሎት መሆኑን ገልፀው ጴጥሮስ እና ጉደኞቹ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት ከእስር ነጻ እንዲሆኑ ያደርጋቸው በጋራ በመጸለያቸው ነው ብለዋል።በጋራ መጸለይ የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን አመልክተዋል ፡፡ በዘመኑ የነበሩት ክርስቲያኖች በስደት ወቅት ከማጉረምረም ይልቅ በጋራ የመጸለይ ልምድ ነበራቸው ብለዋል።

በጸሎት ብዙ ጊዜ ብናሳልፍ እና ቅሬታችንን ብንቀንስ “ብዙ በሮች ይከፈታሉ ፣ ጠፍረው የያዙን ብዙ ሰንሰለቶች ይበጣጠሳሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው ነቢይ መሆን ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ያስከትላል ብለዋል።

ጴጥሮስና ጳውሎስ ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ነቢይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ደቀመዛሙርቱ ከኢየሱስ ፈታኝ የሆነ ጥያቄ ደርሶባቸዋል፣ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እኔ ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ መጠየቁን ያስታወሱ ሲሆን ጳውሎስንም “ሳኦል ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” ብሎ ጠይቆት እንደ ነበረ አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “እነዚህ ተግዳሮቶች እና ተቃራኒ ለውጦች ነቢያት ይከተላሉ” ያሉ ሲሆን በቄሳርያ ውስጥ ኢየሱስ ቤተክርስቲያኑን የሚያንጽበት ድንጋይ እንደሚሆን ለጴጥሮስ ነግሮታል፣ ጳውሎስ ከተለወጠ በኋላ ለአህዛብ ወንጌልን ለማምጣት የጌታ “የተመረጠ መሣሪያ” መሆኑን አብራርተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንስኮስ “ትንቢት የሚወለደው እግዚአብሔር እንዲገዳደረን ስንፈቅድለት ብቻ ነው ” ያሉ ሲሆን እውነተኛ ትንቢት ያስፈልጋል፣ እውነተኛ ትንቢት በሚያስደንቅ ማሳያዎች ውስጥ አይገኝም ፣ ነገር ግን በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር በመመስከር እንደ ሚገኝ የገለጹ ሲሆን “ጴጥሮስና ጳውሎስ እግዚአብሔርን እንደወደዱት ኢየሱስን የሰበኩት በዚህ መንገድ ነበር” ብለዋል።

ለእግዚአብሔር እና ለኢየሱስ የነበራቸው ፍቅር ህይወታቸውን በሰማዕትነት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል “ይህ ትንቢት ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተናገሩ ሲሆን በዚህ ተግባራቸው ደግሞ ታሪክ ቀይረዋል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ኢየሱስ ቤተክርስቲያኑን የሚገነባበት ዐለት እንደ ሚሆን ስለጴጥሮስ የተነበየው ትንቢት እውን እንደ ሆነ ሁሉ ለእኛም ተመሳሳይ ተስፋ ይሰጠናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት “ጌታ የስምዖንን ስም ወደ ጴጥሮስ እንደለወጠው ሁሉ እኛም አዲስ ቤተክርስቲያን እና አዲስ የተገነባ አንድነት የሚገነባበት ሕያው ድንጋዮች እንድንሆን እያንዳንዳችንን እየጠራናል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እያንዳንዳችንን “ኢየሱስ እንዲገዳደረን ልንፈቅድለት የገባል፣ በምድር ላይ የእግዚአብሔርን መንግስት የምንገነባ ነቢያት እንድንሆን ጥሪ ያቀርብልናል፣ አንድነትን እንድንገነባ ጥሪ እያቀረበልን ይገኛል ለዚህ ጥሪ ምላሽ ልንሰጥ ይገባል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

29 June 2020, 17:16