ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እና የሰሜን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እና የሰሜን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለሰሜን አሜርካ ቤተክርስቲያን የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንደ ሚቀጥሉ ገለጹ!

የሰሜን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የሎሳንጀለስ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት ጋር በተዛመደ መልኩ ለመላው የሰሜን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅርብ መሆናቸውን እና በጸሎት አብረዋቸው እንደ ሚሆኑ ቅዱስነታቸው መግለጻቸው የተገለጸ ሲሆን ሁኔታዎች እንዲረጋጉ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የሰሜን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እያከናወነች የምትገኘውን ተግባር ቅዱስነታቸው አመስገነዋል።

የቫቲካን ዜና

ጠንካራ የሆነ ሐዋርያዊ ማበረታቻ እና በጸሎት ከእነርሱ ጋር እንደ ሚሆኑ የተሰጠ ማረጋገጫ፣ ይህ ትላንት ግንቦት 27/2012 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሎሳንጀለስ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ ጋር በስልክ ያደረጉት ውይይት ዋና ይዘት ሲሆን ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጋር ተያይዞ የተከሰተው ሁከት እና ግጭት በተገቢው መልኩ መፍትሄ እንዲበጅለት እና ዘረኝነት እንዲወገድ ቤተክርስቲያን ከዚህ ቀደም የጀመረችሁን ተግባር አጠናክራ እንድትቀጥል ቅዱስነታቸው ጥሪ ማቅረባቸውም ተገልጿል።

በጆርጅ ፍሎይደ ሞት የተነሳ በሰሜን አሜሪካ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሰላማዊ ስለፍ እንዲደረግ፣ በዚህም ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በአሜሪካ ስልታዊ በሆነ መልኩ በአፍሮ አሜሪካዊያን እና በሌሎች ሰዎችም ላይ የሚፈጸመውን የዘረኝነት ጥቃት በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ቤተክርስቲያኗ ማስተባበሯ የሚታወቅ ነው።

“ለፍትህ የሚጮህ እና በኃጢአት የተሞላ የግድያ ተግባር ነበር” በማለት ድምጻቸውን ያሰሙት የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የሎሳንጀለስ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ እሑድ ግንቦት 23/2012 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር በመላው የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ስም ለጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን፣ በሐዘን ውስጥ ለወደቁት ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና ለሚኒያፖሊስ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በሙሉ መጽናናትን በጸሎታቸው መመኘታቸው ይታወሳል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ በብጹዓን ጳጳሳቱ ስም በላኩት መልዕክታቸው፣ የአካባቢው ባለ ስልጣናት ፍትህን ለማረጋገጥ ጠንክረው እንደሚሠሩ፣ የቆዳ ቀለምን በመለየት በአፍሮ-አሜሪካዊያን ላይ የሚደርሰውን በደል፣ አድልዎ እና ዘረኝነት ለማስቀረት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ በአፍሮ-አሜሪካዊያን መካከል የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ ቁጣ ተመልክተው ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ በማከልም በአገሪቱ እጅግ ሥር የሰደደ ዘረኝነት ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ያለ መሆኑን አስረድተው፣ ለፍትህ መጓደል ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን መለየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ በማከልም በእነዚህ ቀናት በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሱ የሕዝብ አመጾች ለተፈጸመው ድርጊት መልስ እንደማያስገኙ አስረድተው፣ በአገሪቱ ጸጥታ እና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠይቀዋል። “የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በዋዛ የሚታለፍ አይደለም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ ዘረኝነትን እና ጥላቻን ከልባችን በማስወገድ ለጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ ክብር መስጠት ያስፈልጋል ብለው፣ በመላው አገሪቱ የሕይወት ዋስትና፣ ነጻነት እና እኩልነት እንዲረጋገጥ በማለት በመልዕክታቸው ጠይቀዋል።

 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በበኩላቸው እንደ ገለጹት በቅርቡ በአሜሪካ በአንድ ፖሊስ አማካይነት ሕይወቱ ያለፈው ጆርጅ ፍሎይድ ላይ የተፈጸመው ተግባር በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን የገለጹ ሲሆን የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት የተቀደሰ በመሆኑ የተነሳ በማነኛውም መንገድ ሊከበር ይገባዋል እንጂ ዓይናችንን በዘረኝነት መንፈስ መሸፈን እና ሰዎችን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነ ቅዱስነታቸው አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

“በሰሜን አሜሪካ የምትገኙ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች፣ ጆርጅ ፍሎይድ አሰቃቂ ሞት ከሞተ በኋላ በእነዚህ ቀናት ውስጥ በአገራችው ውስጥ የተከሰተ የሚገኘውን አሰቃቂ ማህበራዊ አለመረጋጋት በታላቅ ጭንቀት እየተከታተልኩኝ እገኛለሁ” በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ማንኛውንም ዓይነት ዘረኝነትን ወይም ማግለል በየትኛውም የሰው ልጅ ሕይወት እንዲከሰቱ መፍቀድ እና ዓይናችንን መጨፈን እና መታገስ በፍጹም አይኖርብንም፣ የሰው ነፍስ የተቀደሰች ናትና ብለዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ​​እኛ “ባለፉት ቀናት የተከሰቱት ጥቃቶች እና ሁከቶች ራስን የሚያጠፉ እና እራሳን የሚጎዳ ተግባራት መሆናቸውን ልገልጽ እወዳለሁ። ከግጭት ጥፋትን እንጂ ሌላ የምናተርፈው ነገር የለንም።  ዛሬ የጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ እና ለሌሎች በዘረኝነት ኃጢያት ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች መጸለይ ይገባል” ብለዋል።

04 June 2020, 20:12