ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ቅድስት ስላሴ ዓለምን የሚያገለግል ፍቅር ነው” ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ ዕለት ባቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ያታወቃል። በመሆኑም ቢያን ቢያንስ ከሦስት እና ከአራት ወራት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል ማሕበራዊ ርቀት መጠበቅ ተገቢ በመሆኑ የተነሳ ሕዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች እና አብያተ ክርስቲያናት በመዘጋታቸው ይታወሳል። የዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጣሊያን አገር ስርጭቱ እየቀነሰ በመምጣቱ የተነሳ ተገቢውን ማሕበራዊ ርቀት በጠበቀ መልኩ እና የተለመደውን ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ አብያተ ክርስቲያናት እና አንዳንድ ማሕበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንደገና እንዲከፈቱ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በዚህ መሰረት በግንቦት 30/2012 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን አስተንትኖ ለመከታተል ምዕመኑ በስፍራው መገኘታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በግንቦት 30/2012 ዓ.ም የቅድስት ስላሴ አመታዊ በዓል ተከብሮ ማለፉ ይታወቃል፣ ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ መሰረቱን ያደረገው “ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው [...] ኢየሱስም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል” (ዮሐንስ 3፡16-18) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን “ቅድስት ስላሴ ዓለምን የሚያገለግል ፍቅር ነው” ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራና እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የቅድስት ስላሴን በዓል በምናክብርበት በዛሬው ዕለት የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ 3፡16-18)  ትርጓሜ ሐዋርያው ​​ዮሐንስ በተዋሃደ ቋንቋ - እግዚአብሔር እርሱ ለፈጠረው ፍጥረት ለዓለም ያለው ፍቅር ምስጢር ይገልጻል። ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው አጭር ውይይት ዓለምን ለመደገፍ የአባቱን የደኅንነት ዕቅድ የሚያከናውነው ኢየሱስ ራሱ እንደ ሆነ ይገልጻል። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐንስ 3፡16) በማለት ማረጋገጫ ይሰጣል። እነዚህ ቃላት የሚያመለክቱት የሦስቱን መለኮታዊ አካላት ተግባር ሲሆን - አብ ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ - ሁሉም ሰብአዊነትን እና ዓለምን የሚያድን አንድ የፍቅር ዕቅድ አላቸው፣ እሱም እኛን የመዳን ዕቅድ ነው።

እግዚአብሔር ዓለምን መልካም እና ውብ አድርጎ ፈጠረ፣ ነገር ግን የሰው ልጅ ኃጢአት ከሠራ በኋላ ዓለም ክፋት እና የሥነ ምግባር ውድቀት ምልክት ሆነች። እኛ ወንዶች እና ሴቶች ኃጢአተኞች ነን ፣ ስለሆነም እግዚአብሔር በዓለም ላይ መፍረድ ፣ ክፉ ተግባራትን ማጥፋት እና ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ጣልቃ መግባት ይችላል። በምትኩ ኃጢያቶች ቢኖሩም እንኳን እግዚአብሔር ዓለምን ይወዳል፣ እኛ ስህተት በምንፈጽምበት ጊዜ እና ከእርሱ በምንርቅበት ጊዜያት እንኳን ሳይቀር እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ይወደናል። እግዚአብሔር አብ ዓለምን እጅግ ስለወደድ ዓለምን ለማዳን ውድ የሆነውን ስጦታ ሰጠን፤ አንዲያ ልጁን ለእኛ ሰጠን፣ ለያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወቱን የሚሰጠ፣ ለዚህ ሲል የሞተ ከሙታን የተነሣ እና ወደ አባቱ ተመልሶ የሄደ፣ ከአባቱ ጋር ሆኖ መንፈስ ቅዱስን ሊልክልን ቃል የገባውን ልጁን ይልክልናል።ስለሆነም ቅድስት ሥላሴ ፍቅር ነው ፣ ዓለምን የሚያድን እና እንደ አዲስ አድርጎ የሚፈጥር ፍቅር። ዛሬ ስለ እግዚአብሔር አብ፣ ስለ ወልድ እና ስለ መንፈስ ቅዱስ ስናስብ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እናስባለን! እንደተወደድን ሆኖ ከተሰማን መልካም ነው። “እግዚአብሔር ይወደኛል” - ይህ ዛሬ ሊሰማን የሚገባን ስሜት ነው።

ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን  ለዓለም እንደ ሚሰጥ በሚናገርበት ወቅት ​​ስለ አብርሃም እና ልጁን ይሳቅን ለመሰዋት ያደርገውን ሙከራ የሚገልጸው የዘፍጥረት መጽሐፍ የሚናገረው ቃል  በአዕምሮአችን እናስባለን (ዘፍጥረት 22፡1-14)፣ “ጥልቀቱ የማይለካ” ፍቅር እግዚአብሔር ለልጆቹ አለው። እኛም እግዚአብሔር ለሙሴ እንዴት ራሱን እንደገለጠ እናስባለን “ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” (ዘጸ 34፡6)።  የዘፀአት መጽሐፍ እንደሚተርከው ይህ ከእግዚአብሔር ጋር የተደረገው ግንኙነት ሙሴን አበረታቶታል፣ እርሱም “አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን” (ዘፀሐት 34፡9)። እግዚአብሔር ልጁን በመላክ እንዲሁ አደረገ። እኛ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የልጁ ልጆች ነን! እኛ የእግዚአብሔር ቅርስ ነን!

ውድ ወንድሞች እና እህቶች! የዛሬው በዓል በእግዚአብሔር ውበት እንደገና እንድንደሰት ይጋብዘናል፣ ውበት ፣ ቸርነት እና በቀላሉ የማይገለጽ እውነት። ነገር ግን ውበት ፣ መልካምነት እና ትህትና ያለው እውነት ቅርብ ነው ፣ ወደ ህይወታችን ለመግባት ቃል ሥጋ ይሆናል፣ በታሪካችን፣ በእያንዳንዳችን ታሪክ ውስጥ ለመግባት እያንዳንዱ ወንድ እና ሴት የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ወደ እኛ ይመጣል። እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን መቀበሉ በራሱ እምነት ነው፣ ይህንን ፍቅር መቀበላችን በራሱ ክርስቶስ የሚሰጠንን መንፈስ ቅዱስ መቀበል ማለት ነው፣ መንፈስ ቅዱስ እንድንነቃነቅ ያደርገናል፣ መንፈስ ቅዱስን እድንገናኝ፣ በእርሱ እንድንተማመን የሚያደርገን የክርስትና ሕይወት መሰረት ነው። መውደድ፣ እግዚአብሔርን መገናኘት ፣ እግዚአብሔርን መፈለግ፤ እርሱ እራሱ አስቀድሞ እኛን ይፈልገናል።

በቅድስት ሥላሴ ውስጥ ማረፊያ ያላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔርን ፍቅር በደስታ በተሞላ ልብ እንድንቀበል ትረዳን ዘንድ በደስታ እንድንሞላ እንዲሁም በዚህ ዓለም ጉዞአችን ውስጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንኖር ወደ መንግሥተ ሰማይ በሚያመራው መንገድ ላይ መጓዝ የምንችልበትን ፀጋ ከልጇ እንድታሰጠን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

07 June 2020, 19:14